ወቅቱ በኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት ነበር። የጊዜው ጠቅላይ ሚንስትር የነበሩት አቶ ታምራት ላይኔ ባለቤት ናቸው። ወይዘሮ ሙሉ ግርማይ ይባላሉ። ይህችን ምድር የተዋወቁት በቀድሞው አጠራር በወሎ ክፍለ ሀገር በሰቆጣ ከተማ ነው።
በዚያው ስፍራ ጭቃ አቡክተው አፈር ፈጭተው አድገዋል። እናታቸው ወይዘሮ ማማዬ አሸብር ይባላሉ። ከአባታቸው ግርማይ ወልደትንሳኤ አብራክ ተከፍለዋል። የምድርን በጎ ጎን ቢያውቁትም ዓለም የከፋ ጎኗንም አስጎብኝታቸዋለች። በሕይወታቸው እልፍ የመከራ ሰልፎችን አልፈዋል።
ያለፉበት የሕይወት ውጣውረድ ለብዙዎች መማሪያ ይሆናል። የመሠረቱት የበጎ አድራጎት ድርጅትም ሰዎችን ደግፎ ይዟል። ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትም ጋር የሕይወት ልምዶቻቸውን አውግተዋል። ወደ ፖለቲካ ሕይወት አገባባቸውን ሲያወሱ፤ በ1973 ዓመተ ምህረት የቀድሞው ኢህዴን / ብአዴን የአሁኑ አዴፓ ፖለቲካ ድርጅት ተመሠረተ። ዓላማውም ደርግን ለመጣል ነበር። የትጥቅ ትግሉን በዋግ አካባቢ ሲጀምር እርሳቸውም ዕድሉ ደረሳቸው። እንደ ዘመኑ ወጣቶች የደርግን መንግሥት አምርረው ይጠሉ ነበር። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አቋርጠው በ1975 ዓመተ ምህረት የትጥቅ ትግሉን ተቀላቀሉ።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል ከጊዜ ወደ ጊዜ ጠነከረ። በ1983 ዓመተ ምህረት የደርግ መንግሥት ከስልጣን ተባረረ። ቀደም ሲል በአራት ድርጅቶች ጥምረት በተመሠረተው ኢህአዴግ፤ የበላይነት የሽግግር መንግሥት ተቋቋመ። ባለቤታቸው አቶ ታምራት ላይኔ የሽግግር መንግሥቱ ጠቅላይ ሚንስትር ነበሩ። እርሳቸው ደግሞ የአዲስ አበባ ሪጅን ጽሕፈት ቤት የኢህአዴግ ድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ሆነው እየሰሩ ቆዩ።
ከዚህ በኋላ ሕይወት አልጋ በአልጋነቷ ቀረ። በ1989 ዓመተ ምህረት ባለቤታቸው ለእስር ተዳረጉ። በወይዘሮ ሙሉ አጠራር የባለቤታቸው መታሰሪያ ምክንያት “በሥልጣን ያለአግባብ መጠቀም” የሚል የፖለቲካ ሴራ ነው። ኢህአዴግ አቶ ታምራትን ለእስር ዳረገ። ከባለቤታቸው መታሰር በኋላ ሕይወት ጨለማ ጎኗን አስጎበኘቻቸው። ወይዘሮ ሙሉ ‹‹በሕይወቴ ይገጥመኛል›› ብለው ከማይገምቱት ፈተና ላይ ወደቁ። የአቶ ታምራት ሚስት በመሆናቸው ብቻ የመከራ ፅዋን ተጎነጩ። ከሥራ ቦታቸው እና ከኃላፊነታቸው ያለ አንዳች ርህራሄ ተባረሩ።
ወይዘሮ ሙሉ በወቅቱ ምንም ዓይነት ገቢ አልነበራቸውም። እንደ ቤተሰብ ከሚያዩት ድርጅት መባረር ልባቸውን አቆሰለው። ያኔ የመጀመሪያ ልጃቸው አራት ዓመቱ ነበር። ሁለተኛ ልጃቸው የአንድ ወር ጨቅላ ሕፃን ነበረች። የአራስነት ወጉ እንደናፈቃቸው ቀረ። ሲኖሩበት ከነበረው የመንግሥት ቤትም ሳይቀር እንዲወጡ ተደረገ።
ከእለት ወደ እለት ማወከቦች ፣ የማፈን ሙከራዎች፣ ማስፈራሪያዎችና ልዩ ልዩ ፈተናዎችን ያሳልፉ ነበር። ይህ ችግር ሲጨምር በ1992 ሁለት ልጆቻቸውንና ታናሽ እህታቸውን ይዘው ወደ ኬንያ በግፍ ተሰደዱ። በጊዜው የደረሰባቸው መከራና መገፋትን ሲጎነጩ ቆዩ። በልጆች ላይ ሲሆን ደግሞ ከባድ ነው። እንደ እናት ራሳቸውን በድለው ለልጆቻቸው ኖሩ። ጥርሳቸውን በመንከስ ለወለዷቸው ሲሉ በረቱ።
ወይዘሮ ሙሉ በኬንያ አስቸጋሪ ሦስት ዓመታትን አሳለፉ። ከዚህ የስደት ቆይታ በኋላ በ1995 ሌላኛዋ የስደት መዳረሻቸው አሜሪካ ሆነች። በስደት እንዲገቡ ተፈቅዶላቸው በኮሎራዶ ግዛት ዴንቨር ከተማ መኖር ጀመሩ። በአሜሪካን ሀገር ልጆቻቸውን ብቻቸውን ማሳደግ ቀጠሉ። በሀገሪቷ ያልሰሩት ሥራ የለም ለማለት በሚያስደፍር መልኩ ብዙ ሥራዎችን ሰርተዋል። በጊዜውም የጋዝ ማደያ፣ የልብስ መሸጫ መደብርና የመሳሰሉት በእርሳቸው ከተሰሩት መሀል ናቸው። ሥራቸውን እየሰሩ ልጆቻቸውን ማሳደግና ማስተማር ቀጠሉ።
ለአስራ ሁለት ዓመታት ልጆቻቸውን ያለ አባት አሳደጉ። ባለቤታቸው አቶ ታምራት ላይኔ በ2000 ዓመተ ምህረት ከእስር ተፈቱ። ወደ አሜሪካን ሀገር በመሄድም ቤተሰቦቻቸውን ተቀላቀሉ። ባለቤታቸው አሜሪካ በመጡበት ወቅት ወይዘሮ ሙሉ ጋዝ ማደያ ተቀጥረው ይሰሩ እንደነበር ያስታውሳሉ። እነዚያን ረጅም ዓመታት ልጆቻቸውን ያለ አባት ማሳደጋቸው ብዙ አስተምሯቸዋል። ሕይወት በመከራ ሞረድ ሞረደቻቸው። እርሳቸው ባለፉበት የመከራ ሕይወት ውስጥ ሌሎች እንዲያልፉ አልፈቅድም አሉ። ልጆችና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው እናቶችን በተለየ መንገድ ማሰብን ቻሉበት። በሚወዷቸውና የእኔ በሚሏቸው ሰዎች መጠላትና መገለል አሳዛኝ የሕይወት ክስተት መሆኑን ተገነዘቡ። እናም የተቸገረን ሰው ቀርቦ ማፅናናትና መደገፍ ምን ያህል የተቀደሰ ተግባር መሆኑን ከሕይወታቸው ተማሩ።
ከዚያም የእርሳቸው እና የቤተሰባቸው የመከራ ውጤት ፍሬ አፈራ። በ2005 ዓመተ ምህረት ቤተሰብ ጥየቃ ሲመጡ፤ በየመንገዱ የሚለምኑ እናቶችን ጎዳና የወጡ ሕፃናትን ተመለከቱ። ለችግር የተጋለጡ፤ ወላጆቻቸውን ያጡ ልጆችና መበለቶችን የሚያግዝ ድርጅት በእርሳቸው ተከፈተ። በዚሁ ላይፍ ሴንተር ኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ድርጅት ሊመሰረት ቻለ። ላይፍ ሴንተር ኢትዮጵያ ሴቶችን የሚያበረታ የሚያፅናና ድርጅት ነው። ከራሳቸው ሕይወት በመነሳት የከበዳቸው ቀን እንደሚያልፍ ያሳዩዋቸዋል። በአቅምም በሞራልም ይደግፏቸዋል።
ድርጅቱ መቀመጫውን በተለያዩ ሥፍራዎች አድርጓል። በአዲስ አበባ ፣ በአማራ ክልል ዋግህምራ ሰቆጣ ላይ ከትሟል። ከ400 በላይ መበለቶችንና ከ280 ወላጆቻቸውን ያጡ ለችግር የተጋለጡ ልጆችን በመርዳት ላይ ነው። ይሄኛው ሕይወት ለወይዘሮ ሙሉ ተስማምቷቸዋል። በሚረዷቸው ዜጎች ዓይን ላይ የተኳለ ፈገግታ ታድለዋል። ልባቸው አርፏል።
በመልዕክታቸውም ሰዎች ካገለገሉበት ድርጅት ሲገለሉ ቤተሰብ ባይጎዳ ብለዋል። ከዚህም በላይ ሰው ካለፈበት ችግር ሊማር ይገባዋል ይላሉ። ሰዎች በራሳቸው ልጅ ማድረግ የማይፈልጉትን በሌላው ልጅ ባያደርግ የሚል አደራቸውን ሰጥተዋል።
ዳግማዊት ግርማ
አዲስ ዘመን የካቲት 29 ቀን 2016 ዓ.ም