‹‹ዓለም በዕልህ እና በጦርነት የምትታመሠው ሴት ባለመደመጧ ነው››  ወ/ሮ እየሩሳሌም ሹምዬ፣ በአፍሪካ ሕብረት የጥናት ትንተና ክፍል ዋና ሃላፊ አማካሪ

ወልቃይት ፀገዴ ማይአይኒ በምትባል መንደር ውስጥ የተወለደችው እየሩሳሌም ሹምዬ፤ ገና በጨቅላነቷ ከሞት ጋር ታግላለች። ከቤተሰቦቿ ጋር ከአውሮፕላን የሚዘንበውን ቦንብ ሸሽታ በዋሻ ለቀናት ውላለች። ጊዜው 1980 ዎቹ አካባቢ በመሆኑ መንደራቸው የነበረው ጦርነት ቤተሰቦቿን እንዳያሳጣት በብዙ ስጋት ውስጥ አልፋለች።

ጦርነትም ቢኖር ሕይወት ይቀጥላል፤ በአካባቢው ትምህርት ቤት ስላልነበር ቀራቀር ከተማ አያቷ ቤት ሔደች። ትምህርት ቤት ስትገባ ባለምጡቅ ዓዕምሮነት ታዋቂነትን አተረፈች። ለእዚህ የበቃችው አባቷ አቶ ሹምዬ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጤና መኮንን ስለነበሩ ለአካባቢው ሕብረተሰብ የህክምና አገልግሎት ከመስጠት በተጨማሪ ልጆችን ሰብስበው ያስተምሩ ነበርና በእንግሊዘኛም ሆነ በአማርኛ ፊደል ለይቶ ከማወቅ ጀምራ ማንበብ እና መፃፍ እንዲሁም አንዳንድ መሰረታዊ የዕውቀት መነሻዎችን ከአባቷ በመማሯ ነበር።

ቀራቀር ገብታ በ1985 ዓ.ም ስትፈተን የአንደኛ ክፍል ትምህርትን ብቻ ሳይሆን የሁለተኛ ክፍል ፈተናንም በማለፏ በአንድ ጊዜ ለአንድ የግማሽ ዓመት መንፈቀ ትምህርት የ2ኛ ክፍል ትምህርቷን፤ በ2ኛው መንፈቅ ዓመት የ3ኛ ክፍል ትምህርቷን አልፋ 4ተኛ ክፍል ደረሰች። በ1986 ዓ.ም የእየሩሳሌም አባት አቶ ሹምዬ በሥራ ምክንያት ወደ ሽሬ እንዳስላሴ ሔዱ። በዚህ ምክንያት እርሷም ሽሬ ገብታ ፀሐዬ ትምህርት ቤት ለአንድ ዓመት ከተማረች በኋላ የ5ኛ ክፍል ትምህርቷ ደግሞ እምባ ዳንሶ በሚባል ትምህርት ቤት እስከ 8ኛ ክፍል ተምራ እዛው ሽሬ ከ9ኛ ክፍል መማር ጀመረች። ሆኖም የ10ኛ ክፍል ትምህርቷን ከመጀመሯ በፊት በ17 ዓመቷ ተዳረች።

ትዳር የመሰረተችው ባለቤቷን አውቃው ሳይሆን የእርሷ እና የባለቤቷ ቤተሰቦች ተነጋግረው በመስማማታቸው ነው። ባለቤቷ ከአዲስ አበባ ወደ ሽሬ ሔዶ አርብ ቀን ዓይታው እሁድ አገባት። አዲስ አበባ ይዟት መጣ። ሽመልስ ሃብቴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብታ መማሯን ቀጠለች። ምንም እንኳ ልጅ ብትሆንም ትዳር ይዛለችና ቤቷን ለመምራት ስትል የማታ ለመማር ተገደደች። ከተማው ለእርሷ ሰፊ በመሆኑ ተወዳዳሪ ለመሆን ያዳግተኛል የሚል ስጋት አደረባት። ትዳሯ ብቻዋን ከአጋሯ ጋር ሆና የምትመራው ሳይሆን የባለቤቷ ቤተሰቦች ቤት አንድ ላይ ብዙ ሆነው ስለሚኖሩ ተደራራቢ የሥራ ጫናዎችን መጋፈጥ ግድ ሆነባት።

በቤቱ ውስጥ እንደሰራተኛም እንደባለቤትም ሆና የ11ኛ ክፍል ትምህርቷን ስትከታተል እርግዝና ተከሰተ። በተጨማሪ 12ኛ ክፍል ስትደርስ ወንድ ልጅ ወለደች። ባለቤቷ የከተማ ሰው ሆኖ እርሷ የገጠር ሰው ሆና በዛ ላይ ልጅነት ተጨምሮበት ከባለቤቷ ጋር መግባባት አስቸጋሪ ሆነ። ያም ቢሆን በአራስነቷ የ12ኛ ክፍል የማጠቃለያ ፈተናን ወሰደች። ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባ ውጤት አላመጣችም። ስለዚህ ኮሌጅ ለመግባት ተገደደች። ልጇን እያሳደገች ለመማር አድማስ ኮሌጅ ገብታ የቀን ትምህርት ጀመረች። በጥሩ ውጤት አጠናቀቀች። ነገር ግን በቀን ትምህርቷን መቀጠል አልቻለችም። አንደኛው ምክንያት የኮሌጁን ክፍያ መሸፈን አለመቻሏ ሲሆን፤ ሌላው በቤት ውስጥ በሥራ የሚረዳት ባለመኖሩ እና ልጇን ለማሳደግም በመቸገሯ ትምህርቷን ወደ ማታ አዘዋውራ ሥራ መፈለግ ጀመረች።

በጣም ጎበዝ መሆኗን የተረዱ የኮሌጁ መምህራን መስክረውላት ተወዳድራ አልፋ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በመማሯ የላብራቶሪ እረዳት ሆና ተቀጠረች። አድማስ እየሠራች አድማስ እየተማረች ሌላ የመንግስት መስሪያት ቤት ደግሞ አመለከተች። በተወዳደረችበት የመንግስት መሥሪያ ቤት ለመቀጠር በቃች። ከዛ ሕይወት ቀለል ማለት ጀመረ። ከትዳር አጋር ጋር ቤት ተከራይተው ራሳቸውን ችለው መኖር ጀመሩ። ወ/ሮ እየሩሳሌም ሹምዬ ዛሬ አድማስ ኮሌጅ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዲግሪ ከመያዝ አልፋ፤ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሰላም እና ደህንነት ተቋም፤ በአፍሪካ ሰላምን በማስተዳደር ዙሪያ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቷን አጠናቅቃለች። በተጨማሪ ተቋምን በመምራት እና በማስተዳደር (ኦርጋናይዜሽናል ሊደር ሽፕ) የሁለተኛ ዲግሪዋን ተምራለች።

አሁን በአፍሪካ ሕብረት የጥናት ትንተና ክፍል ዋና ሃላፊ አማካሪ ሆና በማገልገል ላይ ትገኛለች። የሁለት ልጆች እናት ሆና ብዙ ውጣ ውረዶችን ብታልፍም የራሷን ተሞክሮዎች እና ሌሎችም የምታምንባቸውን የሕይወት ፍልስፍናዎችን አካታ ‹‹ራስን የመሆን ሚስጥር ›› የተሰኘ መፅሃፍ ፅፋ ሰሞኑን አስመርቃለች። ከዛሬዋ ከሴቶች ቀን እንግዳችን እየሩሳሌም ሹምዬ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እነሆ ብለናል። መልካም ንባብ፡-

 አዲስ ዘመን፡- ትምህርት፣ ሴትነት፣ የቤተሰብ ሃላፊነት እንደገና የሥራ ሕይወት ይሔ ሁሉ አብሮ የሚሔደው እንዴት ነው?

ወ/ሮ እየሩስ፡- የመንግስት መስሪያ ቤት ተቀጥሬ በተደጋጋሚ ከራሴ ጋር አወራ ነበር። ስራዬን ጥንቅቅ አድርጌ እሰራለሁ። ቤቴን በአግባቡ እመራለሁ። ዲግሪዬንም ከጨረስኩ በኋላ ቋንቋን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ስልጠናዎችን በመሳተፍ ሰርተፍኬት እሰበስብ ነበር። ጎን ለጎን አርት ስኩል እማር ነበር። ከባለቤቴ ጋር ልጆቻችንን ስናሳድግ ለብዙ ጊዜ ሰራተኛ አልነበረኝም። የማታ ስማር ምሽት ሶስት ሰዓት ቤቴ ደርሼ የምሳ ዕቃ እና ሌሎችም ለምግብ ማብሰያ እና መስሪያ አገልግሎት ሥራ ላይ የዋሉ ዕቃዎችን አጥባለሁ። በማግስቱ ቤተሰቤ የሚመገበውን ምግብ አስቀድሜ ምሽት ላይ አበስላለሁ። የምሳ ዕቃ ጠረጴዛ ላይ ደርድሬ ስጨርስ ገላዬን እታጠባለሁ። ከዛ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ማጥናት ያለብኝን አጠናለሁ። ለትምህርቴ የሚያግዙ መፅሃፎችን አነባለሁ።

በማግስቱ 11 ከአርባ እነሳለሁ። ቁርስ አቅርቤ የሚታሠረውን ምሳ አስሬ ልጆቼን ካዘጋጀሁ በኋላ የሚፀዳውን አፀዳድቼ ከቤቴ እወጣለሁ። በዛ ሰዓት እኔ ትልቅ ጉዳት የምለው ትምህርቴን ለማቆም ካስገደዱኝ ብቻ ነበር። ትምህርት ማቆም የሕይወቴ መጨረሻ ይሆናል ብዬ አምን ነበር። በትምህርቴ አልደራደርም ነበር። ከዛ ውጪ በምንም ነገር ላይ ታግሼ ኖሬያለሁ። እንደእኔ በልጅነታቸው ተድረው አዲስ አበባ የገቡ ሴቶችን ሕይወት አያለሁ። ያንን ሕይወት በፍፁም አልመኘውም ነበር። ስለዚህ ያ እንዳይሆን በፕሮግራም እየተመራሁ ራሴን ለማሻሻል ከፍተኛ ጥረት አደርግ ነበር።

እኔ ላይ የነበረው ችግር ምንም ዓይነት ማህበራዊ ኑሮ ተሳትፎ አልነበረኝም። ሰርግም ሆነ ልደት ምርቃትም ሆነ ማንኛውም ጥሪ አልሔድም ነበር። ከሰኞ እስከ ዓርብ ቀን እየሠራሁ ማታ ማታ እማራለሁ። እሁድ እና ቅዳሜ ማጥናትን ጨምሮ ቤት ማፅዳት እና ልብስ አጠባን የመሳሰሉ ሌሎች ሥራዎች የሚከናወኑበት ቀናቶች ነበሩ። ከሰዎች ጋር የማወራበት ሰዓት አልነበረኝም። ነገር ግን ሰዓት ሳገኝ ከራሴ ጋር አወራ ነበር። ከዛም ቅዳሜ እና እሁድ ትምህርት ላይ መውሰድ ያለብኝ ስልጠና መኖሩን ካረጋገጥኩ ስልጠናዎችን እወስድ ነበር።

አዲስ ዘመን፡- ከልጆች እና ከባለቤት ጋር ሰዓት ማሳለፍ ያስፈልጋል። ከቤተሰብ ጋር ሰዓት ነበረሽ?

ወ/ሮ እየሩስ፡– መጀመሪያ አንድ ልጅ ብቻ ስለነበረችኝ ብዙ አልቸገርም ነበር። ልጄ የቤት ሥራዋን ሠርታ ያቃታትን ይዛ ትጠብቀኛለች። ከደከማት ትተኛለች። ከባለለቤቴ ጋር ወጥ አሙቄ ራት ከበላን በኋላ ደብተሯን አያለሁ። ከአባቷ ጋር በዛ ሰዓት እናወራለን። ቅዳሜ እና እሁድ ደግሞ የቤቱን ሥራ እየሠራሁ ከእርሷ ጋር ጊዜ አሳልፍ ነበር። ማራሚያዊት ብዙም አስቸጋሪ አልነበረችም። ሁለተኛው ልጅ አማኑኤል ሲወለድ ግን ከፍ ያለ እንክብካቤ ይፈልግ ነበር። ስለዚህ መደበኛውን የማታ ትምህርት እስከ ዲግሪ ተምሬ በማጠናቅቄ በቅርበት እርሱን የምንከባከብበት ጊዜ አላጣሁም። ትምህርቱንም በደንብ እከታተለው ነበር።

ምንም እንኳ ከዕለት ወደ ዕለት ደምወዜ እያደገ ሕይወቴ እየተሻሻለ ቢሔድም ደስተኛ አልነበርኩም። የምፈልገውን ሕይወት እየገፋሁ እንዳልሆነ ይሰማኝ ነበር። ምክንያቱም እኔ ውስጤ ነፃ ነው። ይህንን አድርጊ ይህንን አታድርጊ ተብዬ መኖር አልፈልግም። ሃሳቤን ጠረጴዛ ላይ አቅርቤ የሌላው ሰው ሃሳብም በጠረጴዛ ዙሪያ ቀርቦ ተማምኖ ተነጋግሮ መቀጠል እንጂ ሁሉ ነገር ተጭኖብኝ ሁኚ፣ ስጪ፣ አምጪ እየተባልኩ መኖር አልፈልግም። ደስተኛ ሳልሆን ሕይወቴ እንዲያልፍ አልፈልግም። በራሴ ዙሪያ የምፈልገውን አድርጌ መኖር አፈልጋለ ሁ።

አዲስ ዘመን፡- እና ልጆች ተወልደዋል። ብዙ ሰው ለልጆቹ ሲል የማይፈልገውን ሕይወት እየመራ ሕይወቱ ያልፋል። አንቺ ምን አደረግሽ?

ወ/ሮ እየሩስ፡- የእኔ ሕይወት ትንሽ ይለያል። መጀመሪያም ትዳር መሰረትኩ ይባል እንጄ የራሴ የምለው የትዳር ሕይወት አልነበረኝም። ከላይ እንደገለፅኩት አገባሁ፤ የገባሁት ግን የባለቤቴ ቤተሰቦች ቤት ነው። ሥራ መሥራቱ ይህን አድርጊ ሲባል ከመታዘዝ አልፎ፤ ፈጣሪ የሚሰጠውን የምወልደውን ልጅ እንኳን እኔ ፆታውን እንደፈለግኩ መወሰን እንደምችል አድርጎ ቅሬታ የማቅረብ ሁኔታ ነበር። ትዳሩ የተመሠረተው ፍቅር ላይ አልነበረም። ጭራሽ መተዋወቁም አልነበረም። ገና ከመጀመሪያው ትዳሩ ተዋውቆ፣ ተግባብቶ ተፋቅሮ ኑሮን ለማጣጣም ሳይሆን ትዳር የሚባል ካምፓኒ እንዲመሠረት እና ልጅ እንዲወለድ ብቻ ታስቦ ነው።

የነበርኩበት ሁኔታም ከትዳር በኋላ ፍቅር ለመመስረት የሚመች አልነበረም። በብዙ አስተሳሰብ ውስጥ ያሉ ብዙ ሰዎች የሚኖርበት ቤተሰብ ሲሆን፤ ባለትዳር የሆነው እና ያልሆነው፤ በቤት ውስጥ ለመስራት የተቀጠረው እና ያልተቀጠረው አይነሳም ነበር። ብዙ የሥራ ጫናም ነበር። ወጥ እሰራለሁ፤ እንጀራ እጋግራለሁ። ከዛ አልፎ ያለ አቅሜ ብርድ ልብስ እና ጋቢ ከማጠብ ጀምሮ ከበድ ያሉ ሥራዎችን እንድሰራ እገደድ ነበር። ያ ደግሞ በትዳሬ ላይ ተስፋ እንድቆርጥ አድርጎኛል። ቤተሰቦቹ ከፈለግሽ ኑሪ ካልፈለግሽ መሔድ ትቺያለሽ አይነት አስተያየት ነበራቸው።

ልጅ ይዤ ወደ ሽሬ ብሔድ ካለው ሕይወት የባሰ ጉስቁልና እንደሚያጋጥመኝ በማመን ታገስኩኝ። ከዛ ሕይወት የሚያወጣኝ ትምህርት መሆኑን በማመን ከትምህርቴ ጋር ተጣበቅኩኝ። በአብዛኛው እኔ የምፈልጋቸውን ዕውቀቶች ልቀስምባቸው የምችልባቸው መፅሐፎች የተፃፉት በእንግሊዘኛ ነው። እንግሊዘኛውን መፅሐፍ አንብቦ መረዳት ከባድ ሆነብኝ። ስለዚህ የቋንቋ ትምህርት ቤት መግባት እና ገንዘብ ሲገኝ ደግሞ የግል የቋንቋ አስተማሪ መቅጠር የግድ ሆነ። ስለዚህ እንደሌላው ሰው ገንዘብ ሳገኝ ልብስ እና የቤት ዕቃ ከመግዛት ይልቅ ወደ ፊት ለመሔድ ባለኝ መንገድም ሆነ ገንዘብ በሙሉ እጠቀም ነበር።

እቁብ እገባ እና ሲደርሰኝ የማውለው ለትምህርት ነበር። ባለቤቴም በተደጋጋሚ ትምህርት ቤት እንዳልሔድ መማሬን እንዳቆም ይገፋኝ ነበር። ለምሳሌ ቀን የሚያደክም ሥራ ሠርቼ። ማታ ተምሬ። በታክሲ ተጋፍቼ ቤቴ ስደርስ ሥራ ይጠብቀኛል። ገንዘብ ሳገኝ ሰራተኛ ብቀጥርም የሆነ ሰበብ እየፈለገ ሠራተኛዋ እንድትባረር ያደርጋል። እንደውም ድጋፍ እየተደረገልኝ እንዳልሆነ እንደውም ለማደናቀፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን እየተረዳሁ፤ እንዳላየ አልፋለሁ። የሆነ ቀን ላይ በቃ ምንም ድጋፍ አልፈልግም። እራሴን ራሴ ከደገፍኩ በቂዬ ነው ብዬ መደምደሚያ ላይ ደርሻለሁ።

በጣም ያለቀስኩባቸው ጊዜያቶች አሉ። ማንም ምን ሆነሽ ነው ብሎ ሳይጠይቀኝ ሲቀር፤ ለራሴ ያለሁት ራሴ ብቻ ነኝ ከማለት አልፌ በምንም ነገር እደራደራለሁ በትምህርቴ ላይ ግን አልደራደርም ብዬ ቀይ መስመር አሠመርኩ። ሰራተኛ አይኖርም ስባል ችግር የለም ብዬ ቀጥያለሁ። ትምህርት ቤት አትሔጂም ስባል ግን በምንም መልኩ አልሰማም አልኩ። በሌላ በኩል በየቀኑ ሥራ ከመያዝ ጀምሮ የማገኘው ውጤት የደመወዝ እድገቱ እና ሌላ ሌላውም እኔን የበለጠ እያስደሰተኝ ሃይል እየሰጠኝ ቀጠለ። ሌሎች ሰዎች ያላቸው እይታ እየተሻሻለ መጣ።

በአግባቡ ትልልቅ መፅሃፎችን አንብቤ ለመረዳት ሞከርኩኝ፤ ተሳካልኝ። በየቀኑ የቋንቋ ችግርም እየተቃለለልኝ መጣ። ከንባቤ በኋላ የተረዳሁት ሰዎች ዝቅ አድርገው ያዩኝ የነበረው እኔ ፈቅጄላቸው እንጂ እኔ ባልፈቅድላቸው ያ አይሆንም። አንዱ ለአንዱ እንዳልተፈጠረ ሁሉም ለየራሱ እንደተፈጠረ አንዱ ከሌላው ጋር በመልካም ፍቃዱ ተባብሮ መኖር እንዳለበት ተረዳሁ። ብቁ እና በቂ ከሆኑ ማንም ማንንም ምንም ማድረግ እንደማይችል አንብቤ አወቅሁ።

የሚጠቅመኝን እና የማይጠቅመኝን ለይቼ በማወቄ፣ አተኩሬ ራሴ ላይ በመስራቴ እና ጊዜዬን ምን ላይ ማባከን እንዳለብኝ በጊዜ ገባኝ። ስለዚህ ምንም ዓይነት ደቂቃ የሆነ ቦታ አላባክንም። ምክንያቱም እያንዳንዱ ደቂቃ ለእኔ ዋጋ አለው። የመስሪያ ቤት ምሳ ሰዓት ላይ እንኳን ከጓደኞቼ ጋር ሰዓቱን አላሳልፍም። የምበላው በላፕ ቶፕ እያነበብኩ ስለሆነ በእጄ አልበላም። በማንኪያ እየበላሁ አነባለሁ። የትኛውንም ደቂቃ በማይረባ ጉዳይ ማሳለፍ አልፈልግም።

አዲስ ዘመን፡- የመንግስት መስሪያ ቤት ሆነሽ እንዴት ነበር?

ወ/ሮ እየሩስ፡- የነበርኩበትን ተቋም በዝርዝር በሁለተኛው መፅሐፌ ላይ እገልፀዋለሁ። እንደውም ሁለተኛው መፅሐፌ በዚሁ የመንግስት ተቋም ላይ ያተኮረ ነው። የገባሁበት ተቋም ትልቅ የተባለ ትልልቅ ባለስልጣናት የሚሰሩበት እና የሚገኙበት ተቋም ነው። እኔ በዕውቀት ይበልጡኛል ብዬ ስላሰብኩኝ አብሬያቸው ለመነጋገር እንኳን በጣም እሰጋ ነበር። ጠረጴዛ ላይ ለእነርሱ የሚመጥን ሃሳብ ይዤ ለመቅረብ ከራሴ ጋር ተነጋግሬ ሙሉ ሆኜ ለመቅረብ ማንበብ ጀመርኩኝ።

ስለኢኮኖሚ፣ ስለፖለቲካ፣ ስለ ማህበራዊ ጉዳይ እና ስለሌሎችም በስፋት ሳነብ፤ እነርሱ የሚቀርቡት ሃሳብ አንሶ ታየኝ። እንደውም አንዳንዴ ሲሳሳቱ እስከማረም ደረስኩኝ። እኔ በየቀኑ ሳነብ በየቀኑ በራሴ ላይ መሻሻሎችን ማየት ጀመርኩ። ክፍተቴን ካወቅኩኝ ክፍተቴን ሳልሞላ ማደር አልችልም። ብዙ ሰዓት በጣም አነባለሁ። አንዳንድ ቀን ምሳዬን ራሱ በፌስታል ይዤ በማንኪያ በልቼ ፌስታሉን ቅርጫት ውስጥ ከትቼ ማንበቤን እቀጥላለሁ። አንዳንዴ ለምሳዬ ቆሎ ገዝቼ በሶፍት ላይ ቆሎዬን ዘርግፌ እየበላሁ አነባለሁ። ሻይ መጠጣት ቡና መጠጣት አቆምኩ። ውሃ እጠጣለሁ።

አዲስ ዘመን፡-ሃሳብን የማስተላለፍ ችግር አላጋጠመሽም?

ወ/ሮ እየሩስ፡– መጀመሪያ ከላይ እንደገለፅኩት ለጠረጴዛ የሚመጥን ሃሳብ አይኖረኝም ብዬ ምንም አልናገርም ነበር። ለሶስት ዓመት አካባቢ ማዳመጥ ብቻ ነበር። በሰርቪስ ከስራ ባልደረቦቼ ጋር ስሔድ በታብሌት መፅሃፍ አነባለሁ። መውረጃዬ ሲደርስ ሰው ይነግረኛል እንጂ፤ አንዳንዴ የት እንዳለሁ አላውቀውም ነበር። ምክንያቱም የምፈልገው ማንበብ ብቻ ነው። ሳነብ ደግሞ የማነበው ከልቤ ነው። መንገድ ላይም የምሔደው ያነበብኩትን እያሰላሰልኩ ነው። ሥራ ስሠራም ዩቲዩብ ከፍቼ ጥቁር አሜሪካን ሴቶች እንዴት ሕይወታቸውን እንደተጋፈጡ እሰማ ነበር።

ከዛ በኋላ ግን ተሰማም አልተሰማ፤ ለውጥ አመጣም አላመጣ የእኔ የምለውን ሃሳብ ማስተላለፍ ጀመርኩ። ባገኘሁት አጋጣሚ ባገኘሁት መድረኮች ላይ ሁሉ ዝም አልልም፤ እናገራለሁ። ለምን እንዲህ ሆነ እያልኩኝ መጠየቅ ጀመርኩ። ምክንያቱም እንደአገርም፣ ሃላፊነት እንደሚሰማው ሰውም ሆነ እንደአንዲት ሴት ስህተቶችን ማየት ጀመርኩ። እዛ ላይም ግን ራሴን የተሻለች ለማድረግ እሞክራለሁ። ሁል ጊዜ አልተኛም። ሁሌ አነባለሁ፤ ያገኘሁትን እውቀት አደንቃለሁ። ከዛ ከትንሽ ጊዜ በኋላ የማውቀውን ለማካፈል መሞከር ጀመርኩ። በተለይ እንደእኔ ዓይነት ከሆኑ ሴቶች ጋር ከወጣት ወንዶች ጋር እናወራለን። አንዳንዴ የማስበውን እፅፈዋለሁ። አሁን የታተመው መፅሐፍ የዛን ጊዜ መፅሐፍ ይሆናል ብዬ ባላስብም ስፅፍ የነበረው ተጠረቃቅሞ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ከመንግስት ሠራተኝነት እንዴት ወጣሽ?

ወ/ሮ እየሩስ፡– ማደግ መለወጥ የሚፈልግ ሰው ሁል ጊዜም የሚለውጠውን መንገድ ይፈልጋል። በመንግስት ሠራተኝነት የማመጣው ለውጥም ትንሽ እንደሆነ፤ ከግለሰብ አንፃር የሚኖረኝ መሻሻልም ጥቂት ሊሆን እንደሚችል ተገነዘብኩ። ስለዚህ ለአገሬም ለልጆቼም ሆነ ለራሴ የተሻልኩ ሆኜ ለመገኘት ራሴ ላይ እየሠራሁ መጣሁ። ከዛ በኋላ አጋጣሚዎችን መፈለግ እና እድሎችን ማማተር ጀመርኩ። ከሁለት ዓመት በላይ ስፈልግ ለትንሽ ደመወዝ ጭማሪ ሳይሆን ለመሠረታዊ ለውጥ በመትጋቴ አጋጣሚውም ወደ እኔ መጣ። በመጀመሪያ በአፍሪካ ሕብረት ሥራ መኖሩን ስሰማ ካለፍኩኝ ልሞክር ብዬ መስሪያ ቤቴን ጠየቅኩኝ፤ ፈቃድ ያስፈልግ ነበር። የበለጠ ለመማርም ራሴን የተሻለ ቦታ ላይ ለመድረስ በ2010 ዓ.ም ‹‹ተቋሙን እንድለቅ ፈቀዱልኝ። ›› አልኩ ተፈቀደልኝ።

አዲስ ዘመን፡- የአፍሪካ ሕብረት ተወዳድሮ መቀጠር ብዙዎች ለማሰብ ራሱ አይሞክሩትም አልፋለሁ ብሎ ማሰብስ ከባድ አይደለም?

ወ/ሮ እየሩስ፡– ትክክል ነሽ ቀላል አይደለም። ሌሎችም እንዲህ እንደሚያስቡ አውቃለሁ። እኔም እንደተወዳደርኩ አልፌ በአንድ ጊዜ አልተቀጠርኩም። ቅጥር መውጣቱን ስሰማ እንደማላልፍ ልቦናዬ እያወቀ ቢያንስ ፈተናውን ልየው ብዬ ተፈተንኩ። እናም እንደገመትኩት ወደቅኩ። ውጤቱ ገና ሳይገለፅ እንደምወድቅ አውቄያለሁ፤ ምክንያቱም ለምጠየቀው ጥያቄ ትክክለኛውን መልስ እየሰጠሁ አልነበረም። አንደኛ አንዳንዶቹ ጥያቄዎች እንደውም አልገቡኝም ነበር። ነገር ግን ተፈትኜ ስወጣ እንደምወድቅ ባውቅም በቀጣይ የጎደለኝን አሟልቼ ተወዳድሬ እንደምቀጠር እርግጠኛ ነበርኩ።

በአጋጣሚ አንድ ኖርዌ የኖረ ዘመዴ ቤቴ መጥቶ ሲያጣኝ የፈለገችውን ታድርግበት ብሎ ገንዘብ አስቀምጦልኝ ሔደ። ብዙ ሰዎች እንደሚያደርጉት ልብስ ወይም የቤት ቁስ አልገዛሁም። በግሌ የእንግሊዘኛ ቋንቋ አስተማሪ ቀጥሬ ተማርኩ። ቋንቋውን የማወቂያ ቴክኒክ ላይ ትኩረት በማድረግ ከሁለት ዓመት በኋላ ዕድሉ በድጋሚ ሲመጣ፤ እንደማልፍ እርግጠኛ ነበርኩ። እንደገመትኩት አልፌ ሥራ ጀመርኩኝ።

አዲስ ዘመን፡- አፍሪካ ህብረት ውስጥ መሥራት እንዴት ነው?

ወ/ሮ እየሩስ፡– ለስድስት ወር ያህል ልምምድ አድርጌያለሁ። ሁሉም የአንድ አገር ሰው አይደለም። ከተለያየ የአፍሪካ አገራት የመጡ ሰዎች ናቸው። የተለያየ የቋንቋ የተለያየ የሥራ ልምድ እና ባህል ያላቸው ናቸው። እርሱን መልመድ እና ለስራ በሚመች መልኩ መዋሃድ ያስፈልጋል። እኔ የዋና ሃላፊው አማካሪ በመሆኔ እና ዋና ሃላፊውም በተደጋጋሚ ለሥራ ከሀገር ስለሚወጣ በተከታታይ እንግዶችን አዘጋጃለሁ።

አዲስ ዘመን፡- በዓለም ዙሪያ የሴቶችን ፈተና እንዴት ታይዋለሽ?

ወ/ሮ እየሩስ፡– በእርግጥ ዓለም ለሴቶች ምቹ አይደለችም እንላለን። ዓለም እየተሠራችበት የመጣችበት ሂደት ለሴቶች ምቹ አይደለም። ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ቻይና ውስጥ እንደውም ሴት እንደዕቃ ትታይ ነበር። ባል ሚስቱን ከቤቱ እንደ አንድ ዕቃ ይቆጥራት ነበር። ስለዚህ አንድ ቻይናዊ ሚስቱን የመምታት አልፎ ተርፎ የመግደል መብት ነበረው። ሂደቱ በጣም ረዥም ነው። ሴት ብቁ እንዳልሆነች፤ ነፍሷ እንኳ የእርሷ እንዳልሆነ ይታሰብ ነበር።

ተፈጥሮ ወንዶችን ጠንካራ ሴቶችን ለስላሳ አድርጎ ሚዛኑን ጠብቆ ቢፈጥረንም፤ ዓለም የወንዶችን ጥንካሬ ወደ ሃይል ሲወስድ፤ የሴቶችን ልስላሴ ግን እንደስንፍና አትችልም ለማለት ዝቅ ለማድረግ ተጠቀመበት። ስለዚህ እርሷን እና ሃሳቧንም ዝቅ ማድረግ መጣ። ነገር ግን ሴት ተፈጥሮን የማስቀጠል ምንጭ ናት። ከሁለቱም የወጣ ዘር ተዋህዶ ሰው ሆኖ የሚወለደው ከሴት ነው። የተሻለ ትውልድ እንዲፈጠር ዋናውን ድርሻ የምትይዘው ሴት ናት። የዓለም ስርዓት ግን ሴቶችን በተሳሳተ መንገድ አስቀመጠ።

ሴት በሃይል የተሞላውን የወንድን ጥንካሬ የማርገብ አቅም አላት። ነገር ግን ዓለም የሰጣት ሥርዓት ያ አይደለም። ዓለም በጦርነት እና በዕልህ የተሞላው ሴት ባለመደመጧ ነው። ሃይማኖቶች የተለያየ አስተምሮ አላቸው። ወደ ታች እየወረደ ሲመጣ የሴት ድርሻ ምግብ ማብሰል ላይ ብቻ እንደሆነ ይታሰባል። ይህ ፍፁም የተሳሳተ ሃሳብ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም እጅግ አመሰግናለሁ።

ወ/ሮ እየሩስ፡- እኔም አክብራችሁ ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ።

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን የካቲት 29 /2016  ዓ.ም

Recommended For You