አዲስ አበባ:- በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ የሚሆን አራተኛ ዙር ሰብዓዊ ድጋፍ እየተጠናቀቀ ባለው ሳምንት መጀመሩን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ገለጸ፡፡
የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ አታለለ አቡሀይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ለትግራይ ክልል 15 ወረዳዎች የሚሆን ከ27 ሺህ በላይ ኩንታል ምግብ ነክና አልሚ ምግቦች ከድሬዳዋ መጋዘን ወጪ ተደርጎ ተጓጉዟል፡፡
በሦስተኛ ዙር ድጋፍ ከፍተኛውን ወጪ የሸፈነው መንግሥት እንደነበር ጠቁመው፤ በአራተኛ ዙር ድጋፍ አሰጣጥ ረጂ ድርጅቶች በመቀላቀላቸው ድጋፉ ከፍ ይላል ተብሎ ስለሚጠበቅ በቂ በሆነ መንገድ ድጋፍ ለሚፈልጉ ዜጎች ተደራሽ ይሆናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በአማራና አፋር ክልሎችም ድጋፉ ይቀጥላል ያሉት አቶ አታለለ፤ በኮሚሽኑ ስምንቱ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በተለመደው መልኩ ከተደራጁ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ግዢ በመፈጸም በመጠባበቂያ መጋዘኖች ክምችት ማድረጉ መቀጠሉንና በቂ ክምችት መኖሩን አመልክተዋል፡፡
በአንደኛና ሁለተኛ ዙሮች በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት የቅድሚያ ቅድሚያ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ተብሎ ለተጠቀሱና ልየታ ለተደረገላቸው ሰባት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ዜጎች ርዳታ መሰጠቱን፣ በሦስተኛ ዙር ደግሞ ለስድስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዜጎች ድጋፍ መደረጉንም አስታውሰዋል፡፡
በትግራይ ክልል በድርቅና በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ርዳታ ለሚፈልጉ በአንደኛ፣ በሁለተኛና በሦስተኛ ዙር ርዳታ ለሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ዜጎች በስድስት ወራት 894 ሺህ 302 ኩንታል ምግብ ነክ ርዳታ ተሰጥቷል፡፡
አራት ነጥብ አራት ቢሊዮን የሚጠጋ ብር ለትግራይ ክልል ድጋፍ ወጪ ተደርጓል፡፡ ከዚህ ውስጥ መንግሥት አንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር ሲያወጣ፤ ለጋሾች ሦስት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር አውጥተዋል ብለዋል፡፡
በመንግሥት በተሠራው የዲፕሎማሲ ሥራ በአንደኛና ሁለተኛ ዙር ያልተሳተፉ ረጂ ድርጅቶች በሦስተኛው ዙር ተቀላቅለው የሰብዓዊ ድጋፍ ማድረጋቸውን አንስተዋል፡፡
በተለይም በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ፣ ሰሜን ጎንደር፣ ማዕከላዊ ጎንደር፣ ደቡብ ጎንደር፣ ሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ፣ ኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን፣ ሰሜን ሸዋና ምሥራቅ ጎጃም አካባቢዎች በአጠቃላይ 23 ወረዳዎች ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ተረጂዎች እንደነበሩ አመልክተዋል፡፡
በትግራይ ክልልም 31 የሚጠጉ ወረዳዎች ሰሜን ምዕራብ፣ ማዕከላዊ፣ ደቡብ ምሥራቅና ደቡባዊ ትግራይ በሚባሉ አካባቢዎች ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ተረጂዎች ያሉ ሲሆኑ፤ በአፋር ክልል ዞን አንድ፣ ዞን ሁለት፣ ዞን አራት እና ዞን አምስት በድርቅ የተፈናቀሉ 321 ሺህ የማኅበረሰብ ክፍሎች እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡
በአማራ ክልልም በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ጉዳት ለደረሰባቸው ሁለት ሚሊዮን ለሚጠጉ ዜጎች ርዳታ ተሰጥቷል፡፡ በዓይነትና በገንዘብ በመንግሥት አንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር፤ በለጋሾች ሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በአጠቃላይ አራት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ወጪ ተደርጓል ብለዋል፡፡
በአፋር ክልልም በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው 302 ሺህ ርዳታ ፈላጊዎች 85 ሺህ 853 ኩንታል ምግብ ነክ ነገሮች ድጋፍ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡ በአካባቢያቸው ምግብ ገዝተው እንዲጠቀሙ 25 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ተጨማሪ ገንዘብ መሰጠቱንም ነው የገለጹት፡፡
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን የካቲት 16 ቀን 2016 ዓ.ም