አዲስ አበባ፤ በቦሌ አራብሳ በ150 ቀናት እንዲጠናቀቁ ታቅዶ የተጀመሩ 15 የኮንዶሚኒየም ህንጻዎች ጥራታቸውን ጠብቀው በፍጥነት እየተገነቡ መሆኑን እና በሐምሌ ወር መጨረሻ ቀለም ተቀብተው እንደሚጠናቀቁ የልደታ ቤቶች ግንባታ ጽህፈት ቤት አሳውቋል።
በአዲስ አበባ ቤቶች የልደታ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አረጋ አባተ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ከቤቶቹ ውስጥ 224ቱ ስቱዲዮ፣ 423ቱ ባለአንድ መኝታ፣ 454ቱ ደግሞ ሁለት መጥታ እንዲሁም 69ኙ የንግድ ቤቶች ናቸው። የካቲት ወር ውስጥ የተጀመሩት የኮንዶሚኒየም ቤቶች በፍጥነት እና በጥራት እየተገነቡ ስለመሆናቸው ቁጥጥር እየተደረገ ይገኛል። ቤቶቹ በሐምሌ ወር መጨረሻ ከነቀለም ቅባቸው ተጠናቀው ለተጠቃሚዎች ይተላለፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ግንባታዎቹ አሁን 66 ነጥብ 2 በመቶ ላይ ናቸው።
እንደ አቶ አረጋ ከሆነ፣ ቤቶቹ እየተገነቡ የሚገኙት ቦሌ አራብሳ ሲሆን፣ በካሳ ክፍያ ምክንያት እስከ 2011 ዓ.ም አጋማሽ ሳይገነቡ የቀሩት ናቸው። በመሆኑም ሲጠናቀቁ በቀጥታ እጣ ውስጥ ገብተው ለተጠቃሚ ይተላለፋሉ። በግንባታው ላይ የእነ ቶሎ ቶሎ ቤት አይነት የጥራት ችግር እንዳይፈጠር ካለፉት ጊዜያት በበለጠ ትኩረት ተሰጥቷል። አንዱ ኮንትራክተር ጋር ግብአት እጥረት ሲፈጠር ከሌላው እየወሰደ እንዲጠቀም በማድረግ በፍጥነት እንዲሰሩ የሚያደርግ አሰራር ተግባራዊ ተደርጎባቸዋል።
የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ጋሻው ተፈራ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢንጂነር ሰናይት ዳምጠው ዛሬ በግንባታ ቦታዎቹ ተገኝተው አስፈላጊውን መመሪያ ይሰጣሉ። እስከአሁንም ኢንጂነሯ ቤቶቹ በጥራት እና በፍጥነት እንዲጠናቀቁ አስፈላጊውን መመሪያ እየሰጡ ክትትል አድርገዋል።
እንደ አዲስ አበባ ቤቶች ልማት ጽህፈት ቤት መረጃ ከሆነ፣ እየተገነቡ የሚገኙት 1ሺ170 ቤቶች ከሌሎች ቤቶች ጋር አንድ ላይ ለ20/80 የኮንዶሚኒየም ቤቶች በእጣ መልክ ለነዋሪዎች ይተላለፋሉ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 8/2011
ጌትነት ተስፋማርያም