የሰው ልጅ ልዩነትን ያለ አንድነት፣ አንድነትን ያለ ልዩነት ሊገልፀው አይችልም፡፡ አንድነት የሚለው ንድፈ ሐሳብ በልዩ ልዩ ማንነቶች ውስጥ የጋራ ማንነት እንዳለ የሚገልፅ ነው፡፡ አንድነት የሚኖረውም ልዩነት ሲኖር ብቻ ነው፡፡
ኢትዮጵያዊ ውስጥ ኢትዮጵያዊነት እና ብሄርተኝነት ጎን ለጎን ያሉ ማንነቶች ናቸው፡፡ በአብዛኛው ከሃገራዊ ማንነት ይልቅ ብሄርተኝነት ጎላ ብሎ የሚታይበት ሁኔታ ላይ እንገኛለን፡፡ ኢትዮጵያዊነት እና ብሄረተኝነት ያላቸውን ተነፃፃሪ ነፃነት መሰረት አድርገንና አዋህደን ፖለቲካው ካልተመራ አንደኛውን መካድ ጥፋት እንጂ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት አያመጣም፡፡
ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት በአገሪቱ ውስጥ ካሉት ብሔር ብሄረሰቦች ጋር በጋራ መስተጋብር ያዳበሩት ታሪክ፣ ባህልና አስተሳሰብ መሆኑን ተቀብሎ በተለይ አሁን ባለው ዓለምአቀፋዊ ሁኔታ በአንድነት እሴቶቻችንን የማሳደግና የመጠበቅ ብቻ ሳይሆን ደህንነታቸውም አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል ተረድተን አንድነትን የሚመኝ፣ ለአንድነት የሚታገል፣ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብ መያዝ ይገባናል፡፡
የሕገ መንግሥታችን መግቢያ እንዲህ ይላል ‹‹እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሄረሰቦች ህዝቦች በሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላምና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገታችን እንዲፋጠን የራሳችንን ዕድል በራሳችን የመወሰን መብታችንን ተጠቅመን፣ በነፃ ፍላጎታችን፣ የሕግ የበላይነት፣ እና በራሳችን ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ በጋራ ለመገንባት ቆርጠን ተነስተናል»
ህገ መንግስቱ እንዲህ ቢልም በእስካሁኑ ጉዟችን ኢትዮጵያ ዘላቂ ልማት የሚከናወንባት፣ ዴሞክራሲ የሚገነባባት የሕግ የበላይነት የሚረጋገጥባትና ሰላም የሚሰፍንባት፣ከዚያም ከፍ ሲል አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ በጋራ ለመገንባት የሚያስችል ተግባር በቀጣይነት ማከናወን የሚቻልባት ለማድረግ እርግጠኞች አልሆንም፡፡ምክንያቱ ደግሞ አንድ ከሚያደርጉን ይልቅ የሚለያዩንን ጉዳዮች ስናብጠለጥል መክረማችንና ሊያለያዩን ለሚፈልጉ ፖለቲከኞች ምቹ ሁኔታን መፍጠራችን ነው፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን የጋራ እሴቶቻችንን መሰረት አድርገን የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ጥቅሞችንና እሴቶችን በእኩልነት በመጠበቅ አንድነታችንን በማጠናከር ልማታችንን፣ ደህንነታችንን እና ሰላማችንን ማረጋገጥ ሲገባን በልዩነት ውስጥ ያለውን አንድነታችንን በመዘንጋት ለውጫዊ ልዩነት ተንበርካኪ ሆነናል፡፡
ጠንካራ ኢትዮጵያዊነት ለመገንባት ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ያስፈልጋል፡፡በማያቋርጠው የኢትዮጵያዊነትና ብሔረተኝነት የተለያዩ አመለካከቶች መንፀባረቅ ቢችሉም በጉዳዮቹ ላይ በሰከነ መንፈስ ተወያይተን የሚበጀን የጋራ አስተሳሰብ መያዝ ይጠቅመናል እንጂ የሃሳብ የበላይነት ሊያገኝ የሚችለው የእኔ ብቻ ነው በሚል ፅንፍ መያዝ በልዩነታችን ውስጥ የሚኖረንን አንድነት ይሸረሽረዋል፡፡
ከቅኝ አገዛዝ ነፃ የወጡ የአፍሪካ አገራት በአስተሳሰባቸው ነፃነታቸው ባለመረጋገጡ የአውሮፓ/አሜሪካንን ህገ-መንግሥት እንዳለ ቀድተው፣ ስማቸውን ብቻ ቀይረው ሲገኙ እኛ ፈር ቀዳጅ የተባለውን ሕገ መንግሥት አርቅቀንና አፅድቀን አደጉ ተመነደጉ ለሚባሉትም ምሳሌ መሆናችን ሊያኮራን ይገባል፡፡
ያለፉት 27 ዓመታት ሕገ መንግሥቱን መሠረት ያደረገው የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታችን የተጓዘው ጉዞ አልጋ በአልጋ እንዳልሆነ ያጋጠሙትን ፈተናዎች በውል ተገንዝበናል፡፡ በተለይም ለኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች አንድነት ያለመጠናከር ዋናው ምክንያት ፖለቲከኞች ለሕዝብ አንድነት ከመሥራት ይልቅ ለመለያየት ተግተው መሥራታቸው ለ12 ጊዜ ያከበርናቸው የብሔር ብሔረሰቦች በዓላት ያስገኙልን ፋይዳ ሲመዘን ሚዛን የሚደፋ እንዳልሆነ ዛሬ የምናየው ያለመረጋጋት ምስክር ሆኗል፡፡
ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያዊ አንድነታችን ላይ ያጠላው የመለያየት አደጋ ተወግዶ በፅኑ መሠረት ላይ የቆመ አንድነት እንዲኖረን በልዩነታችን ውስጥ ያለው አንድነታችን ለምንወዳት አገራችንም ሆነ ለዜጎቿ ከምንም በላይ አስፈላጊነቱን ተገንዝበን ልንጠብቀው ይገባል፡፡
በዓድዋ የአፍሪካ እና የጥቁር ህዝቦች ተምሳሌት እንደሆንነው ሁሉ በ21ኛው ክፍለ ዘመንም የህሊና ነፃነታችንን በመጠበቅ ለመላው ዓለም ምሳሌ የሚሆን ፍቅርን ሰንቀን፣ ለልማት በጋራ ተነስተን፣ በችግሮቻችን ላይ በሰከነ መንፈስ ተወያይተንና መፍትሄ ፈልገን፣ ወደ ተሟላ ዴሞክራሲ ለመሸጋገር በአንድነታችን እንፅና፡፡