የዓድዋን ድል ታላቅነት በሰላምና በልማት ደግመን እናግዝፈው!

የዓድዋ ድል ከዓለም ታላላቅ የታሪክ ክስተቶች መካከል አንዱ ሲሆን፤ ለኢትዮጵያውያን የኩራትና የጀግንነት ምልክት፤ ለመላው ጥቁርና ጭቁኖች ደግሞ የነጻነትና እኩልነት ብርሃን ነው፡፡ ምክንያቱም ከዓድዋ ጦርነት በፊት በነጮችና ጥቁሮች መካከል የነበረው ተፈጥሯዊ ግንኙነት የተዛባ ነበር። ነጮቹ ራሳቸውን እንደ ገዢ ሲቆጠሩ፣ ጥቁሮቹን ደግሞ እንደ ተገዢ ሕዝብ ይቆጥሩት ነበር።

በዚህም ጥቁሮቹ ራሳቸውን የማስተዳደር አቅምና ችሎታ እንደሌላቸው፤ ይልቁንም ነጮች ጥቁሮችን የመግዛት ሙሉ መብት እንዳላቸው ያምኑ ነበር፡፡ በተጨማሪም ጥቁሮች ባህልና ታሪክ አልባ፤ እንዲሁም በተፈጥሯቸው ያልተሟሉ የሰው ዘሮች እንደሆኑ ተደርጎ ይነገር ነበር። እናም የዓድዋ ድል በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ይህን ሁሉ ቀይሯል፡፡

በአውሮፓውያን በኩል፣ ነጮች ይከተሉት የነበረው የተዛባ ትርክት “የነጭ ዘር የበላይነት” መንኮታኮትና እርቃኑን መቅረት የጀመረው በዓድዋ ድል ምክንያት ነው። ከዚህ ድል በኋላ ኢምፔሪያሊስቶች አፍሪካ ላይ የነበራቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጥቅሞች ተናግተዋል። የጭቆና መረባቸውም አቅም አጥቷል፡፡

ይህ ሁሉ ድል የተገኘው ጀግኖች ኢትዮጵያውያን አጥንታቸውን ከስክሰው፤ ደማቸውን አፍሰውና ሕይወታቸውን ገብረው በከፈሉት መስዋዕትነት ነው፡፡ ድሉ ግን ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ጥቁር ሕዝቦች እኩልነት የተከፈለ የደም ዋጋ ነው። ለዚህም ነው የዓድዋ ድል በዓል በሰው ልጆች ነፃነትና እኩልነት የሚያምን ማንኛውም የሰው ዘር ሊያከብረውና ሊዘክረው የሚገባ ክስተት ሆኖ የዘለቀው፡፡

ኢትዮጵያ ቀደምትና ታሪካዊት ሀገር፤ ሕዝቧም የዚህ ታላቅ ድል ባለቤት ነው፡፡ ይህ ጀግና ሕዝብ የብሄር፤ የሃይማኖት፣ የጾታ እና ሌሎች ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ልዩነቶች ሳይበግሩት በአንድነት በመትመም ቅኝ ገዢዎችን አሳፍሮ መልሷል፡፡ ለሉዓላዊነቱና ለነጻነቱ እረፍት የማያውቀው ይህ ሕዝብ ታዲያ፤ ሀገሩ የቅኝ ግዛት ጥማት ባለው ኃይል ልትወረር መሆኑን በሰማበት ቅጽበት ቀፎ እንደተነካበት ንብ ከአራቱም ማዕዘናት በአንድነት ተሰባስቦ ወረራውን ቀልብሷል፤ ሀገሩን ከወራሪ ታድጎም የድል ታሪኩን ጽፏል፡፡ በዚህም ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የይቻላልን ሰብዕና አጎናጽፎ ለነጻነታቸው እንዲታገሉ ዓርአያ ሆኗቸዋል፡፡

የዚህ ባለታሪክ ትውልድ ልጆች የሆንነው እኛ የዛሬው ትውልዶችም፤ ከቀደምቶቻችን ተግባር ልንቀስመው ከሚገባው ዘርፈ ብዙ ትምህርት ባለፈ፤ ለውለታቸው ልንከፍል የሚገባን፣ ሀገርና ሕዝብን ከዛሬ በማሻገር ሂደት ውስጥ ልንወጣ የሚገባን ብዙ የቤት ሥራ አለ፡፡ ለምሳሌ፣ ለሀገር ሉዓላዊነትና ለግዛት አንድነት የሕይወት መስዋዕትነት የከፈሉ ጀግኖች ውለታ ከሚመለስባቸው ጉዳዮች አንዱ፤ የኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን ሰላም ማስጠበቅ፣ ልማትን እውን ማድረግ በመቻል ውስጥ ነው፡፡

ለዚህ ደግሞ ከእኛ የጦር ሜዳ አርበኛ መሆን አይደለም የሚጠበቅብን፤ የሰላም እና የልማት መስኩ አርበኛ መሆን መሆን እንጂ፡፡ በተለይም ዛሬ ላይ በተለያዩ ምክንያቶች በሰላም ችግር እየተፈተነች ላለች ሀገራችን እና ሰላምን ለሚሻው ሕዝባችን የሰላም አምባሳደር በመሆን በመሥራት የአባቶቻችንን መስዋዕትነት ለማጽናት የበኩላችንን ጥረት ልናደርግ ይገባል፡፡

ምክንያቱም እኛ ኢትዮጵያውያን ላለፉት ሃምሳ እና ስድሳ ዓመታት ከአንድነት ይልቅ የልዩነት ጉዳዮቻችንን እያጎላን ሕብረታችንን ለማላላት ጥረናል፡፡ በዚህም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሰላማችንን በገዛ ራሳችን እያጠፋን መጥተናል፡፡ በመሆኑም ዛሬ ላይ የግጭት፣ የጦርነት፣ ያለመግባባት ታሪካችን ተዘግቶ በጋራ ታሪኮቻችን ላይ የምንግባባ፤ ለጋራ ሀገራችን የምንተጋ፤ ለልጆቻችንም የበለጸገች ኢትዮጵያን ለማውረስ የጋራ እሳቤ የምናኖር የለውጥ ትውልድ መሆን ይገባናል፡፡

በአባቶቻችንና እናቶቻችን ተጋድሎ ያገኘነው ኩራትና ነጻነታችን ሙሉ እንዲሆን ኢትዮጵያን በሁሉም መስክ ማበልጸግ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የተጀመሩ የብልጽግና አውታሮችን ማጠናቀቅ፤ አዳዲስ የትውልዱን ታሪክ የሚያደምቁ ሥራዎችን መጀመር ይጠይቃል፡፡ ለአብነት፣ ይህ ትውልድ ታላቁን የዓባይ ግድብ ሰርቶ እያገባደደ ነው፡ ፡ ይህን የሀገር ኩራት የሆነ ግድብ አጠናቆ ለሀገር ብሎም ለአፍሪካ ብርሃን ማጎናጸፍ የዚህ ትውልድ አንዱ አደራ ነው፡፡

በግብርና ልማት በተለይም በስንዴ የተገኘውን አኩሪ እንቅስቃሴ ዘላቂ ማድረግና ከኢትዮጵያም አልፎ አፍሪካን መመገብ ሌላው የዚህ ትውልድ ዐሻራ ሊሆን ይገባል፡፡ አረንጓዴ ዐሻራ በማኖር ረገድ ኢትዮጵያውያን ባለፉት አምስት ዓመታት አዲስ ታሪክ በመጻፍ ላይ ይገኛሉ፡፡

ይህ አኩሪ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያን ልማትና ዕድገት የማይወዱ አካላት ሊያጣጥሉት ቢሞክሩም፤ ተግባሩ የሚደበቅ አይደለምና ኢትዮጵያ በተሳተፈችባቸው መድረኮች ሁሉ በውጤታማነቱ እየተወሳ ይገኛል፡፡ ስለዚህም ትውልዱ ይህንን አንጻባራቂ እንቅስቃሴ ከዳር ማድረስና ኢትዮጵያን ብሎም አፍሪካን አረንጓዴ ማልበስ ቀጣይ የቤት ሥራው ሊሆን ይገባል፡፡

በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን ቀደም ሲል በዓድዋም ሆነ በሌሎች የጦር አውድማዎች የሀገርን ዳር ድንበር አላስደፍርም በማለት ደማቸውን በማፍሰስ፤ አጥንታቸውን በመከስከስ ውድ ሕይወታቸውን መስዋዕት እያደረጉ ሀገርን በነጻነት አጽንተው ኖረዋል፡፡ የአሁኑ ትውልድም የሀገሩን ዳርድንበርና ሉዓላዊነት ከመጠበቅ ጎን ለጎን በሰላም እና በልማቱም መስክ ሀገሪቱን ወደ ፊት ሊያራምዱ የሚያስችሉ ተግባራትን በመፈጸም ነጻነቷን ምሉዕ በማድረግ የቀደምት አባቶችን ፈለግ ሊከተል፤ እንደ ዓድዋም የሚዘከር የራሱን ታሪክ ሊያኖር ይገባል፡፡

አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You