የሐዋሳና የጅማ አዳዲስ የደረቅ ወደብ ተርሚናሎች ግንባታ በመጋቢት ወር ይጀመራል

አዲስ አበባ፡- የሐዋሳና የጅማ አዳዲስ የደረቅ ወደብ ተርሚናሎች ግንባታ እስከ ቀጣዩ የመጋቢት ወር መጨረሻ ድረስ እንደሚጀመር የኢትዮጵያ ባሕር፣ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አስታወቀ፡፡

ለሁለቱ ደረቅ ወደቦች ለመጀመሪያ ዙር ግንባታ 300 ሚሊዮን ብር ተመድቧል።

በኢትዮጵያ ባሕር፣ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ የወደብና ተርሚናል አገልግሎት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ምህረትአብ ተክሉ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ድርጅቱ ከማስፋፊያ ግንባታዎች በተጨማሪ አዳዲስ የደረቅ ወደብ ተርሚናሎችን ግንባታ እያከናወነ ይገኛል፡፡

በሐዋሳና በጅማ ሁለት አዳዲስ የደረቅ ወደብ ተርሚናሎች ግንባታን እስከ መጋቢት ወር መጨረሻ ድረስ ለመጀመር ዝግጅት ተደርጓል ያሉት አቶ ምህረትአብ፤ የደረቅ ወደቦቹን ግንባታ በ2016 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ ለማስጀመር ዕቅድ ተይዞ በተለያዩ ምክንያቶች መዘግየቱን አስታውሰዋል።

ተቋሙ የፌዴራል የግዢ መመሪያ የሚከተል መሆኑን አቶ ምህረት አብ ገልጸው፤ ግንባታቸው ላለመጀመሩም ምክንያቱ የግዢ ሂደቱ ላይ ችግር በማጋጠሙ ነው ብለዋል፡፡

ድርጅቱ ግንባታውን ለማስጀመር ሦስት ጊዜ ጨረታ ያወጣ ቢሆንም የግዢ መመሪያ የሚያሟሉና ብቃት ያላቸው ተወዳዳሪ ተጫራቾች ባለማግኘቱ በተደጋጋሚ ጨረታ መሰረዙ አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በጅማ ለሚከናወነው የደረቅ ወደብ ግንባታ የቦታ ርክክቡ ላይ የተወሰነ መዘግየት ተፈጥሮ የነበረ ሲሆን፤ በአሁኑ ጊዜ ግን ከ20 ሄክታር በላይ መሬት በመረከብ የማስተር ፕላንና የቢዝነስ ፕላን ጥናት መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም በሐዋሳ ለግንባታው የተሰጠው ቦታ ሦስት ጊዜ ስፍራው እንዲቀየር መደረጉን የገለጹት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ አሁን ላይ ድርጅቱ ለቦታው ካርታ መቀበሉንና ግንባታ ለማስጀመር የሚያስችለውን ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን ጠቅሰዋል፡፡

በመሆኑም የሁለቱም ደረቅ ወደብ ተርሚናሎች ቅድመ ግንባታ ሂደት በተቻለው ፍጥነት አጠናቅቆ እስከ መጋቢት ወር መጨረሻ ግንባታቸውን ለመጀመር እየተሠራ መሆኑን አቶ ምህረትአብ ገልጸዋል፡፡

ለሁለቱ ደረቅ ወደቦች ለመጀመሪያ ዙር ግንባታ 300 ሚሊዮን ብር መመደቡን አስታውቀው፤ ለቀጣይ ዙር ግንባታዎች ደግሞ ተጨማሪ በጀት እንደሚመደብ አስረድተዋል።

የሚገነቡት ወደቦች ከኮምቦልቻ፣ ከሰመራ እንዲሁም ከመቀሌ የደረቅ ወደብ ተርሚናሎች ጋር የሚመጣጠን አቅም እንደሚኖራቸው አመላክተው፤ አንድ ሺህ 500 ኮቴይነሮችን የማስተናገድ አቅም ይኖራቸዋል ብለዋል፡፡

ግንባታዎቹ በደቡብ የሀገሪቱ ክፍል ያለውን የንግድ እንቅስቃሴውን ለማነቃቃት፣ የወጪ ገቢ ንግድን ለማቀላጠፍ እንዲሁም በወደብ የሚቆዩ ዕቃዎችን ኪራይ ወጪ ከመቀነስ አንጻር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ሲሉ አስረድተዋል።

ፕሮጀክቶቹ በመጋቢት ወር ግንባታቸው ከተጀመረ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቁ የገለጹት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ የቢሮ፣ የመጋዘንና የተለያዩ አገልግሎቶች የሚሰጡባቸው ግንባታዎች እንደሚከናወኑ ጠቁመዋል።

መስከረም ሰይፉ

 

አዲስ ዘመን  የካቲት 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You