በወንድማማችነት እና በአፍሪካዊ መንፈስ የተቃኘ ተምሳሌታዊ ጉርብትና!

በኢትዮጵያና በኬንያ መካከል ያለው ከጉርብትና ያለፈ ግንኙነት ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ ነው። በብዙ መልኩ የሁለቱን ሀገራት ሕዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት ያረጋገጠ፣ በሀገራቱ ሕዝቦች መካከል ያለውን ወንድማማችነት በማጠናከር የቤተሰባዊነት መንፈስ መፍጠር ያስቻለ ነው።

ከጅምሩ በወንድማማችነትና በአፍሪካዊ መንፈስ የተቃኘው የሁለቱ ሀገራት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ግንኙነት በየዘመኑ እያደገና ዘመኑን በሚመጥን እሳቤ እየዳበረ የሀገራቱን ሕዝቦች ወንድማማችነት እና የጋራ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ ዓመታትን አስቆጥሯል።

ይህ የሀገራቱ ሕዝቦች ድንበር ከመጋራት ባለፈ፤ በባህል፣ በቋንቋ እና በታሪክ የተሳሰረ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ግንኙነታቸው እና፤ ግንኙነታቸው የፈጠረው መተማመንና ወዳጅነትም በቀጣናው እንደ ማሳያ ሊጠቀስ የሚችል እንደሆነም ብዙዎች የሚስማሙበት እውነታ ነው።

በተለይም ከኬንያ ነፃነት ማግስት ጀምሮ በሀገራቱ መካከል የነበረው ግንኙነት፣ አፍሪካዊ ወንድማማችነትን መሠረት ያደረገ፤ ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ በሀገራቱ ሕዝቦች መካከል የነበረውን የቆየ ግንኙነት በአዲስ መልክ፤ አፍሪካዊ በሆነ እሳቤና መንፈስ መቃኘት ያስቻለ ነው።

ሀገራቱ በአንድ በኩል በቅኝ አገዛዝ ውስጥ የነበሩ አፍሪካውያን ወንድማማችነትንና የነፃነት ትግል በመደገፍ፤ በሌላ በኩል ትግሉ ተቋማዊ አቅም እንዲያገኝ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እውን እንዲሆን ያደረጉት የተቀናጀ ትግልም፤ በአፍሪካውያን የነፃነት ትግል ውስጥ ትልቅ ስፍራ እንዲያገኙ ያደረጋቸው ነው።

ይህ እውነታ በወቅቱ የነበሩትን የሀገራቱን መሪዎች የአፍሪካ አባት የሚል ከፍ ያለ ስም ያጎናጸፋቸው፤ የሀገራቱ ጉርብትና ከድንበር መጋራት ባለፈ፤ በነፃነትና በወንድማማችነት መንፈስ የተገራ እና ለዚሁ እውነታ የተገዛ ስለመሆኑም እስከዛሬ የመጡበት መንገድ ተጨባጭ ማሳያ ነው።

ሰሞኑን በአዲስ አበባ የተካሄደው 36ኛው የኢትዮጵያና ኬንያ የጋራ ኮሚሽን የሚኒስትሮች ስብሰባ እና በስብሰባው ማጠቃለያ ላይ የተደረሰበት ስምምነትም ይህንን ዘመን ተሻጋሪ የሀገራቱን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ በማሳደግ፤ የሀገራቱን ሕዝቦች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያሳድግ እንደሚሆን ይታመናል።

ስምምነቱ በሀገራቱ መካከል የቆየውን ጠንካራ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በሁሉም መልኩ በላቀ ደረጃ ማስቀጠል የሚያስችል፤ በውጭ ጉዳይና መከላከያ ዘርፎች፣ በንግድና ኢንቨስትመንት፤ በማኅበራት ዘርፎች ለጋራ ተጠቃሚነት አብረው መሥራት የሚያስችላቸውን ዕድል የሚፈጥር ነው።

ሀገራቱ ከፍ ባለ ቁርጠኝነት የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ባደረገ መልኩ አብሮ ለመሥራት የጀመሩት አዲስ መነቃቃት፤ በቀጣይም የጋራ በሆኑ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ሽብርተኝነት፣ ሥራ አጥነት፣ ሕገወጥ ስደትና መሰል ችግሮች ዙሪያ ውጤታማ ሥራዎችን ለመሥራት የተሻለ አጋጣሚ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።

በተለይም አሁን ባለንበት ዓለም አቀፋዊ እውነታ፤ ሀገራት ብሔራዊ ጥቅሞቻቸውን በተሻለ መልኩ ለማስጠበቅ ከተናጠል ይልቅ በጋራ መንቀሳቀስ እንደ ዋነኛ ስትራቴጂ እየተወሰደ ባለበት ሁኔታ በሀገራቱ መካከል እየታየ ያለው አዲስ የትብብር ግንኙነት ብሔራዊ ጥቅሞቻቸውን በተሻለ መልኩ ለማስጠበቅ እንደሚረዳ ይታመናል።

ከዚህም ባለፈ፤ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሕዝቦች ሰላምና ልማት ለማስፈን ካለባቸው መልከ ብዙ ፈተናዎች አኳያ፤ የሀገራቱ አዲስ የትብብር መነቃቃት በአካባቢው ዘላቂ ሰላም እና ልማት ለማስፈን አስፈላጊ የሆነውን የመተማመን መንፈስ ለመፍጠር ይረዳል። የቀጣናው ሀገራት ሕዝቦች በሁለንተናዊ መልኩ የጋራ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ተጨባጭ ተሞክሮ መፍጠር ያስችላል፡፡

በአጠቃላይ የሁለቱ ሀገራት ዘመናት ያስቆጠረ በወንድማማችነትና በአፍሪካዊ መንፈስ የተቃኘው ግንኙነታቸው አሁን ላይ ኢትዮጵያ ሰጥቶ በመቀበል፤ የጋራ ተጠቃሚነት መርህ በአካባቢው አዲስ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ባህል ለመገንባት እያደረገችው ላለው ጥረት ስኬትም ትልቅ አቅም እንደሚሆንም ይታመናል!

አዲስ ዘመን የካቲት 15/2016

Recommended For You