ኔታንያሁ የእስራኤልን የልዑካን ቡድን የዋሽንግተን ጉዞ እቅድ መሰረዛቸው አሜሪካን አስቆጣ

ኔታንያሁ የእስራኤልን የልዑካን ቡድን የዋሽንግተን ጉዞ እቅድ መሰረዛቸው አሜሪካን አስቆጣ።

አሜሪካ በተመድ በቀረበው የተኩስ አቁም የውሳኔ ሀሳብ ላይ ድምፀ ተዓቅቦ ካደረገች በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከፍተኛ የእስራኤል የልዑካን ቡድን በዋሽንግተን ሊያደርገው የነበረውን የጉዞ እቅድ ሰርዘዋል።

አሜሪካ በእሥራኤል ድርጊት ከፍተኛ ብስጭት እንደተሰማት ገልጸለች።

“ይህ በጣም የሚያበሳጭ ነው። በራፋ ስላለው ሁኔታ አማራጮችን ለመፈለግ የሚያስችል ውይይት እንድናካሂድ የሚያስችለንን የዋሽንግተን ጉዞ በመሰረዛቸው በጣም ተበሳጭተናል” ብለዋል፡፡ የዋይትሀውስ ቃል አቀባይ ጆን ክርቢይ።

ክርቢይ እንደተናገሩት ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ለሥራ ጉብኝት አሜሪካ ከሚገኙት የእስራኤሉ የመከላከያ ሚኒስትር ዩአቭ ጋላንት ጋር በታጋቾች፣ በሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እና በራፋ ለንጹሐን ሊደረግ ስለሚገባው ከለላ ጉዳይ ተገናኝተው ይወያያሉ።

ክርቢይ አሜሪካ በተመድ ድምፀ ተዓቅቦ ብታደርግም የአሜሪካ ፖሊሲ አልተቀየረም ብለዋል።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት እስራኤል በጋዛ ጉዳይ በምታራምደው ፖሊሲ ዙሪያ ያላቸውን ስጋት ማንሳታቸውን ይቀጥላሉ ሲሉ ክርቢይ ተናግረዋል።

ክርቢይ “በራፋ ሊደረግ የሚችል የእግረኛ ጦር ጥቃት ትልቅ ስህተት ነው የሚለውን እይታችንን የሚቀይረው ምንም ነገር የለም” ብለዋል።

እስራኤል በጋዛ ድንበር የምትገኘዋን እና ጦርነት ሸሽተው የተፈናቀሉ ሰዎች የተጠለሉባትን በግብፅ ድንበር የምትገኘውን የራፋ ከተማን ለማጥቃት የያዘችውን እቅድ በቅርቡ ማፅደቋ ይታወሳል።

ግብጽን ጨምሮ እስራኤልን እና ሀማስን እያደራደሩ ያሉ አካላት ይህን የእሥራኤልን እቅድ የከፋ አደጋ ያስከትላል በሚል ተቃውመውታል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ረቡዕ መጋቢት 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You