‹‹የልብና ተያያዥ ችግሮችን ጨምሮ ለከፋ የጤና ችግር ያጋልጣል›› –የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጥናት
አዲስ አበባ፡- የረጋ የፓልም የምግብ ዘይት ከፍተኛ የጥራት ችግር እንዳለበትና ይህም የልብና ተያያዥ የጤና ችግሮችን ጨምሮ ለከፋ የጤና ችግር ሊያጋልጥ የሚችል መሆኑን የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያደረገው ጥናት አመላከተ፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ እንደገለጹት፤ በአገሪቱ የዘይት ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ በመምጣቱ መንግሥት በልዩ ድጎማ ከውጭ የሚያስገባው የረጋ የፓልም የምግብ ዘይት ከፍተኛ የጥራት ችግር ያለበት መሆኑን ተቋሙ ያጠናው ጥናት አመልክቷል፡፡
ከህብረተሰቡ የሚመጡ ጥቆማዎችንና አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ያሰራጩትን መረጃ መነሻ በማድረግ ኢንስቲትዩቱ በፓልም የምግብ ዘይት ላይ ባደረገው ጥናት ዘይቱ በዓለም የጤና ድርጅት ከተቀመጠው ደረጃ በላይ ከሃምሳ እስከ ሰማንያ በመቶ የሚሆን ከፍተኛ የአሲድ መጠን የያዘ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ ይህም በገዳይነቱ የሚታወቀውን የልብና ተያያዥ የጤና ችግሮችን ጨምሮ በህብረተሰቡ ላይ የከፋ የጤና ችግር ሊያስከትል የሚችል መሆኑን የጥናቱ ውጤት ማመላከቱን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም በህብረተሰቡ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል መንግሥት ለጤና ተስማሚ የሆኑ አማራጭ የምግብ ዘይቶችን የሚደጉምበትን መንገድ ለማፈላለግ የጥናቱ ውጤት ለጤና ሚኒስቴር ቀርቧል፡፡ የጤና ሚኒስቴርም የጥናቱን ውጤት ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ያቀረበ ሲሆን ጽህፈት ቤቱም የሚመለከተው አካል ማለትም የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ችግሩን ታሳቢ በማድረግ አዳዲስና አማራጭ የመፍትሔ ሃሳቦችን እንዲያቀርብ አቅጣጫ ሰጥቷል፡፡የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በተቀ መጠው አቅጣጫ መሰረት በጉዳዩ ላይ እየመከረበት መሆኑንና በቅርቡም ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ቀርቦ የውሳኔ ሃሳብ እንደሚሰጥበት ዋና ዳይሬክተሩ ዶክተር ኤባ አመላክተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጋዜጣ ግንቦት 8 ቀን 2011 ዓ.ም ጉዳዩን አስመልክቶ የረጋ ፓልም የምግብ ዘይትን ለረጅም ጊዜ መጠቀም ለከፋ የጤና ችግር ሊያጋልጥ እንደሚችል ጤና ሚኒስቴርን ጠቅሶ ዘግቦ የነበረ ቢሆንም ጉዳዩ የሚመለከተው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ግን “የጤና ጉዳቱ በዓለም የጤና ድርጅት እስካልተረጋገጠ ድረስ አቅርቦቱ ይቀጥላል” የሚል ምላሽ መስጠቱ ይታወሳል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 6/2011
ይበል ካሳ