የብሔራዊ መታወቂያ ካርድ ምዝገባ በኦንላይን ተጀመረ

አዲስ አበባ፦ ብሔራዊ መታወቂያ ካርድን በኦንላይን ተመዝግቦ ማግኘት እንደሚቻል የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም አስታወቀ። በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት በኩል ካርዱን ካሉበት ቦታ የማድረስ ሥራ መጀመሩንም ገልጿል።

በብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አቤኔዘር ፈለቀ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ የብሔራዊ መታወቂያ ካርድ የሕትመት ሥራ በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ሲከናወን ቆይቷል። የብሔራዊ መታወቂያ ካርዱን ማግኘት የሚፈልጉ ዜጎችም አገልግሎቱን ለማግኘት በአካል መገኘት ይኖርባቸው ነበር።

አሁን የብሔራዊ መታወቂያ ካርድ ለማግኘት ግዴታ በአካል መገኘት አያስፈልግም ያሉት አቶ አቤኔዘር፤ ዜጎች አገልግሎቱን በቀላሉ ማግኘት እንዲችሉ የኦንላይን ምዝገባ ተጀምሯል። የክፍያ ሥርዓቱም በቴሌ ብር እና በባንክ መክፈል እንደሚቻል ጠቁመዋል።

የብሔራዊ መታወቂያ ካርድ ማግኘት የሚፈልጉ ዜጎች card-order.fayda.et ድረ ገጽ ላይ በኦንላይን መመዝገብ እንደሚችሉ የገለጹት አቶ አቤኔዘር፤ ከዚህ ባለፈ በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት በኩል ካርዱን ካሉበት ቦታ እንዲመጣላቸው ማዘዝ እንደሚችሉ ተናግረዋል። ይህ አገልግሎት በተለይ በክፍለ ሀገር የሚኖሩ ዜጎችን ተደራሽ ያደርጋል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ነዋሪዎችም ካርዱን ካሉበት ቦታ ማግኘት ይችላሉ ያሉት አቶ አቤኔዘር፤ ዜጎች የብሔራዊ መታወቂያ ካርድ የኦንላይን ምዝገባ ከማድረጋቸው በፊት የፋይዳ ቁጥራቸውን የሚገልጽ የጽሑፍ መልዕክት በስልካቸው የተላከ መሆኑን ማረጋገጥ እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል።

እንደ አቶ አቤኔዘር ገለፃ፤ ከዚህ በፊት የነበረው የብሔራዊ መታወቂያ ካርድ አሰጣጥ በአካል መገኘት የሚጠይቅ በመሆኑ ካርዱን ማግኘት የሚፈልጉ በርካታ ዜጎች በአንድ ቦታ እንዲገኙ አድርጓል። ይህም ረጅም ሰልፍ እንዲሁም ካርድ ሳይወስዱ የሚመለሱ ዜጎች እንዲበራከቱ አድርጓል። አሁን የተጀመረው የአሠራር ሥርዓት ይህንን ችግር ይቀርፋል።

በተመሳሳይ ነጋዴዎች እና ግብር ከፋዮች ይህንን የኦንላይን ምዝገባ ሥርዓት መጠቀም ይችላሉ። ከዚህም በተጨማሪ የንግድ ፍቃድ በሚሰጡባቸው ቦታዎች የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ባለሙያዎች እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

እንደ አቤኔዘር ገለፃ፤ በአዋጁ መሠረት የመታወቂያው ትክክለኛ መጠሪያ የኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያ ነው። ይህንን መታወቂያ እውን ለማድረግ እስከ አሁን ሦስት አሠራሮች ተዘርግተዋል። አንደኛው በኪስ የሚያዝ የፕላስቲክ መታወቂያ ሲሆን ሁለተኛው በፒዲኤፍ የተዘጋጀ ነው። ሦስተኛው በስልክ ላይ መታወቂያውን በማስቀመጥ መገልገል የሚቻልበት ሥርዓት ነው።

ሦስቱ አማራጮች በሕግ ፊት እኩል ተቀባይነት አላቸው። ይህንን በሚመለከት ለፖሊስ፣ ለክልሎች እና ለተለያዩ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ተሠርተዋል ያሉት አቶ አቤኔዘር፤ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ በኪስ የሚያዝ ወረቀት ብቻ ሳይሆን የራሱ መለያ /ፋይዳ/ የሚባል ቁጥር ይዞ በማንኛውም ቦታ በቁጥሩ ምክንያት አገልግሎት ማግኘት የሚያስችል ዘመናዊ አሠራር መሆኑን አስረድተዋል።

ዲጂታል መታወቂያ በኢትዮጵያ የሚኖር ማንኛውም ዜጋ የራሱን ማንነት የሚገልጽበት መለያ ነው ያሉት ያሉት አቶ አቤኔዘር፤ አንድ ሰው ከቤቱ ሆኖ የባንክ አካውንት መክፈት፣ የኢንሹራንስ አገልግሎት ማግኘትና በአገልግሎት ሰጭውና ተቀባዩ ዘንድ መተማመን መፍጠር የሚያስችል ነው ብለዋል።

በ2016 ዓ. ም ማብቂያ ለ25 ሚሊዮን ዜጎች የብሔራዊ መታወቂያ ፋይዳ ቁጥር ለመስጠት እየተሠራ ነው ያሉት አቶ አቤኔዘር፤ እስከ አሁን ከሦስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የብሔራዊ መታወቂያ ፋይዳ ቁጥር እንደተሰጠ ገልጸዋል።

በ2018 ዓ. ም ማብቂያ ከ90 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የብሔራዊ መታወቂያ ፋይዳ እንዲኖራቸው ይደረጋልም ብለዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን መጋቢት 19/2016 ዓ.ም

Recommended For You