19ኛው የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና በስኮትላንድ ግላስኮ ከነገ ጀምሮ ለሦስት ቀናት ይካሄዳል፡፡ የአጭርና መካከለኛ ርቀት ሩጫ እና የሜዳ ተግባራት ፉክክሮች በሚስተናገዱበት ቻምፒዮና በርካታ የኦሊምፒክ፣ የዓለም ቻምፒዮና እንዲሁም የውድድሩ የቀድሞ ባለድሎች ይሳተፉበታል፡፡ በዚህ ቻምፒዮና ከሚካፈሉት 133 ሀገሮች መካከል በተፎካካሪነታቸውና በርካታ የወርቅ ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ቀዳሚ የሆኑት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ዘንድሮም ትልቅ የአሸናፊነት ግምት አግኝተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በቻምፒዮናው በጥቂት ፉክክሮች ብቻ ተካፍላ በውጤታማነት ከምታጠናቅቅባቸው መድረኮች አንዱ የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና ነው፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በሰርቢያ ቤልግሬድ አስተናጋጅነት በተካሄደው 18ኛው ቻምፒዮና ኢትዮጵያ 4 የወርቅ፣ 3 የብር እና 2 የነሐስ በጥቅሉ 9 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ አሜሪካና ቤልጂየምን አስከትላ ከዓለም አንደኛ ሆና ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ነገ በሚጀምረው የዘንድሮው ቻምፒዮና ላይም ይህንኑ ድል በማስቀጠል በርካታ ሜዳሊያ ይሰበስባሉ ተብለው ይጠበቃሉ፡፡ ከቀናት በፊት በተጠናቀቀው የዓለም የቤት ውስጥ የዙር ውድድሮች ላይ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አስደናቂ ውጤት ሲያስመዘግቡ የቆዩ ሲሆን፤ ከሳምንት በላይ በዘለቀው የብሔራዊ ቡድን ዝግጅትም አሸናፊነታቸው እንደሚቀጥል ተስፋ ተደርጓል፡፡
በውድድሩ ላይ ከሚካፈሉት 651 አትሌቶች መካከል 331 የሚሆኑት ሴቶች ሲሆኑ፣ 320ው ደግሞ ወንዶች ናቸው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 18ቱ በቤልግሬዱ ውድድር ላይ ቻምፒዮን የነበሩ ስመጥር አትሌቶች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያን ወክለው በውድድሩ ላይ ከሚካፈሉ አትሌቶች መካከልም በሁለቱም ጾታ በ1ሺ500 እና 3ሺ ሜትር ቻምፒዮናዎች (ሳሙኤል ተፈራ፣ ጉዳፍ ጸጋይ፣ ሰለሞን ባረጋ፣ ለምለም ኃይሉ) በድጋሚ ግላስኮ ላይ ለድል ይሮጣሉ፡፡ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በቻምፒዮናው በ5 ወንድ እና 8 ሴት አትሌቶች ስትወከል፤ 800 ሜትር፣ 1ሺ500 ሜትር እና 3ሺ ሜትር ርቀቶች ጠንካራ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በሴቶች 800 ሜትር ሃብታም ዓለሙ እና ጽጌ ድጉማ ኢትዮጵያን ወክለው የሚሮጡ ሲሆን፤ ለሜዳሊያ ከሚፎካከሩ አትሌቶች መካከል ይገኙበታል፡፡ በተለይም በዚህ ርቀት ከፍተኛ ልምድ ያካበተችው አትሌት ሃብታም አለሙ ለወርቅ ሜዳሊያ የቀረበ ቅድመ ግምት አግኝታለች፡፡ አትሌቷ በሦስት የቤት ውስጥ ቻምፒዮና የተሳትፎ ታሪክ ያላት ሲሆን፤ እ.አ.አ 2016 ተሳትፎዋ ስድስተኛ ደረጃን ይዛ ስታጠናቅቅ፣ እ.አ.አ በ2018 ሁለተኛ እንዲሁም በ2022 ሰባተኛ ሆና ፈጽማለች፡፡ በቅርቡ በተካሄደው የወርቅ ደረጃ ያለው የሌቪን የቤት ውስጥ የዙር ውድድር አሸናፊ የነበረችው ሃብታም 1:57.86 የሆነ የግሏን ሰዓት አስመዝግባ ነበር። ይኸውም በጥሩ አቋም ላይ የምትገኝና ለአሸናፊነት የሚያበቃት መሆኑን ያመላክታል፡፡ በዚህ ርቀት በወንዶች በኩል አትሌት ኤፍሬም መኮንን በብቸኝነት ኢትዮጵያን ይወክላል፡፡
በሁለቱም ጾታ ኢትዮጵያ በርካታ ሜዳሊያ ትሰበስባለች ተብሎ ከሚጠበቁ ርቀቶች መካከል አንዱ የ1ሺ500 ሜትር ውድድር ነው፡፡ ቤልግሬድ ላይ ኢትዮጵያ ቻምፒዮን መሆኗን ተከትሎ ሦስት አትሌቶችን የማሳተፍ ዕድል ባገኘችበት የሴቶች ውድድር፤ አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ፣ ድርቤ ወልተጂ እና ብርቄ ኃየሎም ይፎካከራሉ፡፡ እጅግ ጠንካራ የተባለው ይህ ቡድንም እንደተለመደው ሜዳሊያዎቹን ጠራርጎ እንደሚወስድ የተገመተ ሲሆን፤ ቤልግሬድ ላይ በ800 ሜትር የብር ሜዳሊያ ባለቤት የነበረችው ፍሬወይኒ ጉዳፍን ተክታ ድል እንደምታስመዘግብ ትጠበቃለች፡፡ አትሌቷ የተያዘውን የውድድር ዓመት የወርቅ ደረጃ ባላቸው የኦስትራቫ እና ሌቪን የቤት ውስጥ የዙር ውድድሮች በአንድ ማይል እና 1ሺ500 ሜትር አሸናፊ ነበረች፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በ3ሺ ሜትር የነሐስ ባለቤት የነበረችው እጅጋየሁ ታዬም ዘንድሮ ርቀቷን ቀይራ ከሀገሯ ልጆች ጋር ሜዳሊያ ለማጥለቅ ትሮጣለች፡፡
ጠንካራ ፉክክር እንደሚያስተናግድ በሚጠበቀው የወንዶች 1ሺ500 ሜትር ርቀትም ቻምፒዮኑ ሳሙኤል ተፈራ ኢትዮጵያን በድጋሚ ባለድል ለማድረግ ይፋለማል፡፡ እ.አ.አ በ2018 በርሚንግሃም ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በቻምፒዮናው የተሳተፈው የ24 ዓመቱ አትሌት አሸናፊ መሆኑን ተከትሎ በ2022 ቻምፒዮና በቀጥታ የመሳተፍ ዕድል ሲያስገኝለት በድጋሚ የወርቅ ሜዳሊያውን ማጥለቅም ችሏል፡፡ ግላስኮ ላይም ለሦስተኛ ጊዜ የኢትዮጵያን ባንዲራ ለማውለብለብ ከወጣቱ አትሌት ቢኒያም መሃሪ ጋር የሚሰለፍ ይሆናል፡፡
በአትሌቲክስ ቤተሰቡ ዘንድ እጅግ በጉጉት የሚጠበቀው የ3ሺ ሜትር ርቀትም በሁለቱም ጾታ በኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሸናፊነት ይጠናቀቃል የሚለው ሚዛን የሚደፋ ሆኗል፡፡ በቤልግሬድ የ1ሺ500 ሜትር ቻምፒዮን የነበረችው ጠንካራዋ አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ ቡድኑን የምትመራ ሲሆን፤ ፉክክሯ ከሀገሯ ልጅ በ2022 የ3ሺ ሜትር ቻምፒዮና ለምለም ኃይሉ ጋር ይሆናል።
በወንዶች የ3ሺ ሜትር ርቀት የኦሊምፒክና የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮኑ ሰለሞን ባረጋ የኢትዮጵያን ቡድን ይመራል፡፡ ቡድኑ በቤልግሬድ ቻምፒዮና መሆኑን ተከትሎ ሦስት አትሌቶችን የማሳተፍ ዕድል ቢያገኝም አትሌት ጥላሁን ኃይሌ ከቡድኑ ጋር አለመጓዙ ታውቋል፡፡ በመሆኑም በርቀቱ ውጤታማ የሆነው ሰለሞን ከሌላኛው ጠንካራ አትሌት ጌትነት ዋለ ጋር ለአሸናፊነት ይፎካከራሉ፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን የካቲት 21/2016 ዓ.ም