ኢትዮጵያዊነት ህብር ጌጥ ነው። በተለያዩ ብሄሮች ባህል፣ ወግ፣ እምነትና ኪነጥበብ ያጌጠ! በጽጌረዳ አበባ የሚመሰለው ብዝህነታችን ለአገራችን ልዩ ውበት ከመሆኑም በላይ ልዩነቶቻችንን አቻችለንና አንድነታችንን አጠንክረን የኖርንበት ዘመን ታላቅነታችንን ይመሰክራል። አገራችንን ከወራሪ ተከላክለን የቆየነውንና በቅኝ ግዛት መዝገብ ውስጥ ከመከተብ የዳነው በኢትዮጵያዊነት ፍቅርና መተሳሰብ ጸንተን መቆም በመቻላችን ነው።
ያለችን አንድ አገር ስትሆን ዜግነታችንም ኢትዮጰያዊ ነው። ፍት ሃዊነትንና ዴሞክራሲን አስፍነን አንድ ነታችንን ማጠንከርም ብቸኛ ምርጫችን ነው። አገር ማለት ህዝብ ነው እንደሚለው ብሂል አንድነታችን የሚጠነክረው ደግሞ እኛ ኢትዮጵያውያን እርስ በእርስ ስንፋቀርና ስንተሳሰብ ነው። በእውነት መዋደዳችን ተጨባጭ የሚሆነውም የወገናችን ህመም ሲሰማንና ቁሰሉ የእኛም ህመም ሲሆን ነው።
በቃል ብቻ አገራችንና ህዝባችንን እንወዳለን እያልን በተግባር ግን የህመሙና የስቃዩ ምንጭ ከሆንን ግን አገርና ህዝብን እየበደልን ነውና ልናስበብት ይገባል። የእርስ በእርስ መዋደዳችን ከሚገለጽበት መንገድ አንዱ እርስ በእርስ በመደጋገፍ ነው።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ በኢድ አልፈጥር በዓል ከካንሰር ህሙማን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት ከራሳችን አቅም በላይ ባልሆኑ ችግሮችም ጭምር የሌላ አገር ዜጋን ድጋፍ መጠየቁ አጅግ ያሳዝናል።
በእኛው በኢትጵያውያን አቅም ብዙ ወገኖቻችንን ከጎዳና ማንሳት አረጋውያን ለልመና ሳይዳረጉ ማገዝ ቢቻልም በእዚህ ረገድ ያከናወንነው ተግባር አገር መውደዳችንን አይመጥንም ብሎ አፍ ሞልቶ መናገር ይቻላል። በሜቄዶንያ፣ በሜሪጆይ፣ በሙዳይና ሌሎችም አገር በቀል የመረዳዳት ተቋማት የተጀማመሩና አርአያ መሆን የሚችሉ የእርስ በእርስ መደጋፍ ሙከራዎች ቢኖሩም ከሚፈለገው አንጻር ሲታይ ግን በቂ አይደሉም።
ከሻይ ቡና ወጪያችን ጥቂቷን በመመደብ ለአገርና ለወገን የሚተርፍና የህሊና እርካታን የሚያጎናጽፍ አኩሪ ተግባር መፈጸም አንችላለን። ይህንን ሳናደርግ ለአገርና ለወገን ተቆርቋሪ ነን የምንል ከሆነ ድርጊታችን የማስመሰልና የአዞ አንባ ከመሆን አይዘልም።
በቀን ከሚወጣ የማኪያቶ ወጪ አንድ ዶላር ብቻ በመቀነስ ታሪክ መስራት ይቻላል በሚል ጥሪ በተጀመረው የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ እስካሁን የተገኘው ገንዘብ ሲታይ እውን የምናወራውን ያህል አገራችንንና ህዝባችን እንወዳለን የሚል ጥያቄን ያጭራል። የህንድና የቻይና ዳያስፖራዎች ለአገራቸውና ለወገናቸው የሚያደርጉት አስተዋጽኦ አገር መውደድ ምን ማለት እንደሆነ በትልቁ ያስተምራል። ስለሆነም በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከዚህ አንጻር ራሳቸውን ሊፈትሹ ይገባል።
ኢትዮጵያዊ መዋደድ ሊገለጽቸባቸው ከሚገቡ ጉዳዮች ሌላኛው እርስ በእርስ በመተዛዘን ነው። ለአገልግሎት ሰጪው አገልግሎቱ ለነጋዴውም ንግዱ ሊኖር የሚችለው በቅድሚያ ሰላምና ደህንነቱ የተጠበቀ ህዝብ ሲኖር ብቻ መሆኑ መታወቅ አለበት። ይሁንና በተለይም በታክሲ አገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ ሾፌሮችንና ረዳቶችን እንዲሁም የአንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎችን ተግባር ለተመለከተ እውን የሚያገለግሉት ኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸውን መሆኑን ያውቃሉን ያስብላል።
ሰብአዊነት ዝቅ በሚያደርግ ደረጃ ትርፍ መጫን፣ ምክንያት እየፈለጉ ህገወጥ ጭማሪ ማድረግ አዛውንቶችን አለማከበርና ለማገልገል አለመፈለግ ስድብ ወዘተ አገርና ህዝቡን ከሚወድ ዜጋ የሚጠበቁ ተግባራት ባይሆኑም በተለይም በታክሲ አገልግሎት ሰጪዎች ዘንድ ተደጋግመው ሲደረጉ ግን እናያለን። ይህ ደግሞ በሰማይም በምድርም ዋጋ የሚያስከፍል አጉል ተግባር ነውና በፍጥነት ሊወገድ ይገባዋል።
መተሳሰብ ከሌለ በአንድ አገር ውስጥ ሰላም አይሰፍንም። የአንድ አገር ህዝብ ተረጋግቶ እንዲኖርም ፍትሃዊና ምክንያታዊ ገበያ ሊኖር ይገባል። ያለምንም ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ሀዝብን ምሬት ላይ የሚጥል የዋጋ ጭማሪ ሲኖር ህዝብ ተስፋ እንዲቆርጥና የመኖር ህልውናው ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ያደርጋል። ይህ ደግሞ ተስፋ መቁረጥን ስለሚያስከትል ሰላምን ማናጋቱ አይቀሬ ነው። ይህን እውነታ ተመልክተን በአገራችን ያለውን የንግድ እንቅስቃሴ ስናይ እውን ኢትዮጵያዊው ነጋዴ ዘንድ ወገን መውደድ አለን የሚል ጥያቄን ያጭራል።
በርካታ ስራ አጥ ዜጋና በድህነት የሚሰቃይ ወገን ባለበት ሁኔታ ሰንካላ ምክንያቶችን በመደርደር አንዳንዴም ምንም ምክንያት ሳይኖር የሚደረገው የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ በወገን ላይ ሊደረግ የማይገባ ሃላፊነት የጎደለው ድርጊት ነው። አምራቹ ዋጋ ባልጨመረበት ሁኔታ ከሰሞኑ በአገራችን የተከሰተው መረን የለቀቀ የዋጋ ንረትም በምንም መስፈርት ተቀባይነት የሌለው ነው።
ከላይ እንደገለጽነው በሰላም ወጥቶ መግባትና ነግዶ ማትረፍ የሚቻለው ሰላሙና ደህንነቱ የተረገጋጠ ህዝብ ሲኖር ብቻ ነው። ከዚህ በላቀ የምንነግደውም ሆነ የምናገለግለው ለወገናችን መሆኑ ሊዘነጋ አይገባውም።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያዊ መዋደድ ማለት በአፍ ህዝቤን እወዳለሁ ብሎ በአደባባይ መናገር ብቻ ሳይሆን በተሰማራንበት መስክ ለወገን መልካም ማሰብና ማድረግ ብሎም መተሳሰብና በተቻለም መጠን ማገዝ ነውና ይሄው በተግባር ይታይ እንላለን!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 1/2011