የፓን አፍሪካን ማሳያ ከሆኑ ስፖርታዊ ውድድሮች መካከል አንዱና ዋነኛው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች እአአ በ1965 ለመጀመሪያ ጊዜ በኮንጎ አዘጋጅነት ነበር የተካሄደው። በኦሊምፒክ መርህና ስርዓት በየአራት ዓመቱ የሚከናወነው ይህ ውድድር፤ በአፍሪካ ሕብረት፣ በብሄራዊ የኦሊምፒክ ኮሚቴዎች እንዲሁም በአፍሪካ የስፖርት ኮንፌዴሬሽኖች በጋራ ይመራል። ከጊዜ ወደጊዜ እያደገና እየሰፋ በመምጣትም ለኦሊምፒክ እንደማጣሪያ ውድድር እስከመጥቀም የደረሰ ሚናም አለው።
ወራት ብቻ የቀሩትን የፓሪስ 2024 ኦሊምፒክን ተከትሎም የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች በጋና አዘጋጅነት ለ13ኛ ጊዜ መካሄድ ከጀመረ ቀናቶች ተቆጥረዋል። ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሃገር ውድድሩን በዋና ከተማዋ አክራ እና ሌሎች ከተሞቿ ኩማሲ እና ኬፕ ኮስት ያሰናዳች ሲሆን፤ ለዝግጅቱም 145 ሚሊየን ዶላር ወጪ በማድረግ የኦሊምፒክ ደረጃውን የጠበቀ ሁለገብ የስፖርት ማዘውተሪያዎችን መገንባቷን አስታውቃለች። ለሶስት ሳምንታት በሚቆየው በዚህ ውድድር ላይም ከ54 የአፍሪካ ሃገራት የተወጣጡና በሺዎች የሚቆጠሩ አትሌቶች በ30 ዓይነት ስፖርታዊ ውድድሮች ለአሸናፊነት የሚፋለሙ ይሆናል። ይህም እአአ በ2019 ከተካሄደው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች በአራት ብልጫ ያለው ነው።
ከጥቂት ቀናት በፊት ውድድሩ በተጀመረበት ዕለት በተከናወነው የጠረዼዛ ቴኒስ ስፖርት ግብጽ በሁለቱም ጾታዎች ቀዳሚውን ሜዳሊያ በማስመዝገብ በደረጃ ሰንጠረዡ ቁንጮ የተቀመጠች ሃገር ልትሆን ትችላለች። በአንጻሩ በነጠላ እና በቡድን በተካሄደው በዚህ ውድድር ላይ ተሳታፊ የነበረው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አልተሳካለትም። ከፍተኛ ፉክክር ሲያካሂድ የቆየው የሴቶች ብሄራዊ ቡድኑ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ለማለፍ በሚያስችለው ጨዋታ በናይጄሪያ አቻው 3 ለ0 ተሸንፏል። የወንዶች ቡድኑ ደግሞ በመጀመሪያው ዙር ጨዋታ ከምድቡ ማለፍ አልቻለም።
በእግር ኳስ ስፖርት 8 ቡድኖችን በሚያፋልመው የመላ አፍሪካ እግር ኳስ ውድድር ኢትዮጵያ በሴቶች ብሄራዊ ቡድኗ እንደምትወከል ይታወቃል። ቡድኑ ከ20 ዓመት በታች ዓለም ዋንጫ ማጣሪያ እስከመጨረሻው ምዕራፍ ቢደርስም ሳይሳካለት መቅረቱ የሚታወስ ነው። ይህንን ተከትሎም ካፍ በመላ አፍሪካ ጨዋታዎች ላይ እንዲሳተፉ ካደረጋቸው ቡድኖች መካከል አንዱ ሲሆን፤ በሁለት ምድብ ተከፍሎ በሚካሄደው ጨዋታ ተሳታፊ ነው።
የኢትዮጵያ ወጣት ብሄራዊ ቡድኑም በምድብ አንድ ከአስተናጋጇ ጋና፣ ኡጋንዳ እና ታንዛኒያ ጋር ተደልድሎ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ልምምዱን ሲያከናውን መቆየቱ ይታወሳል። የመጀመሪያ ጨዋታውን በኬፕኮስት ስታዲየም ከአዘጋጇ ሃገር ጋና ጋር በማድረግ አንድ ለምንም በሆነ ውጤት መሸነፉ የሚታወስ ነው። በአሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ የሚመራው ብሔራዊ ቡድኑ ሁለተኛ ጨዋታውን ዛሬ የሚያደርግ ሲሆን፤ የኡጋንዳ አቻውን ይገጥማል። ቡድኑ ከሁለት ቀናት በኋላ ደግሞ ሶስተኛ የምድብ ጨዋታውን ከታንዛኒያ ጋር በኤልሚና ስታዲየም ያከናውናል።
ኢትዮጵያ በመላ አፍሪካ ጨዋታዎች የተካፈለችበት ሌላኛው ውድድር የውሃ ዋና ሲሆን፤ በሴቶች የ100 ሜትር የደረት ቀዘፋ ለግማሽ ፍጻሜ አልፋለች። በሁለቱም ጾታ 50 ሜትር የቢራ ቢሮ ቀዘፋ እና 100 ሜትር የደረት ቀዘፋ ውድድሮች የተደረጉ ቢሆንም፤ በውድድሩ ሃገሯን የወከለችው ዋናተኛ ብርሃን ደመቀ በማለፍ በብቸኝነት ፍጻሜው ላይ እንደምትካፈልም ታውቋል።
በመላ አፍሪካ ጨዋታዎች ውድድር ከሚካሄድባቸው ስፖርቶች መካከል 7 የሚሆኑት የኦሊምፒክ ስፖርቶች ናቸው። ከእነዚህ መካከልም ኢትዮጵያ በአምስቱ ስፖርቶች (አትሌቲክስ፣ ብስክሌት፣ ውሃ ዋና፣ ጠረዼዛ እና ሜዳ ቴኒስ ስፖርቶች ውጤታማ ለመሆን አልማለች።
በአጠቃላይ 149 አትሌቶችን የሚያቅፈው ቡድኑ በአትሌቲክስ፣ እግር ኳስ፣ ቦክስ፣ ብስክሌት፣ ወርልድ ቴኳንዶ፣ ሜዳ ቴኒስ፣ ጠረዼዛ ቴኒስ፣ ውሃ ዋና እና ቅርጫት ኳስ ስፖርቶች ትፎካከራለች።
በዚህ የውድድር መድረክ በርካታ ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ ቀዳሚ የሆነችው ግብጽ ስትሆን፤ 1ሺ635 ሜዳሊያዎችን አስቆጥራለች። 1ሺ326 እና 1ሺ54 ሜዳሊያዎች ያሏቸው ናይጄሪያ እና ደቡብ አፍሪካ ደግሞ ሁለተኛ እና ሶስተኛ በመሆን ሰሜን አፍሪካዊቷን ሃገር ይከተላሉ። 174 ሜዳሊያዎች ያሏት ኢትዮጵያ ደግሞ በደረጃ ሰንጠረዡ 7ኛ ደረጃ ላይ ስትገኝ፤ ከእነዚህ ውስጥ 45ቱ የወርቅ፣ 54ቱ የብር እንዲሁም 75ቱ የነሃስ ሜዳሊያዎቹ ናቸው።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን መጋቢት 3 ቀን 2016 ዓ.ም