ሕይወት፣ ናፍቆት፣ ትዝታና ፍቅር

ናፍቆት እንዳረበበበት፣ ትዝታ እንደሰፈረበት፣ በፍቅር ገሰስ አጋሰስ እንደቆመ ሕይወት ምን ውበት ምን ጥያሜ አለ? ሄደን ሄደን አለመቆም ቢኖር.፣ ናፍቀን ናፍቀን አለመርሳት ቢኖር ያን ነበር ሕይወት የምለው፡፡ መጨረሻው በተሰወረ መጀመሪያ ላይ ሰውና ባለታሪክ መሆን…ነገን ባለማወቅ ውስጥ በተስፋ መዳከረ ይሄም የምፈራው ነው፡፡ እንደሰው ከተሰጡኝ የምሰጋው፡፡

ተፈጥሮ ከብዙ ስሜቶች ውስጥ የቀለመን የእንባና ሳቅ ስዕሎች ነን፡፡ ሰው የእንባና ሳቅ ስዕል፡፡ ይሄን ለመረዳት ወደትናንት አሻቅቡ ወደዛሬ አጎንብሱ..አልረሳ ያሏችሁን የሳቅና እንባ ድልብ ታሪኮች እንደምትጋፈጡ በወላዲቷ እምላለሁ፡፡ መቼ ደልቶን ብቻ ያውቅና? መቼስ እንደፈነጠዝን ቀረንና? አንድንም ካልናቸው ትካዜዎች ታክመን የለ..? ባላለፉ ካልናቸው ጊዜና አጋጣሚዎች ተላልፈን የለ? ካደሙን የሆኑ ነገሮቻችን አገግመን የለ? የማያልፉ ከሚመስሉን፣ እንዲደገሙ ከምንፈልጋቸው የሳቅ አለሞች ወጥተን የለ? ተመልሰው እንዳይመጡና ተመልሰው እንዲመጡ በማንከጅላቸውና በምንከጅላቸው ትናንትናዎቻችን ስር በአፍ ጢማችን የተደፋን ነን፡፡ ይነስም ይብዛም በፍቅር በኩል፣ ሰው በመሆን ግድም የተዋሃዱንን የሕይወትን ወያባና አይነግቡ የናፍቆትና የትዝታ በትር ቀምሰናል…ሰንበሩም አሁን ድረስ አለ፡፡ እኔም ይሄን ስጽፍ እናተም ይሄን ስታነቡ እንኳን ባልተመሳሰለ ስሜት ውስጥ ሆነን ነው፡፡

መጨረሻው በተሸሸገ መጀመሪያ ላይ ለመኖር ተስፋን መቋጠር በሰው ልጅ ላይ የፈጣሪ ታላቁ ሴራ እለዋለሁ፡፡ ካልሆነ ትናንት በዛሬ ሲጠራ ነገን ከዛሬ መሰወሩ ለምን ሆነና? መቼም እኛ ሰዎች አልሆን ሲለንና እንዳሳባችን ሳይሆን ሲቀር ነቃፊና አቃቂር አውጪዎች ነን፡፡ ከዘፍጥረት ጀምሮ ዛሬም ድረስ ሰው የፈጣሪ ባላንጣ ነው፡፡ አዳምና ሄዋን አምላክነትን ሻቱ፣ ሊቀመላዕክት ሳጥናኤል ፈጣሪ ነኝ አለ…ናቡከደነጾር ጌታ እኔ ብቻ ነኝ አለ..እናስ ጠላቱ አይደለንም?

እግዜር ለሁልጊዜም ከሰው ያፈነገጠ ነው…እንዳሳባችን አያስብም፡፡ ፈጠረን ገነት አኖረን..ገነት ውስጥ ካሉ ዛፎች ሞት ካለባት ከዚች እጸ በለስ በቀር ሁሉን ብሉ ሲል ነጻነትን ሰጠን፡፡ በነጻነታችን መሀል ራስ ወዳድነትን ዶለን አትብሉ የተባልነውን በላን..ከገነት ተባረርን፣ ተረገምን፣ የሞት ሞትን ሞትን፡፡ ይሄ ሁሉ ያለመታዘዛችን ዳፋ እንደሆነ ሳይገባን በእግዜር ላይ ጣትን መቀሰር ምን የሚሉት ውንብድና ነው? ከበላን በኋላም በበደላችን ሳይቆሽሽ ከክብሩ ዝቅ ብሎ በሞት ታረቀን፡፡

አንዳንድ ጊዜ ወደአእምሮዬ የምትመጣ ለማመን አስቸጋሪ የሆነች ሀሳብ ብጤ አለችኝ..እግዜር ነገን ከሕይወት መደበቁ፣ መጪውን ከዛሬ መሸሸጉ ከሰጠን የተስፋ ሕይወት ዳግመኛ እንዳንሸራተት ሊታደገን ቢሆንስ የምትል፡፡ ይቺ ሀሳብ ከብዙ መጠየቅ በኋላ ያገኘኋት እኔን ብቻ የምትወክል የግል መልሴ ናት፡፡

እንደነገ የሰው ልጅ ምን ባዳ፣ ምን በርሀ..ምን ጨለማ አለው? ነገ እኮ የአለመኖር አንድ ሁለተኛው ነው..፡፡ አለመኖርን ናፍቆ መጠበቅ ማንም ያላበደው እብደት ነው፡፡ የተሰጠንን አሁን ሳንኖር በራቀን ነገ መጨነቃችን አማኑኤል የሚያስገባ ሌላው እብደታችን ነው፡፡ ግን ከመጠበቅና ተስፋ ከማድረግ ውጪ አማራጭ የለንም..

በናፍቆት የተለበጡ አንዳንድ ቀኖችን እንደማስታወስ፣ እንደማውሳት ያለ ህመም የለም፡፡ ማስታወስ የማን ፈልጋቸውን አንዳንድ ነገሮች የሚዘነጋ የሰውነት ክፍል ቢኖረን የሚለው ከምኞቶቼ መሀሉን ነው፡፡ ዋና ህመም ሆኖ የሚመጣው ደግሞ ላለማስታወስ ማስታወስ ነው፡፡ ለመርሳት በሞከርናቸው ቁጥር በሚታወሱን..ላለመርሳት በጣርን ቁጥር በሚረሱን ነገሮች መሀል ሰው መሆን ከባዱ ፈተና ነው፡፡ መቼም ላለማስታወስ መሞከር መቼም ላለመርሳት እድል መስጠት ነው፡፡ ኤጭ..

አንዳንድ ቀንን ማውራት ያህል ህመም የለም፡፡ አንዳንድ ሰውን መራቅ ያህል ዋይ ዋይ የለም፡፡ ሕይወት ‹በበርቺና በሁሉም ያልፋል› እንዳትሽር ሆና የጎበጠችበት ማንም የማይደርስበት ቦታ አለ፡፡ ሊያቃኑት ሲሉ የሚሰበር፣ ሊያሽሩት ሲሉ የሚመረቅዝ፣ ሊረሱት ሲሉ የሚያገረሽ፡፡

ናፍቆት ግን ከምንድነው የተሰራው? ትዝታና ፍቅር ያሉበት ሕይወት ምን ይሆን ንጻሬው? ሁሉም ሰው ትናንትን ተሸክሞ የሚኖር ነው፡፡ በእድሜያችን አመሻሽ በብዙ እንባና ባለመሳቅ ስዕል የምናወጋው እልፍ የታሪክ ባለቤቶች ነን፡፡ እስኪ ልባችሁን በርብሩት ከሆነ ሰው ጋር የሆነ ቦታ በሆነ አጋጣሚ እንዠርግ ታሪክ አላችሁ፡፡ ስትታወስ በምትገርም አጋጣሚ..ይሆናል ተብሎ ባልተገመተ ሁኔታ ለትካዜ የጣሉን ብዙ ናቸው፡፡ የማንረሳው ሰው፣ የማንረሳው ቀን፣ የማንረሳው ወርና ዓመት የትዝታችንን ገሳ ለብሰው ወደዛሬ በማጨንቆር አሉ፡፡ አይመጡም እንሄድባቸዋለን እንጂ..፡፡ ለሌላ ታሪክ ስሎች ሆነን በዛሬ አከርካሪ ላይ ቆመናል..ትናንት ሲሆን በትዝታ ለምንወድቅበት ታሪክ፡፡ ትናንት እንደውብ ከተማ በልባችን ላይ አሸብርቆ አለ፡፡ በሆነ ሰው..የሆነ ቦታ..በሆነ አጋጣሚ ያረበበ፡፡ ለእያንዳንዳችን የማይፈርስ ከተማ ነው..የዛሬ ውበት የማያደበዝዘው..የነገ ተስፋ የማያወግገው..ባለቀለም ከተማ፡፡

ናፍቆት የነፍስ ሰንበሯ ነው እላለው..በሆነ ሰው የሆነ ጊዜ ላይ የተገረፈችው..የተሳመችው፡፡ ከንፈርም አለንጋም የናፍቆት ሰንበር አላቸው..ነፍስ ላይ የሚያርፍ፡፡ በነፍስ ገላ ላይ የንጹህ ከንፈርን ማህተም ያህል ናፍቆት ታውቃላችሁ? በአማኝ ልብ ላይ የከሀዲ ሰውን ያህል ጥዝጣዜ አለ? ሁለቱም በየፊናቸው ያማሉ..፡፡ ገፍቶን ለሄደም ሆኖ አጽንቶን ለሄደ ጥንድ እንባ አለን..ባረፈብን ጥላቸው ስር የሆንውን እያሰብን የምንሆነው፡፡

ናፍቆትን እንደቤት ጥራጊ ከህይወት አውላላ ላይ ጠራርጎ የሚያጠፋ መድሀኒት ወይም ግኝት ቢኖር አልረሳኝ ያሉ አንዳንድ ሰዎችን..አንዳንድ ቀኖችን..አንዳንድ አጋጣሚዎችን ለመርሳት እኔ ነበርኩ ማልጄ የምሸምተው፡፡

ናፍቆት ስለት ነው ነፍስን ገዝግዞ የሚያደማ..ደሙ ዘላለማዊ ነው፡፡ ሞት ካልሆነ ሕይወት የማይከልለው፡፡ ትዝታ በመኖር የተሳለ ስል ፈላጻ ነው..የነፍስን ነገ ገርስሶ የሚጥል፡፡ ትናንት የዛሬና የነገ..ዛሬ የመጪውና የለጣቂው ሾተል እንደሆነ ያልገባው..አሁን የከርሞ ደም እንባ እንደሆነ ያልተረዳ በትካዜ ካራ ራሱን ሊሰዋ ዳዴ ላይ ነው፡፡

ከሁሉም የሚበልጡ አንዳንድ ገጾች አሉ..ከምንም  የማይስተካከሉ ጥላማ ተሲያት፡፡ ቆንጆ ሴት ሰተት ያለችበት ልብ ጽላት እንዳለበት መቅደስ ነው፡፡ የቆንጆ ሴት ዳና በታሪክ ላይ አሻራው እንዳይጠፋ እንደሚፈለግ ጀብድ ነው፡፡ አይሆኑ መሆኛ፡፡ ከሁሉም ናፍቆት ቆንጆ ልጅ ገብታ የወጣችበት የልብ ህመም ይበልጣል፡፡ እረ እንደሱ አይደለም..ናፍቆት ትንሽና ትልቅ፣ አባጣና ጎርባጣ የለውም። ትላንት ሲሆን ሁሉም ዛሬ ተሲያት ነው..

እንዴት ገብታ እንደወጣች ሳስበው ለሁልጊዜ ይገርመኛል፡፡ አገባቧ መቼም ላለመውጣት ስለሚመስል መቼም አጣዋለው ያላልኩትን ታሪኬን አውርሻት ነበር፡፡ ለካ ሰው በምሥራቅ ታይታ በምዕራብ እንደምታሽቆለቁል ጀምበር ነው፡፡ በፍቅር ማበል ምን የሚሉት ስልጣኔ ነው? አስታውሳለው ከእሷ ጋር የተቀጣጠርንባትን የቅዳሜ ከሰዓት ስጠብቅ..አስታውሳለው ከፊቴ ያሉት ሀሙስና አርብ የዘላለም ያህል ርቀውኝ ሲያስተክዙኝ..አስተውሳለው መንፈቅ ለሰነበተ ፍቅራችን የሚሆን ስጦታና ፍቅር አዘጋጅቼ ወደእሷ እንደሄድኩ..ትዝ ይለኛል አጠገቧ ስቆም በህይወቷ ያልመጣ ደስታን ልፈጥርላት ተሰናድጄ እንደነበር..አስታውሳለው ስለብሰው እንደምትወደው በምትነግረኝ አለባበስ ፊቷ እንደቆምኩ፣ ፍቅሬን በቃልና በአበባ ልገልጽላት በአፌ በጎ ቃላትን በእጄ ደግሞ ፍቅር ነጋሪ ቀይ አበባ እንደታቀፍኩ…አስታውሳለው ወደእሷ ስሄድ በምን ኩራት ውስጥ እንደነበርኩ..አስታውሳለው በሕይወቴ አዲስ ታሪክ ልጽፍ እንደተዘጋጀሁ..አስታውሳለሁ ሳገኛት ግንባሯን ስሜ እንደምትወደው ወደማውቀው ወደሆነ ቦታ ወስጄ ላስደስታት ከራሴ ጋር እንደተማከርኩ..አስታውሳለው ከእሷ ጋር ብዙ ህልሞቼን..አስታውሳለው ተጋብተን ብዙ የደስታ ዓመታትን እንደምናሳልፍ ሳስብ…..እና ምን ሆነ አትሉኝም? የታሪኬ ደማቋ ሴት በአንድ ቀጭንና ነሆለል ቴክስት ‹አልመጣም አጠብቀኝ..ብላ ላለመመለስ ከህይወቴ መውጣቷን የነገረችኝ..

ጥሩም ይሁኑ መጥፎ በታሪኬ ላይ የተሰመሩ አንዳንድ መስመሮች የሕይወት ስዕሎቼ ናቸው፡፡ ያለፍኩበትን እንደካሴት ቀድተው ያስቀመጡ..በናፍቆት አለንጋ የሚቀጡኝ፡፡

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ዓርብ መጋቢት 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You