የክሬን ኦፕሬት ስራ እጅግ ጥንቃቄን የሚፈለግና የኦፕሬተሩ ሃላፊነቱን በአግባቡ ለመወጣት አብዛኛውን የስሜት ህዋሳቶቹን በአንድ ጊዜ በአግባቡ መጠቀም መቻል አለበት። ትንሽ ስህተት ውድ የሆነውን የሰው ልጅ ህይወት ያስከፍላል። ከህይወት በተጨማሪም በርካታ ወጪ የወጣበትን ንብረት እስከማውደም የሚያደርስ ጉዳትንም ያስከትላል። ታዲያ ይህን ግዙፍ ተሽከርካሪ የማንቀሳቀስ ስራ ለወንዶች ብቻ የተፈቀደ እስኪመስል ድረስ እምብዛም ሴቶች ሲደፍሩት አይስተዋልም። የዛሬዋ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ የሴቶች ቀን ልዩ እትም እንግዳችንም ሴትነት ይህን ግዙፍ ተሽከረካሪ ከማገላበጥ ያላገዳት ሴት የታወር ክሬን ኦፕሬተር ናት ።
ወይዘሮ ማርታ መሰለ ትባላለች። በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የታወር ክሬን ኦፕሬተር ናት። የተወለደችው ሰኔ 13 ቀን 1964 ዓ.ም ቀድሞ ባሌ በሚባለው በአሁኑ የአርሲ ዞን አዳባ ውስጥ ነው። ወላጆቿ ምንም ሳያጓድሉባት በደንብ እንዳሳደጓት ትናገራለች።
የመንግሥት ሠራተኛ የነበሩት አባቷ፤ ብዙ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት በአዲስ አበባ ነበር። እንዲያም ሆኖ ለስፖርትም ሆነ ለኪነጥበብ ክበብ ተሳትፎ የሚያስፈልጓትን ነገሮች ከማሟላት ወደ ኋላ ብለው አያውቁም። ትምህርት ላይ አማካይ ተማሪ እንደነበረች ትናገራለች ። ከቀለም ትምህርቷ ጎን ለጎን ቮሊቦል መጫወትና በወጣት የኪነጥበብ ክበብ ውስጥ በተወዛዋዥነት ተሳትፋለች።
“ሰዎች ክሬን ላይ በመሥራቴና ከመሬት 70 ሜ. ከፍታ ላይ ወጥቼ ስሰራ፣ እንዴት እንደማያዞረኝ ተደንቀው ሲያወሩ ስሰማ ደስ ይለኛል። ከቤተሰቤና ከሥራ ባልደረቦቼ እንዲሁም ወደ ክሬን ሙያ እንድገባ እድሉን ካመቻቸልኝ የመጀመርያ አለቃዬ ግሩም ድጋፍ በማግኘቴ እድለኛ ነኝ።” ትላለች
አባቷም ልጆቻቸውን እንዳይፈሩ እና ደፋር እንዲሆኑ እያስተማሩ ነበር ያሳደጓቸው። ማርታ የስምንተኛ ክፍል ትምህርቷን እንዳጠናቀቀች ነበር ወላጅ አባቷን በሞት የጣችው። ክፉኛ በማዘኗም ራሷን አረጋግታ ወደ ትምህርት ቤት ለመመለስ አልቻለችም።
ትምህርቷን አቋርጣ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ስራ የገባችበትን አጋጣሚ እንደዚ ታስታውሳለች “ትምህርቴን ትቼ ሥራ ለመፈለግ ወሰንኩ። ክፋቱ ግን የሚቀጥረኝ አጣሁ። ገና የ15 ዓመት ታዳጊ ስለነበርኩና የሥራ ልምድ ወረቀት ስለሌለኝ በብዙ ተንገላታሁ። በመጨረሻ ግን መልካዋከና የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግንባታ መስክ ውስጥ ለወጣት የኪነጥበብ አባላት የሥራ እድል ይሰጡ ስለነበር ለመቀጠር ቻልኩኝ።” ትላለች።
ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀጠረችበት ሥራ የፕሮጀክቱን ግምጃ ቤት መቆጣጠር ነበር። ውስጧ በነበረው መስክ ላይ የመስራት ፍላጎት ቢሮዋ ቁጭ ብላ መስኩ ላይ የሚከናወነውን ሥራ ስትመለከት ነበር የምትውለው። ፕሮጀክቱ ላይ የሚሠሩት የውጭ ሰዎች አነስተኛ ክሬኖች (እቃዎችን ከቦታ ወደ ቦታ የሚያንቀሳቅሱ ማሽኖች) አስመጥተው ሴቶችን ማሰልጠን እንደሚፈልጉ ስትሰማ እድሉን ለመጠቀም ጥያቄ አቀረበች። በእድሉ ለመጠቀም በጣም ጓጉታ ስለነበር በሁሉም ነገር ሲደግፋት የነበረው አለቃዋ የጓጓችለትን ሥልጠና እንድታገኝ ረዳት።
ከሥልጠናውም በኋላ፣ የተሰጠውን የንድፈ ሃሳብና የተግባር ፈተና አልፋ፣ ወዲያውኑ በክሬን ባለሙያነት መሥራት ጀመረች። ሥልጠናውን ከወሰዱት ስምንት ሴቶች መካከል በሥራው የገፉበት ሁለት ብቻ እንደነበሩ ትናገራለች። ወይዘሮ ማርታ በከባድ ማሽን ላይ መሥራቷን ስትቀጥል በጣም የምታደንቃት ሌላኛዋ አብራት ስትሰለጥን የነበረችው ደግሞ በካቶ ክሬኖች እና በመሠረት ቁፋሮ ማሽን ስራ ላይ እንደገፋችበት ትናገራለች።
የ17 አመት ታዳጊ እያለች የመልካዋካና ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ፣ ወደ አዲስ አበባ መጥታ ያቋረጠችውን የቀለም ትምህርቷን ለማጠናቀቅ ሽመልስ ሃብቴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገባች። በመቀጠልም በኢትዮጵያ መንገድ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት የሞጆ ጣቢያ ተቀጥራ በረዳት አውቶ ኤሌክትሪሽያንነት ስራዋን ጀመረች። ቀደም ሲል በክሬን ላይ መሥራቷን የሰሙ የሥራ ባልደረቦቿ፣ ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ለክሬን ባለሙያዎች ላወጣው ክፍት የሥራ ማስታወቂያ እንድታመለክት አበረታተዋት፣ የሥራ ልምዷን ይዛ ወደ ሳሊኒ ቢሮ አመራች።
“መጀመሪያ ላይ ሴት እንዴት ክሬን ላይ ትሰራለች የሚል ጥርጣሬ ገብቷቸው ነበር። የሳሊኒ ማሽን በፊት ከሰራሁበት በእጅጉ የሚበልጥና ትልቅ ፕሮጀክት ቢሆንም መሠረታዊ የኤሌክትሪክ ሲስተሙ ግን ተመሳሳይ ነበር።” ሥራውን ለመቀጠር ፈተና መውሰድ ነበረባትና ፈተናውን እንዳለፈች ወዲያው በግልገል ጊቤ አንድ ፕሮጀክት ላይ ሥራ እንድትጀምር ተነገራት።
በወቅቱ ፕሮጀክቱ የሰው ኃይል እጥረት ስለነበረበት የጤና ምርመራ ውጤት እስክታመጣ እንኳን አልጠበቁም ነበር። ለሦስት ሳምንት ያህል የቅጥር ውል ሳትፈርም ስለቆየች ከደሞዟ ጋር እንደሚያስፈርሟት ጠብቃ ነበር። ሆኖም ዝም ብለዋት ቆዩ። ጉዳዩ ያሳሰባት ወይዘሮ ማርታም “ቢቸግረኝ እኔው ራሴ ጠየቅኋቸው”ትላለች።
ቆይቶ ግን የአስተዳደር ኃላፊው ሴትን በክሬን ባለሙያነት አምኖ ለመቅጠር ፈቃደኛ እንዳልሆነ ነገራት። “የሰራሁበትን ክፈሉኝና እለቅላችኋለሁ” ብላ ልትወጣ ስታስብም። ሥራዋን ያዩና ኃላፊነቷን በአግባቡ እንደምትወጣ የተማመኑባት የቅርብ አለቆቿ እንድትለቅ ሳይፈቅዱ ቆዩ። የቅርብ አለቆቿም ከአስተዳደር ኃላፊው ጋር “ትቀጠር አትቀጠር” በሚል ሲከራከሩ ቆዩ።
በመጨረሻ የአስተዳደር ኃላፊው በስራ ሰአት እሷ ሳትመለከታቸው ስትሰራ በዓይናቸው በመመልከታቸው እንድትቀጠር ተስማሙ። ‹‹ ሥራው ከባድ እንደሆነ መካድ አልችልም ›› ትላለች ማርታ። ሆኖም የወንዶቹን ያህል የመሥራት ብቃት እንዳላት ለማሳየት በትጋት ተወጥታዋለች።
የሳሊኒ ሥራ ሲጠናቀቅ ሳሊኒዎች ክሬኑን ለጀርመኑ ዙብሊን ኮንትራክተሮች ለማስተላለፍ ወሰኑ። በዚህም እሷም ከክሬኑ ጋር እላካለሁ የሚል ተስፋ አድሮባት ነበር። ሆኖም ከቅርብ አለቃዋ ጋር ከሥራ ውጭ በሆነ ጉዳይ ተጋጭተው ስለቆዩ፣ እሷን አባርሮ እሷ ያሰለጠነችውን ረዳቷን ለመላክ መወሰኑን ሰማች። ይህን ፍትሃዊ ያልሆነ ድርጊት በዝምታ ለመቀበል አላስቻላትም። እናም በቀጥታ መብራት ኃይል ቢሮ ሄዳ የደረሰባትን በደል ተናገረች። በደረሰባት ነገር በጣም አዘኑ። በመጨረሻም ከክሬኑ ጋር ወደ ዙብሊን ኮንትራክተርስ እንድትላክ ተወሰነ። በዙብሊን ኮንትራክተርስ ለተወሰነ ጊዜ ከሰራች በኋላ፣ የጤና እክል የነበረባትን ልጇን በቤት ውስጥ ለመንከባከብ ወደ አዲስ አበባ ተመለሰች።
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወንድምና እህቶቿ ወደ ሥራ እንድትመለስ ገፋፏት። በአጋጣሚም ራማ ኮንስትራከሽን ካዛንቺስ አካባቢ ክሬን እየተከለ ስለነበር፣ እዚያ ማመልከቻ አስገባች። የራማ ኮንስትራክሽን ባለቤትን ጨምሮ አመራሩ ሴቶችን ለመቅጠር ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበራቸው በደስታ ለፈተና አስቀመጧት። ፈተናውን አልፋም ወዲያው ሥራ ጀመረች። የሚገርመው ግን ከዚያ በፊት ለውጭ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ለማመልከት ሄዳ ኢትዮጵያዊው የሠራተኛ ቅጥር ኃላፊ፤ ማመልከቻዋን እንኳን ለመቀበል ፈቃደኛ እንዳልነበር ትናገራለች።
‹‹ወጣት ሴቶች ለወንዶች ብቻ የተፈጠረ ሥራ እንደሌለ በማወቅ የፈለጉትን ሁሉ መስራት እንደሚችሉ ማሳሰብ እፈልጋለሁ ። ሥራው ምንም ይሁን ምን ተግተው እስከሰሩ ድረስ ስኬታማ የማይሆኑበት አንዳችም ምክንያት የለም። ›› ስትል መልእክቷን ታስተላልፋለች።
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን የካቲት 29 /2016 ዓ.ም