‹‹ሴትነት የፆታ መገለጫ እንጂ የአቅምና የብቃት ማሳያ አይደለም››  ዮሐና ረታ የጎልደን ስታርስ ኮሌጅ ባለቤት

የብዙ ውጤታማ ሰዎች የስኬት መነሻ ከወደቁበት ለመነሳት በሚታገሉበት በዚያ ስፍራ እንደሆነ ታምናለች። ገና በለጋ እድሜዋ ያጋጠማትን ወድቆ የመነሳት አጋጣሚ እዚህ ለመድረሷ መሠረት እንደሆናት ትገልፃለች። ከገባችበት የተስፋ መቁረጥ ጎዳና ለመውጣትና ሌላ የሕይወት መስመር በመፈለግ ሙከራ ስታደርግ ነበር ከአዲሱ ሕልሟ ጋር የተገናኘችው። እንግዳችን ዮሐና ረታ ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ከምትገኘው ለምለሟና ውቢቷ ቢሾፍቱ ተወልዳ ማደጓንና ከሃገር ወዳድ ወታደር ቤተሰብ መምጣቷን በኩራት ትናገራለች። አሁን ላላት ስብዕናና ማንነት፣ ከሀገር ወዳዱ አባቷ የወረሰችው እንደሆነም ታስረዳለች። ለሌሎች ራስን መስዋዕት ማድረግን፣ የዓላማ ፅናትና፣ ላመነችበት ነገር እስከ መጨረሻ መታገልንና ድል ላይ መድረስንም ጭምር እንዲሁ።

የማንኛውም ሰው የመጀመሪያ ትምህርት ቤቱ ቤተሰብ፤ የሕይወት ተምሳሌቱ ደግሞ እናትና አባት እንደመሆናቸው መጠን የዚህች ጠንካራ ሴት ስብዕና የተገነባው በወላጆቿ መልካም አስተዳደግ መሆኑን አበክራ ትናገራለች። ‹‹አዎ ትውልድ መቀረፅ የሚጀምረው በቤተሰብ ውስጥ ነው”። ቤተሰብ ልጆቹን በፆታ ሳይለይ ማሳደግ አለበት። በተለይ እናት ደግሞ ለሴት ልጆቿ የመጀመሪያ የሕይወት ተምሳሌት ነችና በቤት ውስጥም ሆነ በውጪ ያላትን ተግባርን እያዩ ሲያድጉ ለልጆቿ ትልቅ አስተዋፅዖ ይኖራታል።›› የምትለው እንግዳችን ዮሀና፤ ሴት መሆኔን ሳይሆን ዓላማ ያላት ሰው መሆኔን እየነገሩኝ ያሳደጉኝ ወላጆቼ ትልቅ አቅም ሆነውኛል ትላለች።

በተለይ የአባቷ መልሶች የእርሷ ጥንካሬና ስኬት እንደሆነም ታስረዳለች። ‹‹እኔ የበኩር ልጅ በመሆኔ ሰዎች ‹ቶሎ ወንድ ልጅ ውለድ ስምህን የሚያስጠራ› ሲሉት መልሱ ግን ሁሌ አንድ ነበር። ይህም ‹ስሜን የምታስጠራ ልጅ ወልጃለሁ ያውም የኔን ሥራ የምታስቀጥል ታላቅ ሴት › የሚል ነበር። እናም ይህ ነገሩ በሴትነቴ እንድኮራ፣ ካሰብኩት እንድደርስ፤ ሴት ሆኜ መሰናክልና ተግዳሮቶቼን እንዳልፋቸው አድርጎኛል›› ትላለች።

እንደዮሐና ገለፃ፤ ሕይወትን በተግባር እንድታይ፤ እንድትማር የሕይወት አሰልጣኝዋ ሆነው ያሳደጓት እናቷ ናቸው። በተለይም ከአባቷ ሞት በኋላ ብቻቸውን ያሳደጓት እናቷ በመሆናቸው ‹‹የሴት ልጅ›› እየተባለች ማደጓ እንድትኮራ እንጂ እንድታፍር አላደረጋትም። ይልቁንም ሁልጊዜ ‹‹ሴት ያሳደገኝ ያውም የጀግና ሴት ልጅ ነኝ” እንድትል አስችሏታል። የአባቷ መሞት እሷን ጨምሮ ሦስት ልጆችን የማሳደግ ኃላፊነት እናቷ ጫንቃ ላይ ወደቀ። እርትዋ እናት ያለማንም ድጋፍ ልጆቻቸው ምንም ሳይጎልባቸው፤ በሥነ- ምግባር ታንፀው እንዲያድጉ በማድረግ ሚናቸውን በሚገባ ተወጡ። የእናቷን ጥንካሬና ታታሪነት እያየች ማደጓ በራስ የመተማመን ችሎታ እንድታዳብር አድርጓታል። ኃላፊነትን መወጣትን፣ በሕይወትን በስኬት ለመምራት ተግዳሮቶችን እንዴት ማሸነፍ እንደሚቻል ተምራለች።ጊዜንና አጋጣሚዎችን መጠቀም

ዮሀና ጊዜንና መልካም አጋጣሚዎችን በአግባቡ የመጠቀም ችሎታዋ ወደ ስኬት መድረሻ አንዱ መንገድ እንደሆነ ታምናለች። በተለያዩ ቦታዎች የሚገጥሙንን መልካምም ሆነ መጥፎ አጋጣሚዎችን ለሕይወታችን የስኬት ጉዞ እንድንጠቀመው ትመክራለች። ይህች ጠንካራ ሴት ጊዜን በአግባቡ መጠቀምን ማሳያም ነች። ምክንያቱም በአስራዎቹ መጨረሻዎች ያጋጠማትን ችግር ወደ መልካም ዕድል ቀይራ ለብዙዎች ተርፋለች።

ዮሐና በሃያዎቹ ግማሽ ደግሞ ትዳር በመመስረት የሁለት ሴት ልጆች እናትም ሆናለች። ሴቶች ሁሉን በወቅቱ በማድረግ ብልሆች መሆን አለብን የሚል አቋምም አላት። ሴቶች ስኬትና ቤተሰብን አብሮ ማስኬድ ተግዳሮት ይሆንባቸዋል። ይሁንና ቤተሰብ አንዱ የሕይወት ስኬት መገለጫም እንደመሆኑ ትኩረት ማድረግ ብልህነት በመሆኑ ችግሩን ወደ ድል ቀይረው እናያቸዋለን ትላለች።

ሴት ልጅ በቤት ውስጥ ካላት ከፍተኛ የትዳርና የልጆች እንዲሁም ቤት የመምራት ኃላፊነት ባሻገር በውጪ ወጥታ ሕልሟን ለመኖር የምታደርገው ትግል በአብዛኛው እኩል ማካሄድ ፈታኝ ይሆንባታል። እናም አንዱን በአንዱ ውስጥ ትሰዋለች፤ ሆኖም ጥቂቶች በርትተው ሁለቱንም በእኩል ለማስኬድ ችለዋልና ያን የመሆንን አጋጣሚ መጠቀም እንደሚገባም ታስረዳለች። ለዚህ ደግሞ ከትዳር አጋሯ ጀምሮ የቤተሰብ የማኅበረሰብ እንዲሁም መንግሥት ከፍተኛ ድጋፍ ያስፈልጋታል ባይም ነች።

‹‹በየዓመቱ አንድ ቀን ብቻ የሴቶች ቀንን በጋራ ከማክበር ባለፈ የሴቶችን አቅም ለማዳበር በሞራል፣ በኢኮኖሚ፣ የተለያዩ ግብዓቶች መደገፍ የዕለት ተዕለት ተግባር መሆን ይኖርበታል። ያኔ ነው ሀገራችን በተገቢው የሴቶችን አቅም በአግባቡ መጠቀም የምትችለው›› የምትለው ዮሐና፤ ሴትም የራሷ ድርሻ እንዳላት ታነሳለች። ሕይወት በብዙ አማራጭ ጎዳናዎች የተሞላች ነች። እኛም የምርጫችን ውጤት ነን፤ ይህ ከሆነ ደግሞ ምርጫችንና ውሳኔያችንን ራሳችን እንጂ ሌላ ሰው እንዲመርጥልን አሳልፈን መስጠት የለብንም የሚል እምነት አላት። መኖራችን ዓላማና ግብ ያለው መሆን ይገባዋል ብላ ታስባለችም። የምንወደውን በመሥራት የምንኖርንበትን ዓላማ ልናሳካ እንደሚገባ ትመክራለች።

የሕይወት ፍልስፍና

‹‹ተመሳስሎ ሁሉም የሚኖረውን መኖር አልወድም፤ አዲስ ነገርን መሞከር ያስደስተኛል፣ ታግዬ ማሸነፍ ለሕይወቴ ትርጉም ይሰጠኛል፣ ሌሎች የፈጠሩልኝ ዓለም ተቀብሎ መኖር ሳይሆን ለሌሎች መትረፍ እርካታ ይሰጠኛል›› የምትለው እንግዳችን፤ ይህንን በተግባር የተረጎመች ትገኛለች። ገና በለጋ እድሜዋ የትላላቅ ዕራዮች ባለቤት፣ ከራስና ከቤተሰብ ያለፈ ኃላፊነት ያለባትና በዚህች የምድር ቆይታዋ በዓላማ ተፈጥራ፣ ለዓላማዋ ኖራ፣ ዓላማዋን ፈፅማ ለማለፍ እየታተረች ትገኛለች። በዚህ አቋሟም ብዙዎችን ከችግራቸው ታድጋለች።

ለአብነት ሕጻናትና ሴቶችን የሚረዳ ሀገር በቀል በኋላም ዓለምአቀፍ የሆነውን ‹‹ሴቭ ሄቨን አሶሴሽን የእርዳታ ድርጅት›› በማቋቋምና በሥራ አስኪያጅነት በመምራት አጋርነቷን ማሳየት ችላለች። የብዙ ሺዎችን ሴ ትና ሕጻናት እንባ አብሳለች። የተጎዱና በኤች.አይ. ቪ በደማቸው ውስጥ ያሉ ሴቶችን አቅም አጎልብታ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች መኖርን እንዲጀምሩ አድርጋለች። በዚህም ሥራዋ ደግሞ በሀገራችንና በተለያዩ አሕጉረ አፍሪካ፣ አውሮፓና ሰሜን አሜሪካ በመዘዋወር ሽልማቶችን አግኝታለች። የሀገር ውስጥና የውጪም መጽሔቶችና ጋዜጦች ‹‹ወጣቷ በጎ አድራጊ›› በሚል ርዕስ ስለእሷ ከትበውላታል።

ዮሐና በመውደቅ መነሳት ውስጥ አቅሜን እፈትናለሁ የሚል አቋምም ያላት ወጣት ነች። ከዚህ አንጻርም በሰው አዕምሮ፣ ሕይወትና ስብዕና ላይ መሥራት ያስደስታታል። ብዙው ጊዜዋንም የምትፈጀው በዚሁ ተግባር ላይ ነው። በእሷ እድሜና በሴቶች የማይደፈሩ ሥራዎችን መሞከር ልምዷም ፍላጎቷም ነው። ምክንያቷ ደግሞ ለሌሎች ተምሳሌት መሆንን ትፈልጋለችና ነው። በተለይ የሁለት ሴት ልጆች እናት መሆኗ ይህንን ሥራ ይበልጥ እንድትገፋበት አድርጓታል። ሴት ልጆቿም ሆኑ ሌሎች ሴቶች ሴትነት ውበት፣ ጥንካሬ፣ ስኬታማነት መሆኑን እንዲያምኑና በዚያ መሠረት ላይ እንዲቆሙም ትፈልጋለች። ‹‹ሴትነት የፆታ መገለጫ እንጂ የአቅምና የብቃት ማሳያ አይደለም›› የሚለውን አቋሟን አበክራ ለሁሉም ማስረዳት ትሻለች።

የሥራ ሕይወት

ዛሬ በሦስት ከተሞች ላይ ካምፓሶችን ከፍታ በማንኛውም ቦታ ላይ ብትሆን እንደምታሸንፍ አሳይታለች። አምስት ዓመታትን ያሳለፈው ‹‹ጎልደን ስታርስ ኮሌጅ›› በቲቪቲ፣ ዲግሪ ተማሪዎችን ያሠለጥናል። በቅርቡ ደግሞ በማስተርስ ለማስተማር በዝግጅት ላይ ይገኛል። ለበርካታ ምሑራን መምሕራንና ሠራተኞች የሥራ እድል ፈጥሯል። ማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎትም እየሰጠ ነው። የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን በመሥራትም ሀገራዊ ኃላፊነቱን ይወጣል። ለበርካታ አቅመ ደካማ ተማሪዎች ነፃ ትምህርት ዕድልን፤ ለተማሪዎች፣ ሴቶችና ወጣቶች ሥልጠናዎችና ይሰጣል።

ዮሐና የወጣቶችና የሴቶችን አቅም ለማጎልበት ‹‹በጎልደን ብሪጅ ሥልጠናና ማማከር ድርጅትም›› የተለያዩ አመራርነት፣ የአቅም ግንባታ፣ የሥራ ፈጠራ ክህሎት እንዲሁም አጫጭር ሥልጠናዎችን ትሰጣለች። በማማከርና በአጠቃላይ በተለያዩ ከተሞች የሴቶችን የሚያበረታታ አቅም ግምባታና የማነቃቂያ ዎርክሾፕ በማድረግ የተለያዩ ወጣቶችንና ሴቶችን የሚያበረታቱ ተግባራትን ታከናውናለች። በውሳኔዋ መፅናቷና ተግዳሮቶቿን በድል በመወጣቷ በምታገኘው እርካታ የገጠሟትን መሰናክሎች ሁሉ እንደ መስፈንጠሪያ ድንጋይ መጠቀምን ትወዳለች። ዛሬ ለብዙዎች የምታካፍለውና በርካቶችን የምታበረታታውም ለዚህ ነው።

ሰው ሥራ ሲሠራ ደልዳላ የሕይወት ጎዳና መጠበቅ የለበትም። አባጣ ጎርባጣው ከስኬት ላይ እንደሚያደርስም መረዳት ያስፈልጋል። ድሉ ደግሞ ጣፋጭ እንደሚሆንም መመልከት ይገባል። ስለዚህም ስኬትን በቁስ፣ ዝናና፣ ክብር ብቻ መመልከት አይኖርብንም። ስኬት ከዚያም በላይ ነው፡ ሕልምን የመኖር፣ የሌሎች መትረፍም መሆኑን መገንዘብ አለብን›› የምትለው ዮሐና፤ በሀገሪቱ የሴቶች ቁጥር ከፍተኛ ቢሆንም በተለያዩ አስተሳሰብ፣ ችግሮችና ተግዳሮቶች ምክንያት አቅማቸውን ማውጣት ባለመቻላቸው ሀገር በሚፈለገው መጠን አልተጠቀመባቸውም። በኅብረተሰቡና በሌሎች ላይ በማሳበብ ያላቸውን እድል ሳይጠቀሙ አቅማቸውን በተገቢው ሳያወጡ፣ ሕልማቸውን ሳይኖሩ በሌላ ሰው ሕልም ተሸፍነው በቁጭት የሚኖሩ በርካቶች ናቸው። ስለሆነም ሴቶች ሕልምን ለመኖር ቆራጥነትን፣ የውሳኔ ሰው መሆንንና ውጣውረዶችን ለመጋፈጥ መወሰን ይኖርባቸዋል ትላለች።

የሥራ ላይ ፈተና

‹‹ሴት ሆኜ ለመፈጠሬ አስተዋፅዖ ባይኖረኝም የማኅበረሰቡን ኋላቀር አስተሳሰብ ተጋፍጦ ማሸነፍ ግን እችላለሁ። በሴቶች ላይ ያስቀመጠውን ገደብ ማለፍ እንደሚቻልም በኔ ፅናትና ትጋት ማሳየት እችላለሁ›› የምትለው ዮሐና ለብዙዎች እንደ ችግር የሚመለከቱት ነገር ለጥቂቶች መልካም አጋጣሚ የሥራ እድልም ይፈጥራል ብላ ታስባለች። ለዚህም እንደማሳያነት የምትጠቅሰው በ2011 ዓ.ም በደቡብ ክልል የሆነውን ጉዳይ ነው። በወቅቱ የነበረውን የክልል መሆን ጥያቄና አለመረጋጋት ምክንያት ብዙዎች ሀዋሳ ከተማን ጥለው ቢወጡም እርሷ ግን ወደዚያ በማምራት ችግሩን ወደ ጎን ትታ የወቅቱ ሁኔታ ሳይበግራት ኮሌጅ መክፈት ለስኬት በቅታለች።

በእርግጥ በጊዜው በበርካታ ፈተና ተፈትናለች። በተለይም ወደማታውቀው ቦታ በድፍረት መሄዷና የአካባቢው ባሕልና ወግ ያለማወቋ እንዲሁም የተመቻቸ ኑሮዋን ቤተሰቧን ትታ መሄዷ ነው። ሌላኛው ደግሞ ለቅርብ ቤተሰቧና ጓደኞቿ በአካባቢው የነበረው የፀጥታ ችግር ስጋትና ጭንቀት ከፍተኛ እንደነበር ታስታውሳለች። በአብዛኛው በወንዶች የሚሠራ የከፍተኛ ትምህርት ሴክተር በመምረጧ ብዙዎችን ሴት ተቋም መርታ ለምርቃት ታበቃለች ብሎ ማመንና መቀበል አቅቷቸው ነበር። ሆኖም ከጎኗ በነበሩት ከቤተሰብ እስከ አንዳንድ በሀዋሳ ከተማ በነበሩ ጥቂት የኮሌጅ ባለቤቶችና አመራሮች እንዲሁም በማኅበረሰቡ ድጋፍ ነገሩን እንድታልፈው ሆናለች፤ በተለይ የልጆቿን ድጋፍ ሳታስታውስ ማለፍ አትችልም።

ቀጣይ እቅድ

ዮሐና በቀጣይ ኮሌጁን ከዓለም አቀፋዊ የትምህርት ተቋማት ጋር በጋራ በመሥራት ጥራት ያለው የትምህርትና የምርምር ማዕከል ማድረግ ትፈልጋለች። በተመሳሳይ በሥልጠናውና ማማከሩ ዘርፍ እንደምትገፋበትም ትናገራለች። በቅርቡ ደግሞ በአዲስ አበባ እየከፈተች ባለችው ሴቶችና ወጣቶች ሥልጠናና ማማከር ማዕከል ጠንክራ መሥራት እንደምትሻ ትገልጻለች። ከዲግሪ እስከ ዶክትሬት በውጪ ሀገር ለመማር የሚፈልጉ ሰዎች በማማከር፣ ማገናኘትና ጉዞን ጭምር ማመቻቸት ሥራ በትኩረት እንደምትገፋበት ታስረዳለች። እንዲሁም ከኬጂ እስከ ዩኒቨርስቲ የሚያስተምር የትምህርት ማዕከል የመሥራትም ሕልም አላት። በመጨረሻም ሀገር የተወሰኑ ግለሰቦች ኃላፊነት ብቻ ሳትሆን የሁሉም ዜጋ ድርሻ ናትና አባቶቻችን በደም መስዋዕትነት ያቆሟትን ሀገር እያንዳንዱ ግለሰብ ማስቀጠል አለበት። እኔም በገንዘቤ፣ በእውቀቴ፣ በጉልበቴ ትውልድ ላይ በመሥራት ለልጆቼ የተሻለች ሀገር ለመገንባት የበኩሌን አደርጋለሁ በማለት ቃል ገብታ ሀሳቧን ትቋጫለች።

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን የካቲት 29 /2016 ዓ.ም

Recommended For You