
በፓን አፍሪካን ተምሳሌትነትና በኦሊምፒክ መርህ መሠረት የሚካሄደው የአፍሪካ ጨዋታዎች ለ13ኛ ጊዜ በጋና አስተናጋጅነት መካሄደ ከጀመረ ሰንብተል። ውድድሩ ወደ መገባደጃ በተቃረበበት በዚህ ወቅትም ኢትዮጵያ በተለያዩ የአትሌቲክስ ውድድሮች በወርቅ ሜዳሊያዎች መድመቅ ቀጥላለች።
በበርካታ የስፖርት አይነቶች ተሳታፊ ሀገራት እየተፋለሙ፣ አሸናፊዎችም የሀገራቸውን ሰንደቅ ከፍ አድርገው እያውለበለቡ ይገኛሉ። ተሳታፊ ሀገራት እንደየአቅማቸው በተካኑባቸው ስፖርቶች ሜዳልያዎችን እየሰበሰቡ ብቃታቸውንም እያስመለከቱ ይገኛሉ። ኢትዮጵያም ከሌሎች ሀገራት አኳያ የምትሳተፈው በጣት በሚቆጠሩ ስፖርቶች ቢሆንም፤ በአትሌቲክስ ግን ግሩም የሚባል ድል እያስመዘገበች በሜዳሊያ ሰንጠረዡ ደረጃዋን ለማሻሻል ጥረት እያደረገች ነው።
በቦክስ፣ ብስክሌት፣ ጠረጴዛ ቴኒስ እና ውሃ ዋና ስፖርቶች አንጻራዊ ፍክክርን ማድረግ የቻለው ኢትዮጵያ በአትሌቲክሱ አስደማሚ ድሎች ማስመዝገቧን ቀጥላለች።
በሴቶች 5ሺ ሜትር የተጀመረው የአረንጓዴ ጎርፍ ድል በወንዶች 3ሺ ሜትር ወርቁን ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት መከተሉ ይታወሳል። ኢትዮጵያ በተካፈለችባቸው የአጭር ርቀትና የሜዳ ተግባራት ውድድሮች ስኬታማ ባትሆንም በተለመዱት የመካከለኛና ረጅም ርቀት ሩጫዎች ግን ሌሎች ድሎች ተከታትለው በመገኘታቸው በደረጃ ሰንጠረዡ ለውጥ አምጥታለች።
ሦስተኛው የወርቅ ሜዳሊያ ኢትዮጵያ እምብዛም በማትታወቅበት የ800 ሜትር የሴቶች ውድድር በወጣቷ አትሌት ጽጌ ድጉማ ማክሰኞ ምሽት ተመዝግቧል። በቅርቡ ግላስጎው ላይ በተካሄደው የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና ላይ በርቀቱ ታሪክ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያ የወርቅ ሜዳሊያ ያጠለቀችው ጥቁሯ ፈርጥ አትሌት ፅጌ ዱጉማ፤ በርቀቱ ያላት ተስፋ በግልጽ የታየ ነበር። ጠንካራዋ አትሌት በምትታወቅበት ድንቅ ብቃትና አጨራረስ በሳምንታት ልዩነት ሁለተኛውን የርቀቱን ድል በአፍሪካ ጨዋታዎች ለማስመዝገብ ችላለች። ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የተገኘችው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አትሌት ጽጌ ርቀቱን በ1:57.73 ሰዓት ማጠናቀቅ የቻለች ሲሆን፤ ግላስጎው ላይ ከገባችበት 2:01.90 የሆነ ሰዓት ብልጫ ያለውም ነው። በርቀቱ አብረዋት የተሳተፉት አትሌት አዳኑ ኔንቆ እና አስቴር አሬሬ ደግሞ ስምንተኛ እና ዘጠነኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቀዋል።
ቀጣዩ ድል በ10ሺ ሜትር የወንዶች ውድድር የተመዘገበ ሲሆን፤ የወርቅና የብር ሜዳሊያዎቹ ወደ ኢትዮጵያ ገቢ ሆነዋል። አመሻሽ ላይ በተካሄደው የፍጻሜ ውድድር በእልህ አስጨራሽ ፍልሚያ አስቀድመው ትኩረት ያገኙት ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች አሸናፊ ሆነዋል። በርካታ ጠንካራና ልምድ ያላቸው አትሌቶች በተፎካከሩበት መድረክ አትሌት ንብረት መላክ አሸናፊ በመሆን የወርቅ ሜዳሊያውን አጥልቋል። አትሌቱ ውድድሩን ለማጠናቀቅ የፈጀበት ሰዓት 29፡45፡37 ሲሆን፤ ተከትሎት ከገባው የሀገሩ ልጅ ጋር አትሌት ገመቹ ዲዳ ጋር ያለው የሰዓት ልዩነት የማይክሮ ሰከንዶች ብቻ መሆኑ ፉክክሩ ከፍተኛ እንደነበር ማሳያ ነው። አትሌት ገመቹ ዲዳ የሁለተኝነቱን ደረጃ በመያዝ የብር ሜዳለያውን ሲያገኝ የገባበት ሰዓት ደግሞ 239፡45፡68 በመሆን ተመዝግቧል። ጠንካራ ተፎካካሪያቸው የነበረው ኬንያዊ አትሌት ኢቫንስ ኪፕቱም ደግሞ 29፡47፡61 በሆነ ሰዓት በመግባት የነሐስ ሜዳሊያውን ወስዷል።
ኢትዮጵያ ካሰለፈቻቸው ጠንካራ አትሌቶች አንዱ የሆነው ኃይለማርያም አማረ ደግሞ ውድድሩን 7ኛ በመሆን ፈጽሟል።
ትናንት ሜዳሊያ የተመዘገበበት የአትሌቲክስ ውድድር ርምጃ ሲሆን፤ በወንዶች የወርቅ በሴቶች ደግሞ የብር ሜዳሊያው ተገኝቷል። ትናንት ረፋድ ላይ በተካሄደው የ20 ኪሎ ሜትር ርምጃ ውድድር ኢትዮጵያ በሁለቱም ጾታዎች ሦስት ሦስት አትሌቶችን አሰልፋለች። በዚህም በወንዶች ምስጋና ዋቁማ አምስተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ለሀገሩ አስመዝግቧል። የብር ሜዳሊያው ደግሞ በሴቶች ተመሳሳይ ውድድር በአትሌት ስንታየሁ ማስሬ የተመዘገበ ሆኗል።
የአፍሪካ ትልቁ የውድድር መድረክ የሆነው የአፍሪካ ጨዋታዎች 39 ሀገራት የሜሊያ ሰንጠረዡ ውስጥ መግባት ችለዋል። ኢትዮጵያም እስከ ትናንት ረፋድ 10 ሜዳልያዎችን ማስመዝገብ ችላለች። ከእነዚህ ሜዳሊያዎች አብዛኞች የተመዘገቡት በአትሌቲክሱ ሲሆን፤ 5 የወርቅ፣ 3 የብር እና 1 የነሐስ ሜዳሊያዎች ተገኝተዋል። በብስክሌት ስፖርት ደግሞ 1 የብር ሜዳሊያ በማስመዝገብ ከአትሌቲክስ ቀጥሎ ስሙ ሰፍሮ ይገኛል።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን መጋቢት 12/2016 ዓ.ም