
ዘንድሮ የጊዜ አጋጣሚ ሆኖ ረመዷንና ዐቢይ ጾም ለአንድ ወር ያህል በተመሳሳይ ጊዜ ይጾማሉ። በእስልምናው እምነት ተከታዮች ዘንድ የረመዷን ወር ልዩ ቦታ ያለው ነው። በክርስትናም ቢሆን የዐቢይ ጾም የበረከት ሥራዎች የሚሠሩበት ጊዜ መሆኑ ዕሙን ነው። ታዲያ በእነዚህ የጾም ወራት ለተቸገሩ መርዳት፣ ጾመኞችን ጾም ማስፈታት ወይም ማስፈጠር የተለመደ ተግባር እየሆነ መጥቷል።
ጾመኞችን ከሚያስፈጥሩ ተቋማት መካከልም ባቡልኽይር በጎ አድራጎት ማኅበር አንዱ ነው። ወይዘሮ ሀናን ማሕሙድ የባቡልኽይር በጎ አድራጎት ማኅበር መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ናቸው። ወይዘሮ ሀናን ማሕሙድ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ባደረጉት ቆይታ የረመዷን ወር ያለእምነት ልዩነት አቅመ ደካማ ጾመኞችን ጾም ማስፈታት ወይም ማስፈጠር መቻል የኢትዮጵያውያን አብሮነት ማሳያ መሆኑን ይገልጻሉ። ለምስኪኖች አለኝታ መሆን የዱያንም (የምድርን)ና የአኼራንም(ሰማያዊ) ደስታን ያጎናጽፋል ይላሉ።
በባቡልኽይር ቅጥር ግቢ ውስጥ አሁን ላይ በቀን አምስት ሺህ ያፈጥራሉ። ከ40 በላይ በጎ ፍቃደኛ የክርስትና እምነት ተከታዮች መጥተው በር ላይ ከማስተባበር ጀምሮ ቀድመው ሾርባ በመቅዳት፣ ቴምር በማከፋፈል እንዲሁም ወገኖቻቸውን ጾም ሲያስፈቱ ወይም ሲያስፈጥሩና አለኝታ መሆናቸውን ሲያሳዩ መመልከት ልዩ ስሜት እንደሚፈጥር ይገልጻሉ።
በተጨማሪም ጎረቤቶች ወደ ማኅበሩ መጥተው በፍቅር ሲያግዙና አቅመ ደካሞች በልተው ሲደሰቱ ማየት ከምንም በላይ ነው ባይ ናቸው። እንደ ሀገር ለአንድ ዓላማ ተባብሮ መቆም፣ መደጋገፍና መተሳሰብ ትልቅ ፋይዳ አለው የሚሉት ወይዘሮ ሀናን፤ ማኅበሩ ረመዷን ከመግባቱ በፊት በቀን ሰባት መቶ ሺህ ብር እንደሚያወጣ ያብራራሉ።
ዘንድሮ የረመዷን ወር በርካታ ዜጎች ወደ ማኅበሩ በመምጣታቸው አሁን ላይ የቀን ወጪ አንድ ሚሊዮን ብር መድረሱን ያስረዳሉ። ከእስልምና እምነት ተከታዮች በተጨማሪም አቅመ ደካማ የክርስትና እምነት ተከታዮች ከአራት እስከ ስድስት ሰዓት እንደሚስተናገዱ ይናገራሉ። ይህም ማኅበራዊ መስተጋብርን ለማጠናከር ሚናው የጎላ ነው።
በመቀጠልም እስከ ምሽት የእስልምና እምነት ተከታዮች ይስተናገዳሉ። የጾም መያዣ(ሱሁር)ና ጾም መፍቻ(ኢፍጣር) ቴምር፣ የገብስ ሾርባ፣ ዶናትና ስጋ ወጥ በማዘጋጀት አቅመ ደካሞች የማስፈጠር ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ይገልጻሉ። ሕይወታቸውን ጎዳና ካዳረጉ ዜጎች ውጪ ያሉት ዜጎች የማፍጠሪያ ምግብ ወደ ቤት ይወስዳሉ። በረመዷን ወር ከወገኑ ጎን ቆሞ መገኘት ከሌሎች ግዜ ይለያል፤ ከዛም ባሻገር ተቸግረው ነገር ግን የሰው ዓይን ለማየት የሚፈሩ ዜጎችን ቤት ለቤት እንደሚደረስላቸው አንስተዋል።
ከአስር ዓመት በፊት ዩኒፎርም የለበሱ ተማሪዎች ከትምህርት ሰዓት ውጪ ከጎረምሶች ጋር እየተጋፉ ምግብ ሲመገቡ ማየታቸው ለማኅበሩ መመሥረት ምክንያት መሆኑን የሚናገሩት ወይዘሮ ሀናን፤ ተማሪዎቹ ለምን እንደወጡ ሲጠየቁ ተርበው እንደሆነ ገልጸውልኛል ይላሉ።
ከዚህም ባለፈ በርካታ አቅመ ደካማ ኢትዮጵያውያን የሚገጥማቸውን ችግር ለመቅረፍ ታስቦ መመሥረቱን ይናገራሉ።
ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ባለሀብቶች በሥራ እቅዳቸው ውስጥ ቢያንስ በዓመት ሁለት ጊዜ የበጎ አድራጎት ማኅበርን ለመጎብኘት ማቀድ ይኖርባቸዋል ይላሉ። ይህም ቀጣዩ ትውልድ መልካምነት ስላለው ዋጋ ትምህርት እንዲያገኙ እንደሚያደርግ ያስረዳሉ። በርካታ አረጋውያን እንዳይራቡ ለማድረግ የተከፈለው ዋጋ ከባድ ቢሆንም ለበጎነት የተከፈለ ስለሆነ ያኮራልም ያስደስታልም ሲሉ ይገልጻሉ።
ማኅበሩ ቋሚ ገቢ ባይኖረውም በልበ ቀና ኢትዮጵያውያን ድጋፍ በማሰባሰብ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ይናገራሉ። በመሆኑም ተቋማትና ግለሰቦች አቅማቸው በፈቀደ መጠን ለማኅበሩ ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ መልዕክታቸውን አክለዋል።
አማን ረሺድ
አዲስ ዘመን መጋቢት 19 ቀን 2016 ዓ.ም