የሴቶችን መብትና እኩልነት ማስፈን የመንግሥት ዐቢይ የልማት አቅጣጫ ሆኖ ይቀጥላል

አዲስ አበባ:- የሴቶችን መብትና እኩልነት በማስፈን ሁለንተናዊ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ የመንግሥት ዐቢይ የልማት አቅጣጫ ሆኖ የሚቀጥል እና የተሰጠው ትኩረትም ሴቶች በመንግሥት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ እንዲቀመጡ ማስቻሉ ተጠቆመ፡፡

“ሴቶችን እናብቃ፣ ልማትና ሠላምን እናረጋግጥ” በሚል መሪ ሃሳብ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከበረው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በዓድዋ ድል መታሰቢያ ትናንት ተከብሯል፡፡ በወቅቱ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባስተላለፉት መልዕክት መንግሥት የሴቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን እንዲሰፍን በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቁመዋል።

መንግሥት የሴቶችን መብትና የፆታ እኩልነት በማረጋገጥ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የልማት ተሳትፎዎች ላይ ያላቸውን ድርሻ ለማሳደግ ጥረት ማድረጉንም አመልክተዋል፡፡ የሴቶችን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትና ተሳትፎ ለማስፈን የሚያስችሉ እቅዶች ተቀርጸው ተግባራዊ መደረጋቸውንና ተግባሩ ስኬታማ መሆን መቻሉንም ገልጸዋል።

ሆኖም አሁንም ሴቶች በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና በፖለቲካ ጉዳዮች የሚገባቸውን ያህል እኩል ተጠቃሚና ተሳታፊ መሆን እንዳልቻሉና ሴቶችን ማብቃትና ተሳታፊነታቸውንና ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸዋል። ክፍተቱን ለማጥበብም እድሉን አግኝተን ሀገር እየመራን ካለን ሴት የፖለቲካ አመራሮች ይጠበቃልም ብለዋል፡፡ የዘንድሮው የሴቶች ቀን በዓድዋ ድል መታሰቢያ መከበሩ የተለየ እንደሚያደርገው፣ የዓድዋ ድልም ለሴቶች የተለየ ትርጉም እንዳለውም ተናግረዋል።

በአስተዋፅዖዋቸው ልክ ባይነገርም ለዓድዋ ድል መገኘት በርካታ ሴቶች ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማበርከታቸውን የሴቶች ጥበብ እና ብልሀተኛ መሪነት የታየበት አንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ ሴቶች የፆታ እኩልነት ተረጋግጦላቸው ካለባቸው ድርብርብ ተጽዕኖ እንዲላቀቁ፣ በኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መስኮች እኩል ተሳታፊ እና ተጠቃሚ እንዲሆኑ በርካታ ትግል ሲደረግ መቆየቱን በመጠቆምም፤ በትግል የተገኘውን ውጤት መዘከር እንደሚገባም አንስተዋል፡፡

በወሲብ ንግድ ላይ የተሠማሩ ሴቶች ሠልጥነው ሥራ የሚያገኙበት “የሴቶች ተሐድሶና ልህቀት ማዕከል” በቀጣዩ ሳምንት ተመርቆ ሥራ እንደሚጀምርም አብስረዋል። የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ በሁለት ወራት በተከናወነ ንቅናቄ ተሳታፊነታቸውንና ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጡ ተግባራት መከናወናቸውንም አመልክተዋል። የሴቶችን የነቃ ተሳትፎ ማስፈን፣ ተገቢ ትኩረት እንዲያገኙ እና ለተጎዱ ድጋፍ የማድረግ ሥራ በልዩ ትኩረት እየተተገበረ እንደሚቀጥል፣ ሴቶች ላይ ጥቃት እና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እንዳይደርሱ መከላከል የሁሉም አካላት ትብብርን እንደሚጠይቅም ተናግረዋል፡፡

መንግሥት በሀገሪቱ 52 በመቶ የሚሆነውን የሕዝብ ቁጥር የሚሸፍኑትን ሴቶች መብት እና ጥቅም ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንደሚገኙና የተሰጠው ትኩረት ሴቶች በመንግሥት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ እንዲያገለግሉ ማስቻሉንም ተናግረዋል፡፡ የሴቶች የኢኮኖሚ አቅም እንዲጎለብት፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ተሳትፏቸው እንዲያድግ እንዲሁም ፆታ ተኮር ጥቃቶች እና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እንዲቆሙ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር የሴቶችና ሕጻናት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አለሚቱ ኡሞድ ሴቶችን አሳታፊ ባደረጉ፣ አመለካከቶችን በሚለውጡ፣ ተሳታፊና ተጠቃሚነታቸውንም በሚያረጋግጡ ተግባራት በዓሉ እየተከበረ መሆኑን ተናግረዋል። የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፎችን ተግባራዊ በማድረግም የሴቶችን ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት ያሰፈኑ በርካታ ስኬቶች መገኘታቸውንም ጠቁመዋል።

ዘላለም ግዛው

አዲስ ዘመን የካቲት 30 / 2016 ዓ.ም

Recommended For You