አዲስ አበባ፡– የዲጂታል ኢኮኖሚን በመገንባት የማህበረሰቡን ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ መሆናቸው የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ።
በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የአይሲቲ እና ዲጂታል ኢኮኖሚ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ይሹሩን ዓለማየሁ (ዶ/ር) የዲጂታል ኢትዮጵያ ሳምንትን አስመልክቶ ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተናገሩት፤ በአሁኑ ጊዜ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዓለምን እየተቆጣጠረ ይገኛል። በኢትዮጵያም መንግሥት የዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም ኢኮኖሚውን ለማሳደግና የማህበረሰቡን ጥያቄ ለመመለስ የዲጂታል 2025 ስትራቴጂ ነድፎ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል ብለዋል።
በርካታ የአፍሪካ ሀገራትም የዲጂታል ቴክኖሎጂ በመጠቀም አገልግሎታቸውን በቀላልና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ ተደራሽ እያደረጉ ናቸው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ኢትዮጵያም በዲጂታል 2025 ስትራቴጂ ከተቀመጡት አንኳር ጉዳዮች መካከል የዲጂታል መሠረተ ልማት በመዘርጋት፣ የኢንተርኔት ተደራሽነት ማስፋት፤ የዳታ ማእከላትን መገንባት እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል፡፡
እንዲሁም ዲጂታል ቴክኖሎጂ ለመጠቀም የዲጂታል መታወቂያ ማዘጋጀትና የሳይበር ደህንነት የማስጠበቅ፣ የኢ- ኮሜርስና የመንግሥትን አገልግሎት ዲጂታል በሆነ መንገድ ተደራሽ ማድረግ እንዲሁም በዘርፉ አስቻይ ምህዳር ለመፍጠር በክህሎት በፋይናንስና በሕግ ማእቀፍ ረገድ ዝግጅት ማድረግ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በእዚህ ረገድም እስካሁን በተከናወኑ በርካታ ተግባራት ጠንካራ ኢኮኖሚ ያላት የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ይገኛል ብለዋል።
የዲጂታል ሳምንት ዝግጅትም ለማህበረሰቡ የኢትዮጵያን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ሥራዎች ለማስተዋወቅ፤ ብሎም ኅበረተሰቡ የዲጂታል ቴክኖ ሎጂዎችን እንዲጠቀሙ ግንዛቤን በመፍጠር የዲጂታል ኢኮኖሚ እድገትን ለማፋጠን የሚጠቅም መሆኑን ገልጸው፤ መንግሥት የዲጂታል ቴክኖሎጂን ለልማት እና ለዕድገት በማዋል የማህበረሰቡን የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ቀላልና ቀልጣፋ ለማድረግ እያከናወናቸው ስላሉ ዘርፈ-ብዙ እንቅስቃሴዎች የሚቀርቡበት መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በተጨማሪ የኢትዮጵያን የዲጂታል ሽግግር ጉዞ ገፅታዎችን የሚያጎሉ የተለያዩ አሳታፊ ተግባራትና ትምህርታዊ ዝግጅቶች የሚካሄዱበት ሲሆን፤ ማህበረሰቡ በዚህ ረገድ የተሰሩ ሥራዎችን በመከታተል መጠቀም የሚጠበቅበት መሆኑን አመልክተዋል።
የመጀመሪያው የዲጂታል ኢትዮጵያ ሳምንት በሀገር አቀፍ ደረጃ “የጋራ ጥረታችን ለዲጂታል ኢትዮጵያችን” በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ ከየካቲት 18 እስከ 22 ቀን 2016 ዓ.ም በተለያዩ መርሀ ግብሮች የሚከበር ሲሆን፤ ከሁሉም ክልል የሚመለከታቸው አካላትና የፌዴራል ተቋማት የሚታደሙበት መሆኑ በመግለጫው ተገልጿል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን የካቲት 17 ቀን 2016 ዓ.ም