አዲስ አበባ፡- የሚኒስትሮች ምክር ቤት 27ኛ መደበኛ ስብሰባው በተለያዩ ረቂቅ ደንቦችና ስምምነቶች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ::
ምክር ቤቱ ትናንት ባካሄደው 27ኛ መደበኛ ስብሰባው በተለያዩ ሀገራዊ ፋይዳ ባላቸው ረቂቅ ደንቦችና የድጋፍ ስምምነቶች ላይ በጥልቀት ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል:: ከተወያየባቸው ጉዳዮች መካከልም የደን ልማት ፣ጥበቃና አጠቃቀም ረቂቅ ደንብ ፣ከዓለም
አቀፍ የልማት ማህበር ጋር የተፈረሙ ሦስት የፋይናንስ ድጋፍ ስምምነቶች እና ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩትን በልማት ድርጅትነት ለማቋቋም የወጣውን ደንብ ለማሻሻል ረቂቅ ደንብ እንደሚገኙበት ተጠቅሷል።
የደን ልማት ፣ጥበቃና አጠቃቀም ረቂቅ ደንብ ሀገራችን ያላትን የደን ሀብት በአግባቡ ለማልማት፣ ለመጠበቅ እና በዘላቂነት ለመጠቀም፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችል ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበ ሲሆን፤ ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በሥራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል።
በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው ከዓለም አቀፍ የልማት ማህበር ጋር የተፈረሙ 3 የፋይናንስ ድጋፍ ስምምነቶች ላይ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ ስምምነቶቹ ለዲጂታል መታወቂያ አካታችነትና አገልግሎት አሰጣጥ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል የ300 ሚሊዮን ዶላር፣ ለትምህርትና ስልጠና ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል የ200 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ለንግድ ሎጅስቲክስ ማሻሻያ ፕሮግራም ማስፈጸሚያ የሚውል የ90 ሚሊዮን ዶላር ብድር የሚያስገኙ መሆናቸው ተጠቅሷል::
ምክር ቤቱም ሁሉም ብድሮች ወለድ የማይታሰብባቸው፣ የ6 ዓመታት የችሮታ ጊዜ ያላቸው እና በ38 ዓመታት ተከፍለው የሚጠናቀቁ መሆናቸውን በማረጋገጥ ረቂቅ አዋጆቹ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ በሙሉ ድምጽ መወሰኑ ተጠቁሟል፡፡
ምክር ቤቱ ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩትን በልማት ድርጅትነት ለማቋቋም የወጣውን ደንብ ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ ደንብ በነጋሪት ጋዜጣ ከታተመበት ቀን ጀምሮ ሥራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
በተጨማሪም የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኢንስቲትዩት እና የፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ተቋማት ለሚሰጧቸው አገልግሎቶች የሚከፈሉ የአገልግሎት ክፍያዎችን ለመወሰን በቀረቡ ረቂቅ ደንቦች ላይ ምክር ቤቱ ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው ከወጡበት ቀን ጀምሮ በሥራ ላይ እንዲውሉ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
ምክር ቤቱም በአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ረቂቅ ፖሊሲ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል ከጸደቀበት የካቲት 16 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በሥራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
በይነ መንግሥታት የልማት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ማቋቋሚያ ማሻሻያ ስምምነትን ለማጽደቅ በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይም ተወያይቶ ይጸድቅ ዘንድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ምክር ቤቱ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡
በመጨረሻም ምክር ቤቱ የተወያየው የብሮሚን፣ የግራናይት ፣የድንጋይ ከሰል እና የደለል ወርቅ ማድናት ልማትን የተመለከቱ አራት ረቂቅ ስምምነቶች ለሀገር ዕድገት አስተዋጽኦ የሚያበረክቱና የመንግሥትን የፖሊሲ አቅጣጫ የተከተሉ ስምምነቶች መሆናቸውን በማረጋገጥ የማእድን ሚኒስቴር ስምምነቶቹን እንዲፈራረም እና ወደ ሥራ እንዲገባ በሙሉ ድምጽ ይሁንታ ሰጥቷል፡፡
ምክር ቤቱ ከጣሊያን መንግሥት ጋር በተፈረሙ 2 ፋይናንስ ድጋፍ ስምምነቶች ላይም ከተወያየ በኋላ ረቂቅ አዋጆቹ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ በሙሉ ድምጽ መወሰኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን የካቲት 17 ቀን 2016 ዓ.ም