አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ የባህር ትራ ንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የሎጅስቲክስ አገልግሎትን ፈጣንና ዘመናዊ ለማድረግ የደረቅ ወደብ ማስፋፊያዎችን እየሠራ ነው። ለወደብ ማስፋፊያዎችም ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር በጀት መያዙን አመልክቷል።
የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሮባ መገርሳ እንደገለጹት፤ ሞጆ ላይ ለሚሰራው የደረቅ ወደብ ማስፋፊያ በዓለም ባንክ በጀት 150 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ተይዟል። በቀጣይም እስከ 300 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ የማስፋፊያ ፕሮጀክት ይሰራል። ይህም ሞጆን ትልቅ የሎጅስቲክስ ከተማ ለማድረግ የሚያስችል ይሆናል፡፡
ግንባታውን በዘመናዊ ማሽኖችና ቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ሥራ አስፈፃሚው ተናግረው፣ በአሁኑ ወቅት ዘመናዊ የወደብ ማስተናገጃ ዕቃዎች መገዛታቸውንና ተጨማሪ መጋዘኖችም እየተገነቡ መሆኑን አስታውቀዋል።
ድሬዳዋ ከተማ ላይ ዘመናዊ ደረቅ ወደብ በ69 ሚሊዮን ዶላር እየተገነባ እንደሆነም አቶ ሮባ ገልፀው ፣ በተመሳሳይ ኮምቦልቻ ከተማ ላይ በ25 ሄክታር መሬት ላይ ደረቅ ወደብ እየተገነባ መሆኑን ጠቁመዋል። በደቡብ ጎንደር ወረታ እና መቐለ ላይም ደረቅ ወደብ ግንባታ እየተሠራ ሲሆን በሌሎች አካባቢዎችም የሚጀመር መሆኑን አስገንዝበዋል። ለደረቅ ወደብ ማስፋፊያዎች የትራንስፖርት ችግሩን ለመፍታት ከፍተኛ የመጫን አቅም ያላቸው 150 ከባድ ተሽከርካሪዎች ተገዝተዋል።
የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎቱን ለማዘመን ከዓለም አቀፍ ወኪሎች ጋር በምክክር መድረክ የልምድ ልውውጥ እንደሚደረግ ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል። የአገሪቱ የወጪ ንግድ ተወዳዳሪ እንዲሆን ከተለያዩ የዓለም አገራት ወኪሎች ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
‹‹የሎጅስቲክስ አገልግሎት አፈፃፀም ከሚለካባቸው ነገሮች አንዱ መሰረት ልማት ነው›› ያሉት አቶ ሮባ፤ የትራንስፖርት አገልግሎት ተግዳሮት እንዳይሆን በኮሪደሮች አካባቢ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በ2011 ዓ.ም በጀት ዓመት 3 ሚሊዮን 855 ሺ 248 ቶን ጭነቶች አጓጉዟል። 796 ሺ 955 በራሱ መርከቦች ሲሆን የተቀሩት 3 ሚሊዮን 58 ሺ 293 ቶን ጭነቶች በሌሎች አገራት መርከቦች የተጓጓዙ ናቸው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 8/2011
ዋለልኝ አየለ