የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሲቢኢ ኑር ስድስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ደንበኞችን አፍርቷል

-የሲቢኢ ኑር አገልግሎት በአንድ ሺህ 939 ቅርንጫፎች እየተሰጠ ነው

አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሲቢኢ ኑር ስድስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ደንበኞችን ማፍራት መቻሉን አስታወቀ። በመላ ሀገሪቱ የሲቢኢ ኑር አገልግሎት በአንድ ሺህ 939 ቅርንጫፎች እየተሰጠ መሆኑን ተጠቁሟል።

ከጥቅምት 22 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች “ስኬታማ ምዕራፍ፤ ብሩህ ተስፋ” በሚል መሪ ቃል ሲከበር የቆየው የሲቢኢ ኑር 10ኛ ዓመት ክብረ-በዓል ትናንት የማጠቃለያ መርሀ ግብር ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ በወቅቱ እንደገለጹት፤ በኢትጵያ የተሟላ ከወለደ ነፃ የባንክ አገልግሎት በመስጠት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ግንባር ቀደም ነው።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተሟላ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ 10 ዓመት ማስቆጠሩን ገልጸው፤ በዚህም ልዩ ልዩ የሸሪአ ሕግን የተከተሉ የፋይናንስ ሥርዓት በመዘርጋት ስድስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ደንበኞችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስታውቀዋል።

በአሁኑ ጊዜ የሲቢኢ ኑር የባንክ አገልግሎት በአንድ ሺህ 939 ቅርንጫፎች እየተሰጠ እንደሚገኘ ገልጸው፤ በ156ቱ ቅርንጫፎች ሙሉ በሙሉ የሲቢኢ ኑር አገልግሎት የሚሰጥባቸው መሆናቸውን አመልክተዋል።

የሲቢኢ ኑር ተቀማጭ ገንዘብ ከ107 ቢሊዮን ብር በላይ የተሻገረ ሲሆን፤ የብሔራዊ ባንክ ደንብ እና መመሪያዎችን ተከትሎ በአካታች የፋይናንስ ሥርዓት በርካታ ደንበኞችን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የሲቢኢ ኑር 10ኛ ዓመት ክብረ በዓል በአዲስ አበባ፣ በአዳማ፣ በጂማ፣ በድሬዳዋ እና በሌሎች ከተሞች ተከብሯል ያሉት አቶ አቤ፤ ባንኩ ስለሚሰጠው አገልግሎት ግንዛቤ የማስጨበጥ፣ አዳዲስ ደንበኞችን የማፍራት፣ የደም ልገሳ መርሀ ግብር እና ሌሎች ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል።

የሲቢኢ ኑር 10ኛ ዓመት ክብረ-በዓልን በማስመልከት የባንኩን ቋሚ ሠራተኞች በማስተባበር 715 ሺህ ብር ተሰብስቦ ለኢትዮጵያ ሕፃናት የልብ ሕሙማን መርጃ ማዕከል ማስረከባቸውንም ጨምረው ገልጸዋል።

ባንኩ እአአ 2023 በሳውዲ አረቢያ ጂዳ ላይ በሪቴል ኢስላሚክ ባንኪንግ ሽልማት የተበረከተለት መሆኑን አውስተው፤ ሽልማቱ የተበረከተለት ባለፉት ዓመታት በፋይናንስ አፈፃፀም የኢስላሚክ ባንኪንግ አገልግሎትን ሳይሸራረፍ ተግባራዊ በማድረጉ እና ለሸሪዓ መርሆች ተግባራዊ በማድረግ ባስመዘገበው የላቀ አፈፃፀም መሆኑ አስታውቀዋል።

የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዢ አቶ ሰለሞን ደስታ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ባንክ ለሀገር እድገትና ብልጽግና ወሳኝ በመሆኑ ሁሉምን የኅብረተሰብ ክፍሎች ያካተተ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮችን ማስፋፋት ይገባል።

ባንኩ በዜጎች መካከል የሚታየውን የሀብት ክፍፍልና የገቢ አለመመጣጠን ችግርን ለመፍታት፣ አካታች የፋይናንስ ሥርዓት ለመዘርጋት፣ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ ለሥራ እድል ፈጠራ እና ሌሎች ጠቀሜታዎችን የሚያስገኝ ነው ያሉት ምክትል ገዢው፤ የፋይናንስ ተቋማትን በማሳደግ አካታች አገልግሎት እንዲሰጡ ከማድረግ አንጻር መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

በአነስተኛ የሥራ ዘርፎች ለተሰማሩ ዜጎች፣ ለአርሶ አደሮች፣ ለአርብቶ አደሮች እና ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች በቀላሉ ተደረሽ ሊሆኑ የሚችሉ የፋይናንስ አገልግሎት ሥርዓቶችን መገንባት እንደሚገባም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከዓለም አቀፍ ገበያ ጋር ያለውን ትስስር ወደላቀ ደረጃ ለማሻገር መንግሥት ዘርፉን ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት ለማድረግ አቅጣጫ ማስቀመጡን አስታወሰው፤ ባንኮች በሚሰጡት አገልግሎት ተወዳዳሪ መሆን እንዲችሉ በአቅም ግንባታ፣ በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂ እና በተደራሽነት ከወዲሁ ሊዘጋጁ እንደሚገባ አስገንዘበዋል።

ለባንኩ ሁለተናዊ ዕድገት የበኩላቸውን ድርሻ ላበረከቱ አጋር ተቋማትም ዕውቅና ተሰጥቷል።

ሄለን ወንድምነው

አዲስ ዘመን  የካቲት 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You