“አዲሱ ትርክት ብዝሃነትን ያቀፈና አብሮነትን መሠረት ያደረገ መሆን አለበት” – አቶ ብናልፍ አንዱዓለም የሰላም ሚኒስትር

አዲስ አበባ፡- አዲሱ ትርክት ብዝሃነትን ያቀፈ አብሮነትን መሠረት ያደረገ መሆን አለበት ሲሉ የሰላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዱዓለም ገለጹ።

የሰላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዱዓለም እንደገለጹት፤ አዲሱ ትርክታችን ብዝሃነትን ያቀፈ ወንድማማችነትንና አብሮነትን መሠረት ያደረገ መሆን አለበት።

ባለፉት ጊዜያቶች በሀገረ መንግሥት ግንባታ ላይ የተጠቀምንባቸው ትርክቶች የፈጠሩት ችግር አለ ያሉት ሚኒስትሩ፤ በተለይም አንድነትን ማዕከል ያደረጉ ልዩነትን የማይቀበሉና ልዩነትን ማዕከል ያደረጉ የፖለቲካ ትርክቶች ነበሩ ብለዋል።

ትርክቶቹ ልዩነትን ተቀብሎ በማስተዳደር በኩል ችግር እንደነበረባቸው ጠቅሰው፤ በልዩነቶች ላይ ብቻ ያጠነጠነና ዜጎች በጥላቻ እንዲተያዩ ያደረገ ትርክት ነግሶ እንደነበር ገልጸዋል።

የበፊቶቹ ትርክቶች ያስከተሉትን ጉዳት በአግባቡ ያየ፣ የፈተሸ ያንን ሊያርም የሚችል አዲስ ትርክት እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት አቶ ብናልፍ፤ አዲሱ ትርክት ብዝሃነትን ያቀፈ ወንድማማችነትን ፣እህትማማችነትንና፣ አብሮነትን መሠረት ያደረገ መሆን አለበት ብለዋል።

በዜጎች መካከል የእይታ፣ የአስተሳሰብ፣ የፖለቲካ፣ የእምነት ፣ የአካባቢና፣ የጾታ ልዩነቶች ሊኖሩ እንደሚችል አመላክተው፤ በሀገራዊ ጥቅሞች ላይ አንድ መሆንና ብሔራዊ መግባባት ላይ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ሀገራዊ ጥቅም ላይ ከተለያየን ሀገር ግንባታ የሚባል ነገር አይሠራም ያሉት ሚኒስትሩ፤ ልዩነቶች መፈታት መቋጨት የሚችሉት ብሔራዊ መግባባት ሲቻል ነው ሲሉ አስረድተዋል። ያለውን መንግሥት ስለጠሉና ተቃውሞ ስላለን ብቻ ሀገር ማፍረስ እንደማያስፈልግ ገልጸው፤ የሀገርን ጥቅም ከመንግሥት ጋር ባለማያያዝ ማስከበር እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ልዩነቶች እንደተጠበቁ ሆነው ኢትዮጵያ የምትባል የጋራ ቤት አለችን የሚል መግባባት መፈጠር አለበት ያሉት አቶ ብናልፍ፤ በኢትዮጵያዊ ማንነት ላይ የማይደራደር ትውልድ መፈጠር አለበት ብለዋል።

አሁን ላለው የኢትዮጵያ የሰላም ማጣት ችግር ዋናው ምክንያት ፖለቲካዊ ችግር መሆኑን ጠቅሰው፤ ከማንነት፣ ከወሰን፣ ከአስተዳደር፣ ከክልልነትና አስተዳደራዊ ጥያቄዎች፣ ከሀብት አጠቃቀምና ፍትሐዊነት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ተመርኩዘው የሚነሱ ግጭቶች መኖራቸውን አስታውቀዋል።

ለውጥ ለማምጣት የኃይልን አማራጭ ብቻ ታሳቢ የማድረግ መጥፎ ባህል እየጎላ መጥቷል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ቀደም ባሉት ጊዜት በቀይ ሽብርና በነጭ ሽብር ፣አብዮተኛና ፀረ-አብዮተኛ በሚል ስያሜ ትውልድ መስዋዕትነት መክፈሉንም አስታውሰዋል።

በሰለጠነ መንገድ ከታየ የብዙ ሃሳብ መኖር ጠቃሚ ነው፤ ከሃሳቦቹ መካከል ተጨምቆ የተሻለ ሃሳብ ሊያመጣ ይችላል። የፖለቲካ ባህሉ ከመገዳደል ይልቅ ወደ መደራደር መቀየር አለበት ብለዋል

የመገዳደል፣ በኃይል የመጠፋፋት መንገድ ሀገሪቱን ወደ ፊት እንዳላራመዳት ገልጸው፤ ኢትዮጵያ በበርካታ ውስብስ ችግሮች ውስጥ እንድትቀጥል ከማድረግ ውጪ ለሀገሪቱ መፍትሔ የሚሆን ነገር እንዳላመጣ አስረድተዋል።

ባለፉት ዓመታት የፖለቲካችን በሽታና ችግር እሴቶቻችንም ላይ መሸርሸር ማስከተሉን ተናግረው፤ ፖለቲከኞቻችን፣ ልሂቃኖቻችን፣የተለያዩ የኅብረተሰብ መሪዎች ወደ መነጋገርና መደራደር መምጣት እንዳለባቸው አንስተዋል።

ግጭቶች ቁርሾ ሆነው እንዳይቀጥሉ እርቀ ሰላም፣ የሽግግር ፍትሕና ሀገራዊ ምክክር ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ሁሉም ሊሠራ እንደሚገባ አመላክተዋል።

ማርቆስ በላይ

አዲስ ዘመን ሰኞ መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You