«በአፈጣጠሬ ምክንያት ብዙ ፈተናዎችን ለመጋፈጥ ተገድጃለሁ» -ሰርካለም አየለ

ገና በልጅነት ዕድሜዋ ነበር የሕይወት ፈተናዋ የጀመረው። እናትና አባቷ ከወለዷቸው ስምንት ልጆች ስድስተኛ ሆና የተወለደችው ልጅ ከሌሎች ሰዎችና ከእህት ወንድሞቿ የተለየ አፈጣጠር እንዳላት ስትረዳ ነበር ̋ለምን እንደዚህ ሆንኩ ? ̋ እያለች መጠየቅ የጀመረችው።

ልጆቹም ከእነሱ ልዩ መሆኗን ሲመለከቱ ̋አጭሯ ልጅ፤ አጭሯ ልጅ ̋ እያሉ ከመጠቋቆማቸው በላይም ትልልቅ ሰዎች ̋ እናቷ አጭር ሰው አይታ ስቃ ነው፤ የወላጆቿ ሀጥያት ነው፤ እርግማን ነው ̋ የሚሉ አስተያየቶችን መስጠታቸው ቤተሰቦቿ የተለየ በደል እንደበደሏት እንድታስብ አድርጎ እንዳሳደጋት ትናገራለች።

በልጅነቷ የተለያዩ አስተያቶች መስማቷም ሆነ አንድ እግሯ ታማሚ ሆኖ መፈጠሩ በጣም ያስከፋት የነበረ ቢሆንም ስታድግ ግን ̋ ያጠረው ቁመቴ፤ የተንጋደደው እግሬ እንጂ ጭንቅላቴ አይደለም ̋ በማለት በጥንካሬ መሞከር ያለባትን ነገር በሙሉ እየሞከረች ሕይወቷን በስኬት ለመምራት ትታትራለች።

ሰርካለም አየለ ትበላለች። ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ቀበና አካባቢ ነበር። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን በኮኮበ ፅባህ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትላለች። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በዳግማዊ ምኒሊክ ሁለተኛ ድረጃ ትምህርት ቤት አጠናቃለች። በመቀጠል በእንጦጦ ቴክኒክና ሞያ ኮሌጅ በደረጃ አራት የሆቴል ማኔጅመንት ኮርስ ወስዳ ተመርቃለች። ሆቴል ማኔጅመንት ብትማርም እንኳን ካላት ተፈጥሮ የተነሳ ስራ የማግኘት እድሏ አናሳ የነበረ መሆኑን ትናገራለች። በተማረችበት ዘርፍ የስራ እድል ማግኘት የማይታሰብ ቅዥት የሆነባት ይች ልጅ አመራጮችን ለማግኘት ብዙ ቦታ መቃኘቷን ታስታውሳለች።

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች በድሎት ውስጥ ሳይሆን በከፍተኛ የኑሮ ውጣ ውረድ ውስጥ የሚኖሩ ናቸው የምትለው ሰርካለም በሀገሪቱ ዘጠና አምስት በመቶ የሚሆኑ የአካል ጉዳተኞች ከድህነት ወለል በታች የሚገኙ መሆናቸውን፣ ዘጠና ስምንት በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ሥራ መቀጠር አለመቻላቸው በጥናት መረጋገጡንም ጭምር ታነሳላች። ይህም የሆነው ለሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል እኩል የስራ መደላድል ባለመፈጠሩ መሆኑን ታብራራለች። አብዛኞቹ አካል ጉዳተኞች ‹‹በሥራ ሥምሪት፣ በተሳትፎ፣ በትምህርት፣ በፖለቲካዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ጭምር የተካተቱ አይደሉም›› የምትለው ሰርኬ፣ ‹‹በአገራችን አካል ጉዳተኞች በሁሉም የልማት መስኮች ማካተት ያልተለመደና መለመድ ያለበት ወቅታዊ ተግባር ነው፡፡ ይህ ሲሆን ብቻ ነው የሠለጠነና ዘመናዊ ኅብረተሰብ የሚለው ስያሜ ባለቤት መሆን የምንችለው፤›› ብላለች።

በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት የሥራ ሥምሪቶች አካል ጉዳተኞችን በልዩ ሁኔታ የሚያስተናግዱበት አመቺ ሁኔታ እንደሌላቸው የምታነሳው ሰርኬ የቅጥር መሥፈርቶቹ ‹‹ዝሆንና ጦጣን እኩል ዛፍ ላይ እንዲወጡ የማዘዝ ያህል ነው›› ትላለች። ለይምሰል የሚመስል ለአካል ጉዳተኞች ይህ መደረግ አለበት የሚል አቋም ይዘው የግብር ይውጣ የሚሰሩ አካላት በርካታ ናቸው ትላለች። ይህ በመሆኑ ምክንያት አካል ጉዳተኞች ላይ የሚደርሰው ተደራራቢ ችግር መፍትሄ ሳያገኝ ቆይቷል ትላለች።

ለዚህም መፍትሄ ነው የምትለውን ሀሳብ ሰርኬ ስታስቀምጥ፤ በየተቋማቱ ያሉ የሥራ ድርሻዎችን በመለየት ለአካል ጉዳተኛ ምቹ በሆኑ ሥራዎች እንዲሰማሩ ማድረግ። አካል ጉዳተኞችን ማሳተፍ የመንግሥትና የበጎ አድራጎት ተቋማት ኃላፊነት ብቻ ማድረግ የተሳሳተ ግንዛቤ በመሆኑ፣ በግል ቢዝነስ ተቋማት፣ በሆቴሎች፣ በባንኮችና በፋብሪካዎች መቅጠርና ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል ትለናለች።

በተማረችበት የትምህርት ዘርፍ ስራ ማግኘት የተሰናት አካል ጉዳትና የቁመት ማጠር ያላት ወጣት አማራጯን ወደ አካል ጉዳተኞች ስፖርት አዙራ ፓራ ኦሎምፒክ ላይ በመሳተፍ አዲስ አበባን ወክላ የተለያዩ ውድደሮችን አሸንፋለች። ስፖርቱ ሁሉንም የአካል ጉዳት አይነቶች ያካትት ስለነበር ከሰዎች ጋር ያላትን ግንኙነት በማጠናከር ትናንት ስለ እራሷ የሚሰማት ስሜት ተቀይሮ ሁሉን ለማድረግ የምትችል ጠንካራ በራሷ የምትተማመን ወጣት እንድትሆን እንዳደረጋት ትናገራለች።

የራስ መተማመኗ ራሷን የመቀበሏ ሁኔታ ከተስተካከለ በኋላ ከስፖርቱ ባሻገር ሌሎች አማራጮቸን መመልከት ጀመረች። በዚህ አጋጣሚ ነው እንግዲህ አሜሪካ ኤምባሲ ባዘጋጀው የአካል ጉዳተኞችን የሚያካትት የፋሽን ትርኢት ላይ ለመሳተፍ የቻለችው። የአሜሪካ ኤምባሲ አካል ጉዳተኞች ፋሽን ሾ ላይ 28 አካል ጉዳተኞች በርካታ ጉዳት አልባዎች፤ ፋሽን ዲዛይነሮች የተካተቱበት ስራ ላይ ከተሳተፈች በኋላ በርካታ አካል ጉዳተኞች የተሳተፉበት ፋሽን ሾዎችን በመስራት ራሷን ለማውጣት ታግላለች። ለእለት ኑሮዋ የሚሆኑ እነዚህን ስራዎች ከመስራቷም ባሻገር ቡና ጠጡ እየሰራች ኑሮዋን ለማሸነፍ ትጥራለች።

እንደ ሰርኬ ገለፃ አካል ጉዳተኞች ሥራ ለመቅጠር ያለው ዕድል ጠባብ በመሆኑ፣ የራሳቸውን ስራ ፈጥረው ጠንክረው በመሥራት ከሌሎች ጋር እኩል ለመሆን በትጋት መስራት አለባቸው። እነዚህ የሕብረተሰብ ከፍሎች በግል ዘርፎች ማሳተፍ ምርታማነት እንዲጨምር ያደርጋሉ፡፡ ስለዚህ ቅጥርን ከመጠበቅ ይልቅ ስራ ፈጣሪነት ላይ ማተኮርም ሌላው አማራጭ ነው ትላለች፡፡ ሀገሪቱ የዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ኮንቬንሽንን ከ12 ዓመታት በፊት ተቀብላ የፈረመች ሲሆን፣ የአካል ጉዳተኞች የሥራ ሥምሪት አዋጅ፣ የሕንፃ አዋጅ፣ የቀረጥ ነፃ መመሪያና አካል ጉዳተኞችን ከ60 በመቶ በላይ የቀጣሪ ድርጅት ከታክስና ቀረጥ ነፃ መሆን አለበት የሚሉት በአገር ውስጥ መውጣታቸው እንደ ጥሩ ጎን ታነሳለች።

̋አካል ጉዳተኞች አይችሉም በሰዎች ተደግፈው ነው የሚቆሙት የሚለውን አመለካከት አልቀበለም፤ ̋ የምትለው ሰርካለም ̋የምኖረው ኮንዶሚኒየም ቤት ነው። ቁመቴ ቢያጥርም ልብስ አጥቤ የማሰጣው እራሴው ነኝ፤ ከኪችን ካብኔት እቃ ማውጣት ማስገባትም የራሴ ስራ ነው፤ ወንበር ላይ ቆሜም ቢሆን አደርገዋለሁ ̋ ጓዳ ድረስ ሰውን ይዞ ከመግባት አቅም የቻለውን ጥረት አድርጎ የተሰጠን ተፈጥሮ በፀጋ መቀበል ተገቢ ነው ትላለች። ̋ብዙ ነገሮችን ሰዎች ላይ ሳልደገፍ በራሴ ማድረግ የሚገባኝን አደርጋለሁ። ሰርካለም ለሌሎች አካል ጉዳተኞች ምን ታስተምራለች ቢባል ሰው ጉዳቱ አካሉ ላይ እንጂ ጭንቅላቱ ላይ አለመሆኑን ተረድቶ በጭንቅላቱ መስራት የሚገባውን ስራ መሰራት ይችላል፡፡ እኔም ያንን ማስተማር ነው የምፈልገው ̋ ብላለች።

አካል ጉዳተኞች ትዳር መመሥረት፣ ልጆችን መውለድና ቤተሰብ ማፍራት ከባድ ስለሆነ እንዲህ አይነት ሃሳብ ማሰብ እንደማይኖርባት ብዙ ሰዎች አስተያየቶች ሰጥተዋት የነበረና ብዙዎችም በተለያየ መልኩ ተቃውመዋት እንደነበር ትናገራለች። እሷ ግን ለፍቅርም ይሁን ለመውለድ አእምሮ ደህና ይሁን እንጂ ጉዳት አያግድም በማለት አሁን ላይ የአንዲት ሴት እናት ለመሆንም ታድላለች። አካል ጉዳተኝነት በራሱ የሚፈጥረው ጫና እንዳለ ሆኖ በተለይ ሴት አካል ጉዳተኞች ላይ የሚደርሰው ተፅዕኖ ቀላል የማይባል መሆኑን የምትናገረው ሰርካለም፤ ለዚህም በጤናና ሥነ-ተዋልዶ ዙሪያ ያልተዳሰሱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ ትናገራለች።

በተለያዩ ጊዜዎች የሚሰሩ መሠረተ ልማቶች አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ አለማድረጋቸውን የሚያሳዝናት ጉዳይ መሆኑን የምትናገረው ሰርካለም መንገድ፣ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት፣ የመዝናኛ ሥፍራዎች፣ የተለያዩ ሕንፃዎች ወዘተ.) አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ አድርገው ባለመገንባታቸው እንደ ሌላው ሰው ውሎ ለመግባት አስቸጋሪ መሆኑን ታስረዳለች። በተለይ እንደሷ አይነት ጉዳቶች ያላቸው መሮጥ የማይችሉ፤ እንቅስቃሴ የሚከብዳቸውን ምቹ ሕንፃዎችና ምቹ መንገዶች በማሰራት የተመቸ ከተማ ውስጥ እንዲኖሩ መድረግ ተገቢ ነው ትላለች።

በሕይወት ውስጥ ምንም አይነት ፈተና ቢኖር ተስፋ መቁረጥ አይገባም። ሕይወት ሁልጊዜም ሁለት አማራጭን የምትሰጥ በመሆኗ ይሆናል ወይም አይሆንም የምንለውን አማራጭ ሀሳብ ይዞ እስከ መጨረሻው መታገል ሰው ያለ ምንም ተስፋ መቁረጥ እንዲጓዝ የሚያስችለው መሆኑን ታስረዳለች። የሚገርመው አንድ ጉዳት አልባ ሰው አካል ጉዳተኛን አግብቶ ቢገኝ ሰዎች ምኗን አይተህ ነው ሀብት ሰላላት ነው ወይስ ምንድነው የሚሉ ሰዎች አሉ። ሀብት ንብረት ከሰው በኋላ የመጡ ናቸው። ከሀብትና ንብረት በላይ አስተሳሰብ የሰው ስብዕና መቅደም ይኖርበታል ትላለች።

̋እኔ ግን ሰርካለም አጭሯ እንዲህ ናት ሲባል ነው። አሁን ልጄን ለብቻ ነው የማሳድጋት። የወልድኩ በኦፕራሲዮን ሰለነበረና በጣም ታምሜ ስለነበር ልጄ ጡት አትጠባም። ለዚህም የዱቄት ወተት እየገዙ ማጥባት ቸግሮኛል። እርግዝና ብዙም ሳያሰቃየኝ በዘጠኝ ወር ከአስር ቀን ብወልድም ከወሊድ በኋላ በተፈጠረብኝ ህመም እንደ ልቤ ተንቀሳቅሼ የቀደመ ስራዬን መሰራት አልቻልኩም። በዚህም ምክንያት በጊዜያዊነት እርዳታ ያስፈልገኛል ̋ ትላለች። አካል ጉዳት ብሎም እናትነት አሁን ደግሞ ጊዜያዊ የጤና ችግር የገጠማት፤ ታትራ እራሷን ከድህነት ለማውጣት የምትታገለውን ይህችን ሴት ሰው በሚችለው ልክ ቢረዳት እንደምትፈልግ ትናገራለች።

ከዚህ ቀደም በተለያየ መልኩ ለአላማዋ መሳካት ከጎኗ የቆሙትን በሙሉ የምታመሰግነው ሰርካለም በተለይም ወይዘሮ መሰረት አዛገን የመሰረት በጎ አድራጎት ድርጅት መስራችን፤ እውን በጎ አድራጎት ድርጅት መስራች እና ባለቤት ወይዘሮ ማርታ ደጀኔ ስላደረጉልኝ ነገር በሙሉ ከልብ አመሰግናለሁ ብላለች። ሰርካለም አሁን ላይ ወቅታዊ ችግር ቢገጥማትም ትናንት ካሳለፈችው ፈታና፤ ከተሻገረችው ችግር አይበልጥምና በፅናት ታግላ እንደምታሸንፈው ነግራን የነበረንን ቆይታ አጠናቀናል። ቸር ይግጠመን።

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን የካቲት 19/2016 ዓ.ም

Recommended For You