ብርሀን

በሴትነቷ ፈር ውስጥ የብርሀን ጎርፍ ይንፎለፎላል። በምሽት ጉያዋ ውስጥ የእምዬ ማርያምን ምስል አትማ እንደምትንፏቀቅ ጨረቃ የብርሀን ምንጭ ከቀይ ፊቷ ላይ ይፈልቃል፡፡ ሰው ሆኖ ብርሀናማ መሆን ይቻላል? ሁሌ ከእጄ የማይጠፋው የአፈንጋጩ የኦሾ ፍልስፍና እንኳን የእሷን ውበት ያክል አላስለፈለፈኝም፡፡ ማማር ስትወድ። አንድም ቀን ከላመል ጉድፍ ጋር አላየኋትም።ደሞ ዘናጭ ናት..ከሰውነቷ ጋር ያበሩ፣ ውበቷን ያጎሉ ደመቅማቃ ልብሶች ታዘወትራለች፡፡

ጸጉሯ አጭር ነው..ፊትሽ ለአጭር ጸጉር የሚሆን ነው ተብላ ረጅም ጸጉሯን ያሳጨደችው ይመስለኛል። ብርሀናማ ፊት ከብርሀናማ አይኖች ጋር ፊት ለፊቴ ሲደነቀሩ አልደነባበርም ለቀን ሙሉ የሚሆነኝን የሀሳብ ስንቅ ከውብ ፊቷ ላይ እቃርማለው፡፡ የሆነ ልማድ አላት..አንድን ሰው ለረጅም ጊዜ የማየት።በዛ አይንና ውበት ለረጅም ጊዜ መታየትን ዳዋውን አስቡት? በውበቷ በኩል ስርየት የሌላቸውን ትላልቅ ሀጢዐቶችን ሰርቻለው። ካህን ፊት ቀርቤ ብናዘዛቸው መዳኛ የማላገኝባቸውን ሀጢዐቶች፡፡ ጸንቼ ሰንብቼ መሰነካከያዬ የእሷ ፊት ነው፡፡

የከፋው ነገር እኔን አትወደኝም፡፡ አንድ ቢሮ ውስጥ ለአስር ስንሰራ የማታወራው ከእኔ ጋር ብቻ ነው፡፡ ዓለም ላይ የሰው ልጅ ሁሉ አልቆ እኔና እሷ ብቻ ብንቀር የምትጎራበተኝ አይመስለኝም፡፡ እኔ ፊትና ሌሎች ወንዶች ፊት ሁለት አይነት ናት፡፡ የምትደናበረውና የምትመናቀረው እኔን ስታይ ነው።አንድ ቀን ቀናኝ..ፊት ለፊቴ ተረከዛማ ጫማዋ ተበጠሰ። በሁለት እጅዋ እንደ እሷ መንገደኛውን የሚያስቀላውጡ መልከኛ ፔስታሎችን አንጠልጥላለች። (እገምታለው ልብስ ነው የያዘችው።በየሳምንቱ ዓርብ በስራ በኩል ገበያ ወጥቶ ያማራትን የመሸመት አመል አላት) ተረከዛማ ጫማዋ ተበጠሰ፡፡ እኔን እርዳታ ከመጠየቅ ውጪ ምንም ምርጫ እንደሌላት በማሰብ ለመጀመሪያ ጊዜ የምታወራበትን አጋጣሚ በኩፈሳ ስጠብቅ እግሯን እየጎተተች አልፋኝ ሄደች።

እንደዚህ የጠላችኝ ምን በድያት ነው? ወደሚል የሀሳብ አዘቅት ተወረወርኩ፡፡

ከብዙ ቀናት በኋላ አንድ ረፋድ ውስጤ የሚመላለስን ሀሳብ ተከትዬ ከቢሮዬ ወጣሁ። እንደነገሩ ነው የለበስኩት። የመስሪያ ቤታችን እብድ መሳይ ሰራተኛ ነኝ። በዚህ ዝርክርክነቴ እዛች ጣኦት መሳይ ቆንጆ ሴት ፊት ስቀርብ ደፋርነቴ ነው የሚመጣብኝ፡፡ ከአእምሮ እንጂ ለአካል ግድ የለኝም፡፡

ማሰብ እወዳለው፡፡ በሆነ ርዕሰ ጉዳይ ላይ መወያየትና መከራከር የምዝናናበት ተፈጥሮዬ ነው። አንዳንዶች አለባበሴን አይተው በሩቁ የማይረባ ያደርጉኛል፡፡ የተረዱኝ ደግሞ በግድም ለወዳጅነት ይመርጡኛል። እንደ እኔ ነፍሱን በሀሳብ ያከሳ ሰው አላውቅም፡፡ አእምሮ አፍ ቢኖረው በአግባቡ የተጠቀመብኝ ሰው ብሎ ይኩራራብኝ ነበር፡፡ እኔ ስወጣ ጀምበር ስትገባ ከመንገድ ተገናኘን፡፡ ጸሀያማው ቀዬ ጠይም ደመና ለበሰ፡፡ ወዲያው ማካፋት ጀመረ፡፡ የተረገመ ቀን አልኩ፡፡ እንደ ሀሳቤ ሳይሆን ሲቀር እንዲህ የምለው መርገምት አለ፡፡ ጥሩ ላለበሰ፣ ሀሳባዊ ለሆነ ሰው ጸሀይ ሆነ ደመና ምን ሊበጀው? ከካፊያው ሽሽት ከመስሪያ ቤታችን አቅራቢያ ወደሚገኝ ገብቼበት ወደማላውቅ ካፌ ሰተት አልኩ፡፡

ተደላድዬ ሳልቀመጥ እንዲሁም ሀሳቤን ፈር ሳላሲዝ አንዲት ጸጉሯን ቀለም ያጠጣች፣ ደረቷ ላይ የእሾህ አክሊል ያለበትን የእየሱስን ምስል ያተመች ሴት ልትታዘዘኝ ፊቴ ተዘባና ቆመች፡፡ ማንም ከዚህ በፊት እንዲያ ባለ ዝብናኔ አስተናግዶኝ አያውቅም፡፡ በዝብናኔዋ አልተቀየምኳትም ይልቅስ አዲስ ሀሳብ አጋባችብኝ እንጂ፡፡ ‹ወተት አልኩ› ብዙ ሳላለፋት፡፡ ካፌ ገብቼ ከወተት ውጪ የምጠጣው ነገር የለም፡፡ አንዳንድ ወዳጆቼ ሲቀልዱብኝ የእናት ጡት ስላልጠገበ ያንን እየተካ ነው ይሉኛል፡፡ እኔ ምን ገዶኝ..አንድ ለመጨረስ በሚሳቀቁ ቄንጠኛ ወዳጆቼ ፊት ሁለት..ሶስቱን ደርግሜ እመለሳለው፡፡ ከእንስሳ የላም አፍቃሪ ነኝ፡፡ ከሰው ደግሞ የራሴ፡፡ ያቺን የመስሪያ ቤታችን ቆንጆ ዘናጭ ሴት ሁለተኛ ላደርጋት ከራሴ ጋር ምክክር ላይ ነኝ።

ከቡሀቃ መለስ ባለ አንዳች በሚያክል ጥንታዊ ብርጭቆ ትኩስ ወተት መጣልኝ፡፡ በዛ ዘመነኛ ቤት ውስጥ ያን ብርጭቆ መኖሩ ዙሪያ ገባዬን እንድቃኝ አደረገኝ። ቤቱ ባህላዊ ቤት እንደሆነ በተቀመጥኩበት ወንበርና፣ ግድግዳው ላይ በተሰቀሉ አንዳንድ ባህላዊ ጌጦች አረጋገጥኩ፡፡ ትልቁ ብርጭቆ ውስጥ ይመጥነዋል ብዬ ያሰብኩትን ስኳር በስሌት ጨምሮ ወደአፌ አስጠጋሁት፡፡ በአንዲት ቀብራራ ሴት የመጣ ነጭ ወተት..ወደ ሆዴ ሲሰርግ በተለየ እርካታ ነበር። አጠጣጤን እየታዘበች ይሆን እንጃ ላጋሳ ቀና ባልኩበት አስተናጋጇን አይኗን አነጣጥራብኝ አገኘኋት፡፡ ደረቷ ግድም በእሾህ አክሊል እየሱስን ወደ አንድ ጎን አዘንብሎ አየሁት፡፡ ካልጠፋ ቦታ የዓለምን ንጉስ እዛ ቦታ ማኖሯ ፈጣሪ በንፍር ውሀ ሊጠብሰን እያኮበኮበ እንደሆነ እንዲሰማኝ አደረገኝ። በሴት ርቃን ላይ፣ ለዛውም በጡት ሰፈር እየሱስን ተስሎ ሳየው ስምንተኛው ሺ መድረሱን አወኩ፡፡ ‹ከፍቅሯ ነው ከድፍረቷ ያን ማድረጓ? ስል ጥያቄ መጣብኝ፡፡

ከቀይ ዳማ ሸሸት ከጠይምነት መለስ ያለ መሀል ላይ ያለ ስም የሌለው መልክ አላት፡፡ ከውበቷ ሁሉ ቶሎ አይን ውስጥ የሚገባው ጡቷና ቆፍጣናነቷ ነው፡፡ የሀበሻ ቀሚስ ለብሳ ቢሆን ፊቴ የቆመችውና የምትታየኝ እቴጌ ጣይቱ በወጣትነቷ ትሆን ነበር፡፡ ጡቶቿ ለእይታ እንዲመቹ ሆነው መልኩን በሚያሳብቅ ጥቁር ጡት ማሳዣ ተጠፍረዋል። ደረቷን ለሁለት ገምሰው ተነፋፍተው እና አጮልቀው። ከአንዴ ልቀው ለዘላለም እንዲታወሱ በሀጢዐተኛ ሴት መላ ተዘባነዋል፡፡ አማረችኝ፡፡ ከወተቱ ጋር እሷን የሚያሰኝ መስተፋቅር ሰታኝ ይሆን? አይቻት የማላውቃትን ሴት በአንድ ጊዜ መከጀሌ ስል አሰብኩ። ከሴት ውበት መድከሚያዬ ጡት ነው፡፡ ትልቅ ጡት ያላት ሴት ሰፊ አለሜ ናት፡፡ ሴት ጡት ከሌላት ሴት አትመስለኝም፡፡ አብሬአት ተጋድሜ እንኳን አምሮቴን ለማውጣት የማውቃቸውን ትልቅ ጡት ያላቸውን ሴቶች በሀሳቤ አምጥቼ ነው የምረካው፡፡ የዚህ ዓለም እድለኛዋ ሴት ትልቅ ጡት ከትልቅ መቀመጫና ከትሁት ልብ ጋር ያላት ናት የሚል ምልከታ አለኝ፡፡

ሂሳብ ልከፍላት በዛውም በደንብ ልረዳት በምልክት ጠራኋትና መጣች፡፡ ስትራመድ ለማንም ዝቅ እንዳትይ ተብላ ያደገች ነው የምትመስለው፡፡ ቆፍጣናነቷ ተጋብቶብኝ ትህትናዬን ነጥቆ ‹ሂሳብ ስንት ነው? ስል ተጀነንኩባት፡፡ ለሰላሳ ብር ወተት ያን ያክል መጀነን.. ‹ተከፍሏል› አለችኝ፡፡ በማውቀው ቆፍጣናነቷ፡፡

ምን እንዳስደነገጠኝ እንጃ ተከፍሎልኝ የማያውቅ ይመስል ድንግጥ አልኩ፡፡ ማን አባቱ ነው የከፈለልኝ በሚመስል አካኋን ፊቷ ላይ አንጃበብኩ፡፡ የጠጣሁበትን ባላገር ብርጭቆ አንስታ፣ ያዝረከረኩትን ወተት ጠረጴዛውን አባብሳ ከፊቴ እብስ አለች፡፡ ቁፍጣኔዋ ራሷ የከፈለችልኝ እንደሆነ እንዳስብ አደረገኝ፡፡ ከአይኔ ከመሰወሯ በፊት ‹ማነው የከፈለው? ስል ዘለግ ያለ ድምጼን ወረወርኩላት። ትታኝ ትሄዳለች ብዬ ስፈራ ጣቷን ከገባሁ ጀምሮ ወዳላየሁት ቦታ ቀስራ ወደ ከፈለችልኝ ሴት ጠቆመችኝ፡፡ እኔና ሀሳቤ፣ እኔና ምኞቴ.. ዘላለሜ ሳይቀር እዛ ቦታ የጨው ሀውልት ሆነን የበደንን ይመስለኛል ካልሆነ ለምን መራመድ አቃተኝ? በዛ ቦታ ለክፍለ ዘመናት የቆምኩ ይመስለኛል፡፡ ብርሀናማዋን የመስሪያቤታችንን ሴት እያስተዋልኩ። ፊቷን ለግድግዳው ሰጥታ፣ እጇን ደረቷ ላይ አጣጥፋ በሆነ ሀሳብ ተወስዳለች። የማውቀው ፈገግታዋ የለም። ግድግዳውን እያናገረች መሰለኝ፡፡ ሊስማት ከንፈሯ ስር በደረሰው ግድግዳ ቀናሁ። ግድግዳውን ባረገኝ አልኩ፡፡

አመሰግናለው ሳልላት ወጣሁ..

የያዝኩትን መጽሀፍ ረስቼ ኖሮ በነጋታው ቢሮ አምጥታ ስትሰጠኝ ከፈጣሪ ስጦታ የተበረከተልኝ ነበር የመሰለኝ፡፡

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን መጋቢት 6/2016 ዓ.ም

Recommended For You