ሴቶች ይችላሉ ብዬ መነሳት አልፈልግም ፤ ምክንያቱም ከትላንት እስከ ዛሬ በተለያዩ መስኮች ችለው፤ ችለው ብቻም አይደለም በልጠው አሳይተውናል። ሴቶች እድል ያላገኙባቸው የተለያዩ ማህበራዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ቢኖሩም፤ ዛሬም ድረስ ግን በተለይም በጥረታቸው ታግለው የወጡ ሴቶች አለምን ጉድ የሚያሰኙ ተግባራትን እየፈጸሙ አይተናል ።
ለወንዶች ብቻ ተለይተው ሴቷ አትችልም ተብለው የኖሩ ስራዎችን በጥረታቸውና በብቃታቸው ተወጥተውት የሴት ተምሳሌት ጀግና የተባሉም ብዙ ናቸው። እኛ እንደ ባህልም ይሁን አመለካከት ሴቶችን በውስን ነገሮች ላይ ገድበን አየናቸው እንጂ፤ ከጥንት ጀምሮ በፖለቲካዊ አመራር ብቃታቸው በሃገር መሪነታቸው ከወንዶች የበለጠ ውሳኔ ሲያሳልፉ የነበሩ እንደ ጣይቱ ብጡል አይነት ጀግና ሴት ያለን ህዝቦች ነን።
ከዛም በኋላ ቢሆን በተለያዩ አጋጣሚዎች ብቅ ያሉ ሴቶች በፖለቲካው፣ በማህበራዊው፣ በኢኮኖሚውና በዲፕሎማሲያዊው ዘርፍ ግንባር ቀደም ሆነው በመውጣት ለሃገራቸው ቀላል የማይባል አበርክቶ በማትረፍ ታሪክ ሲዘክራቸው የሚኖሩ ሴቶቻችንም ቁጥር ብዙ ነው።
ይህ ሁሉ እንዳለ ሆኖ ግን የባሎቻቸው የልጆቻቸው ደጀን በመሆን የእነሱን ሁለንተናዊ ድጋፍ በማድረግ ስኬታማ እንዲሆኑ ሌት ተቀን የሚለፉ ግን ደግሞ ልፋታቸው ያልተነገረላቸው በየቤቱ ያሉ አያሌ ጀግና ሴቶች ያለን ነን።ባል በተሰማራበት መስክ ውጤታማ እንዲሆን ሰርቶ ቤተሰቡን አገሩን ይጠቅም ዘንድ የልጆቿን ሙሉ ሀላፊነት ወስደው ደፋ ቀና የሚሉ እናቶች በተቃራኒው ባላቸውን በተለያየ ምክንያት አጥተው፤ ልጆቻቸውን ዝቅ ብለው ወርደው ሰርተው የሰው ፊት ገርፏቸው ዶክተርና ኢንጂነር ያደረጉ ለሃገራቸው መልካም ዜጋን ያፈሩ ሴቶችም ቤት ይቁጠራቸው።
እንደ አለመታደል ሆኖ ጀግኖቻችንን በተለይም ሴቶችን የማክበርና የማወደስ አቅማችን ውስን ሆኖ ነው እንጂ፤ ሲነገርላቸው ውሎ ሲነገርላቸው ቢያድር ከስራቸው አንጻር የሚያንስባቸው ብዙ ሴቶች አሉ።ህብረተሰቡ ውስጥ ያለው ጎታች አስተሳሰብ ከህልማቸው ያላስቀራቸው በራሳቸው ጥረትና ስራ ዛሬ ላይ ከፍ ብለው ዓለም ወዶ ሳይሆን ተገዶ ሊመሰክርላቸው የቻለ ሴቶችንም ማውሳት ይቻላል ።
በየዓመቱ የሚከበረው ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀንም (ማርች 8) ዋናው አላማው በተለይም ጓዳ ተደብቀው ያሉ ሴቶችን ማውጣት፤ አደባባይ የወጡትንም ለበለጠ ስኬት ማበረታታት እንዴት አድርጌ ይሆንልኛል ብለው ወደኋላ የሚሉትንም ተምሳሌት የሆኑትን እያሳዩ ማውጣት ነው። እኛም የዘንድሮውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በማስመልከት በተለይም ለሴቶች አይደፈሬ የሆነውን እስከ አሁንም በብቸኝነት በአንዲት ሴት ብቻ እየተሰራ ያለውን የባቡር አሽከርካሪነት ሙያ ልንቃኝ ወደናል ።
ወይዘሮ አንቀጸብርሃን ግርማ ትባላለች።አንቀጸ በኢትዮ ጅቡቲ የምድር ባቡር የባቡር አሽከርካሪ ናት። የትውልድ ቦታዋ አርሲ ኮፈሌ በሚባል ቦታ ሲሆን ያደገችው ደግሞ አሰላ ከተማ ነው።የአስተማሪ ልጅ የሆነችው አንቀጸ ለቤተሰቦቿ ሶስተኛ ልጅ ናት።የመጀመሪያ ደረጃና ሁለተኛ ደረጃ እንዲሁም የመሰናዶ ትምህርቷን ባደገችበት አሰላ ከተማ ስለመማሯም ትናገራለች።
“……..በትምህርቴ በጣም ጎበዝ የምባል ባልሆንም ለራሴ ግን የማንስ አልነበርኩም።ቤተሰቦቼ እናቴና አባቴ ሁለቱም መምህራን ስለነበሩ ለትምህርት ትኩረት ይሰጣሉ ፤ እኛም ትኩረት እንድንሰጥ ያበረታቱን ይደግፉን ነበር። በዚህም ደህና ተማሪ ነበርኩ” በማለት ሁኔታውን ታስታውሳለች።
ወይዘሮ አንቀጸ 12ተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከተፈተነች በኋላ በቀን የትምህርት ክፍለ ጊዜ ገብቶ ለመማር የሚያስችላት ነጥብ ባለማምጣቷ በማታው የትምህርት ክፍለ ጊዜ ለመማር በቀጥታ ያመራችው ወደ አዳማ ዩኒቨርሲቲ ነበር ፤ በዛም የኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ትምህርቷን ለመማር ተመዘገበች ።
“…….በወቅቱ የ12ተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ላይመጣልኝ ይችላል የሚል ግምት አልነበረኝም ፤ የሚገርመው ነገር ከመግቢያ ነጥቡ ያነሰኩት በአንዲት ነጥብ ነበር፤ በወቅቱ በጣም ብናደድም በቀጣይ ምን ማድረግ አለብኝ የሚለውን ግን በደንብ አሰብኩበት። በዚህም ውጤት ስላልመጣልኝ ብዬ ከመናደድ በማለት አዳማ ዩኒቨርሲቲ በማታው ክፍለ ጊዜ ተመዝግቤ የኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ትምህርቴን ቀጠልኩ “ ትላለች።
አንቀጸ እንደዚህ ወስና ትምህርቷን በማታው ክፍለ ጊዜ ትቀጥል እንጂ ትምህርቱን በቀን ፕሮግራም እንደመማር አስደሳች አልሆነላትም።እንደውም የመጀመሪያ አመት ትምህርቷን ለጊዜ ማሳለፊያ ሁሉ የምትማር አድርጋ በመውሰድ ብዙም ትኩረት ሳትሰጠው ማለፏን ትናገራለች።ነገር ግን ዋል አደር እያለች ትምህርቱንም ስታየው እየወደደችው ከዛም የክፍለ ጊዜ ቀንና ማታ መሆን በትምህርቱ ላይ ለወጥ እንደማያመጣ ተግቶ መስራት ከተቻለ በሁሉም ወደስኬት እንደሚወስድ ስለገባት አንደኛ አመት ላይ ላላ አድርጋ የተማረችውን ትምህርት በሁለተኛው አመት አጥብቃ ያዘችው። በዚህም ውጤቷ ሲሻሻል በጣም አስደሳች ሲሆን መመልከቷ ሞራሏን ገነባላት።በጣም ደስም ስላላት እንደውም የቀኑን ክፍለ ጊዜዬን በመቀመጥ ማሳለፍ የለብኝም ሌላ ነገር ደግሞ ላስብ ልማር በማለት ተነሳሳች።
“……..እንዳልኩሽ የማታ መማር ብዙም ምቾት አልሰጠኝም ነበር። የጊዜ ማሳለፊያ እንደሆነ ይሰማኝ ነበር ፤ ነገር ግን በመካከል የሃሳብ ለውጥ አመጣሁ። ለትምህርቴም ከፍ ያለ ትኩረትን መስጠት ጀመርኩ፤ በዚህም ውጤቴ ሲሻሻል አየሁ ይህ ከሆነማ በማለት ያለትምህርት የማሳልፈውን የቀኑን ክፍለ ጊዜ ለምን አልጠቀምበትም ብዬ አዳማ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በመሄድ የኤሌክትሮኒክስ ትምህርት ለመማር ተመዘገብኩ” ትላለች ።
ከሁለተኛ አመት ትምህርቷ በኋላ ሙሉ ትኩረቷን በትምህርቷ ላይ ያደረገችው አንቀጸ፤ ሁለቱ ትምህርቶች ደግሞ እየተመጋገቡላት አንዱ አንዱን እየደገፈላት ውጤቷም ያማረ የሰመረ እየሆነ ሄደ።አንቀጸ በጣም በሞራል ስለምትማር እንዲሁም አንዱ ትምህርት ከአንዱ ተደጋጋፊ በመሆኑ ውጤቷ ላቅ ያለ ነበር።የዲግሪ ትምህረቷን ሳትጨርስ የቴክኒክና ሙያ ትምህትርቱ አለቀና ተመረቀች።ከአንድ አመት በኋላ ደግሞ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን አጠናቃ ተመረቀች።
“……..የመረጥኳቸው ትምህርቶች ተመጋጋቢ መሆናቸው በጣም ጠቅሞኛል፤ የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ደግሞ አብዛኛውን ጽንሰ ሃሳቡን መማር በመሆኑና በቴክኒክና ሙያው ደግሞ ከጽንሰ ሃሳብ ባሻገር ተግባራዊ ልምምድንም ማጠቃለሉ ለውጤታማነቴ በጣም አግዞኛል”ትላለች።
አንቀጸ ኢትዮ ጅቡቲ የምድር ባቡርን የተቀላቀለችው የማታውን የዲግሪ ትምህርቷን ሳታጠናቅቀ በቴክኒክና ሙያ የትምህርት ማስረጃዋ ነበር።” ……ዲግሪውን እየተማርኩ ቴክኒክና ሙያ ትምህርቴን አጠናቅቄ ባለሁበት ወቅት ኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር የስራ ማስታወቂያ አወጣ። እኔም ስራ ስለምፈልግና ረዳት የባቡር ሹፌር የሚለውን ማስታወቂያ አሟላ ስለነበር ስራውን ተመዘገብኩ” ትላለች።
ረዳት ባቡር ሹፌርነት ስራ ተመዘገብኩ እንጂ ከዛ በፊት ባቡር የሚባለውን ነገር እንኳን አላውቀውም ነበር፤ የምትለው አንቀጸ ነገር ግን ፈርቶ ወደኋላ ከማለት ይልቅ ልየውና ከሆነ ይሆናል ካልሆነ ይቀራል ብላ ስለመመዝገቧ ትናገራለች። እንዳሰበችውም አንቀጸ ድርጅቱ የትምህርት ዝግጅቷን በማየት ለፈተና ጠራት ፈተናውን አልፋም ድርጅቱን ተቀላቀለች።
“…….ፈተናውን እንዳለፍኩ ለስድስት ወር ስልጠና አለ ተብሎ፤ ቻይናዎቹ የሚያሽከረክሩት ባቡር ረዳት በመሆን ለመሰልጠን ስሄድ ምድር ባቡር ግቢን ለመጀመሪያ ጊዜም ዓየሁት ፤ በወቅቱም የተሰማኝ ስሜት ከባቡሩ ትልቅነት አንጻር ይከብድ ይሆን ብዬ ብፈራም እሞክረዋለሁ በማለት ራሴን አበረታትቼ ወደስልጠናው ገባሁ” ትላለች።
ስልጠናው ልክ እንደትምህርት ቤት ንድፈ ሃሳብን ከልምምድ ጋር ያጣመረ ነበር። አዳዲስ መጽሃፎች አጋዥ የሆኑ ሞጁሎች ተሰጥተውን ተማርን የምትለው አንቀጸ፤ ይህ መሆኑ ደግሞ ባቡሩን በአግባቡ እንድትረዳው ከማድረጉም በላይ የባቡሩ ኤሌክትሪካልነት ከትምህርቴም ጋር ስለሚሄድ ብዙም የከበደ ነገር አልሆነብኝም በማለት ሁኔታውን ታብራራለች።
ሶስቱን ወር የንድፈ ሃሳብ ትምህርት በክፍል ከሰለጠንን በኋላ በስራ ላይ ልምምድ ለማድረግ ወጣን፤ ጅቡቲም ሄድን ብቻ በጣም አሪፍ ጊዜን በማሳለፍ ስራውን እንደተቀላቀለችውም ታብራራለች። ማስታወቂያው ወጥቶ መጀመሪያ ቅጥር ሲፈጸም ከአንቀጸ ጋር ስድስት ያህል ሴቶች እንደነበሩ በማስታወስ፤ ተጠርተን ስራውን ስንጀምር ግን እኔ ብቻ ነበርኩ የቀረሁት ትላለች። ሌሎቹ ሴቶች በመፍራትም ይሁን ሌሎች ምክንያቶች ብቻ ስራውን እንዳልተቀላቀሉትም ትናገራለች።
አንቀጸና ሌሎች ወንድ ጓደኞቿ ለምድር ባቡር የመጀመሪያ ቅጥሮች ቢሆኑም በቀጣይ ግን ተቋሙ ተከታታይ ማስታወቂያዎች ያወጣ ቢሆንም ሴት አመልካቾችን ግን ማግኘት አለመቻሉን ትናገራለች። ይህ የሆነው ደግሞ ምንልባትም ስራው አገር አቋራጭ በመሆኑ ሴቶች መድፈር አቅቷቸው፤ አልያም የትዳር ጓደኛና የቤተሰብ ማበረታቻ አንሷቸው ሊሆን እንደሚችልም ትገምታለች። ይህም ቢሆን ግን አንቀጸ እዛው እንደራሷ የባቡር ሹፌር ከሆነው የትዳር አጋሯ ጋር በመሆን ከአዲስ አበባ ጅቡቲ ብዙ ማይሎችን አቋርጦ የሚሄደውን ባቡር በብቃት እየዘወረችው ትገኛለች።
“…….ባቡሩ መጠኑ በጣም ትልቅ ነው። የሚጎትተው እቃም በተመሳሳይ ትልቅ ነው፤ በሃገራችን በማህበረሰባችን የተለመደው ደግሞ ትልልቅ ነገሮችን ማድረግ የሚችሉት ወንዶች ብቻ እንደሆኑ ነው፤ ይህ አስተሳሰብ ደግሞ ሴቶቹም ላይ ይንጸባረቃል። ከዚህ አንጻር ስራውን እስከ አሁን መድፈር አልቻሉም” ትላለች።
በመሰረቱ ትላለች አንቀጸ፤ ስራውን እንደጀመርኩ አካባቢ ምንም ዓይነት ሴት በዙሪያዬ ሳጣ የማይሆን ቦታ ላይ የተገኘሁ መስሎኝ ነበር። ነገር ግን ቤተሰቦቼ ችግር የለውም ሞክሪውና ካልቻልሽ ትወጪያለሽ በማለት ከፍተኛ ድጋፍን ያደርጉልኝ ነበር። በእነሱ ብርታት ጀመርኩት ሳየውም የሚያስፈራ አልነበረም እንደውም ደስ የሚል ሆኖ አገኘሁት” ትላለች።
ላለፉት አምስት ዓመታት ባቡርን በብቃት ከአዲስ አበባ ጅቡቲ ከጅቡቲ ደግሞ አዲስ አበባ ስታመላልስ ብዙ አስፈሪ ገጠመኞች ገጥመዋት እንደሚያውቁ የምትናገረው አንቀጸ፤ በተለይም ባቡር ሲበላሽ የመብራት መቆራረጥ ሲያጋጥም አጉል ቦታ ምናልብትም በረሃ ላይ ሁሉ መዋል ማደር ስለሚያጋጥም እሱ ፈታኝ መሆኑን ታብራራለች። እንደጀመሩ አካባቢ መብራት ጠፍቶ እልም ያለ በረሃ ላይ ለአንድ ሳምንት ያህል መቆየቷን ታስታውሳለች። ከዛ ውጪ ግን ቀኑን ሙሉ ወይም ለአንድና ለሁለት ቀን ጫካ ውስጥ መቆየት የተለመደ ነው ትላለች።
ባቡር የሚሄደው ከከተማ ውጪ ነው። ድንበር ተሻግሮ ሰው አገር ስገባም ቋንቋው ምግቡ የተለየ ነው፤ በመንገዱ ላይም ብዙ የሚያጋጥሙ ነገሮች አሉ። አሁን ደግሞ ሰዎችና ከብት ወደባቡር መንገድ እየገቡ ስለሚያስቸግሩ ለአደጋ ላለመጋለጥ በትኩረት መስራትን ይፈልጋል፤ በጠቅላላው ግን ባቡር ለመንዳት መሪውን ስይዝ ጀምሮ ሃሳቤን ሰብስቤ ስራዬ ላይ ትኩረት አድርጌ ነው የምሄደው” ስትል ትናገራለች ። በዚህም እስከ አሁን ድረስ ምንም አይነት አደጋ አጋጥሟት እንደማያውቅም ታብራራለች።
“……ባቡር ከተማን ሳይሆን ገጠሩን ከፍሎ የሚያልፍ ከመሆኑ አንፃር በርካታ የማያቸው ነገሮች አሉ፤ በተለይም ሴት ህጻናት በእረኝነት ትልልቆቹ ደግሞ ከአንዱ ቦታ ወደሌላው ልጆቻቸው ተሸክመው የሚሸጡትን ወይም የሚገዙትን እቃ አዝለው ሲሄዱ አያለሁ፤ ይህ በጣም ልቤን ይነካኛል። ልቤን መንካት ብቻ ሳይሆን እነዚህ ሴቶች እንደ ከተማ ሴቶች እድል ቢያገኙ ቢማሩ ለአገር ምን ሊያበረክቱ ይችላሉ የሚለውንም አስባለሁ። በተጨማሪም ከተማ ውስጥ ያለን ሴቶች ከትዳር አጋሮቻችን ጋር ልጅ በማሳደግም ሆነ ሌሎች ሃላፊነቶቻችንን በመወጣቱ በኩል ምን ማድረግ እንዳለብን እናውቃለን አንረዳዳለን። እነዛም ሴቶች ይህንን እድል ቢያገኙ ብዬ እመኛለሁ።” በማለት በስራው ላይ ስትሆን ስለ ሴቶች የምታስበውንና የሚሰማትን ትናገራለች።
ሴቶች አትችሉም ስንባል ኖረናል ነገር ግን እንደምንችል ልናሳይ የሚገባን ራሳችን ነን፤ አሁን ላይ በመጠኑም ቢሆን የተሻሻለ ነገር ያለ ቢመስለም ግን ደግሞ ሴቶች መስራትም መዋልም ያለባቸው ቢሮ ነው የሚለው ነገር አልተቀረፈ ። ስለዚህ ይህንን ነገር ማሻሻል ወንዶች የሚሰሩትን መስራት እንደምንችል ማሳያት አለብን። ሴቶችም ሴት ወንድ የሚለው ነገር ጾታ መለያ እንጂ የአቅም መለኪያ አለመሆኑን በመረዳት በተለያዩ ዘርፎች መሰማራትና መሞከር ተገቢም አስፈላጊም ነው ትላለች።
በመጨረሻም በሌላ በኩልም ሴቶች ፍላጎቱም አቅሙም ቢኖራቸውም፤ ያንን የሚያወጡበት እድል ካላገኙ ውጤቱ ምንም ነውና ተቋማት በሚያወጧቸው የስራ መስኮች ላይ የሴቶችን ተሳትፎ የእውነት በሆነ መልኩ ማጉላት፣ ማሳየት፣ እድል መፍጠር አለባቸው ስትል ሃሳቧን አጠቃላለች።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን የካቲት 29 /2016 ዓ.ም