ከአስር አመት በኋላ መኝታ ክፍሌ አልጋ ውስጥ ያስቀመጥኩትን የወረቀት ፋይል አገላብጣለሁ። ዩኒቨርሲቲ እያለሁ የማነባቸውን መጽሐፍቶች፣ የተማርኩባቸውን አንዳንድ ደብተሮች እያየሁ የትዝታ አለንጋ ገረፈኝ። ከዩኒቨርሲቲ ከወጣው ጀምሮ እጄን ወደ አልጋዬ ሰድጄ አላውቅም። ዛሬ ምን ወደዚያ እንደሰደደኝ አላውቅም…ትዝታዎቼ በአእምሮዬ ውስጥ እንጂ እንዲህ አካል ለብሰው ወረቀት ላይ አገኛቸዋለሁ ብዬ አልገመትኩም ነበር። አልጋዬ ስር ባስቀመጥኩት ትናንቴ ወደ ተውኩት አምና ተሰደድኩ።
የትዝታ ተጠቂ ነኝ…ትናንትና ምንም ይሁን ከነግሳንግሱ ይናፍቀኛል። ነገ የትናንትን ያክል ናፍቆኝ አያውቅም። ዘንድሮ ያምናን ያክል ብርቅ ሆኖብኝ አያውቅም። በእኔ ሕይወት ውስጥ ዛሬ ነገ ሲሆን ሁሉም ትዝታ ነው። ከሙዓለ ሕፃናት አሁን እስካለሁበት ጊዜ ድረስ ያለው ትናንት፣ ያለው አምና፣ ያለው ድሮ ናፍቆቴ ነው። ትናንትን አንቆ መግደል አቅቶኛል።
ብዙ ነገሮችን አየሁ…የረሳኋቸውን ብዙ ነገሮች አስታወስኩ። ደብተሬ ላይ የብዙ ጓደኞቼ የእጅ ጽሑፍ ነበር። ክፍል ውስጥ ማድመጥ እንጂ መጻፍ አልወድም ነበር፣ ለዚህም ክፍል ውስጥ እኔ ደብተር ላይ ያልጻፈ አንድም ተማሪ አልነበረም። ትናንትናዬን ገለጥኩት..ዛሬም ድረስ የማይረሳኝን የመክሊትን የእጅ ጽሑፍ ደረስኩበት። መክሊት የክፍላችን ብቻ አይደለችም የዩኒቨርሲቲያችን ብቸኛ ቆንጆ ተማሪ ነበረች። ዛሬም ድረስ የእሷን ዓይነት ቆንጆ ሴት አላየሁም። ድሮዊንግ አስተማሪያችን በእሷ ምክንያት ‹ኤፍ› እስከሰጠኝ ጊዜ ድረስ ተለያይተን አናውቅም ነበር።
አይ ትቸር ሞገስ…ትቸር ሞገስ ድሮዊንግ አስተማሪያችን ነው…ክላስ እንደገባ የመጀመሪያ ሥራው ወዳለችበት ተራምዶ አጠገቧ መቆም ነው። ከዚያ በኋላ ነው ብላክ ቦርዱ ላይ የሆነ ነገር ስሎ የሚያስተምረን። ከእኔ ኋላ ስለምትቀመጥ አጠገቧ ሲቆም ጥላው ያርፍብኛል። ዛሬም ድረስ የሚጠረንፈኝ ሽቶው ይሸተኛል። ሰማይ የተደፋብኝ ያክል ክብድ ይለኛል። ወንድነቱ ነፍሴ ላይ ያርፋል። ሰው እንዴት ያንን ያክል ይገዝፋል? ሳይናገር፣ ሳያወራ፣ ቃል ከአፉ ሳያወጣ የኔን ነፍስ ያስጨንቃታል። እሱ ጎልያድን እኔ ደግሞ ዳዊትን ሆነን እዚያ ስፍራ ለአንድ አመት ተሰቃይቻለሁ። ከአጠገቤ እብስ ሲል እንደ ዳዊት በጠጠር ያባረርኩት ነው የሚመስለኝ። በነጋታው አጠገቤ ጥላው አርፎብኝ ሳየው ጎልያድ ፊት እንደ ቆመው ኮሳሳው ዳዊት እኮስሳለሁ።
ትቸር ሞገስ የመክሊትን ስም ሳይጠራ አስተምሮን አያውቅም። ዛሬም ድረስ ያልገባኝ ነገር የሴት ስም ለአንድ ድሮዊንግ ምሳሌ ሆኖ መቅረቡ ነው። አመት ሲያስተምረን ከመክሊት ስም ሌላ ምሳሌ ተጠቅሞ አያውቅም። እኛ ክላስ ኤክስና ዋይ የሚያርፉት በድሮዊንግ ክላስ በመክሊት ስም ነው። ኤክስና ዋይ ነፍስ ቢኖራቸው ኖሮ መክሊትን የሚያመሰግኑ ይመስለኛል። ክላስ ውስጥ በእሷ ምክንያት ለሰባት ልጆች ‹ኤፍ› ሰጥቷል..ከዚያ ውስጥ አንዱ እኔ ነኝ። በአንድ ቆንጆ ሴት ምክንያት ምንም የማናውቅ የሰባት ወንዶች ህልም መደናቀፉ ዛሬም ድረስ ያናድደኛል። ትቸር ሞገስ ለምን መምህር እንደሆነ አላውቅም…
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መክሊትን ፈራኋት….ግዝት እንዳለበት ሰው በመቶ ሜትር ነበር የምርቃት። እስከተመረቅንበት ጊዜ ድረስ አውርቻት አላውቅም። የምርቃታችን ጊዜ ከአዳራሽ ስወጣ ጠብቃ አንድ ነገር አለችኝ…..‹ከእንግዲህ እኮ አንገናኝም፣ ነገ ለእኔና ለአንተ ሌላ ቀን ነው..ከአንተ ጋ አንድ ማስታወሻ እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ አለችኝ።
ዝም ብዬ ፊቷ ቆምኩኝ…ያ ቀን ከረጅም ጊዜ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ፊቷ የቆምኩበት ቀን ነው። በደንብ አየኋት…እንደዚያ ቀን ውብ ሆና አይቻት አላውቅም። ፊቷ ላይ ውበቷን ያደመቁ ብዙ ዓይነት ቀለሞች ይታዩኛል። ቅንድቧ በቀጭን ተቀንድቧል፣ ዓይኖቿ ዙሪያ ገባውን ተኩለዋል። ጉንጮቿ በወዛማ ቀለም ልመዋል። ከንፈሯ እንደምትወደው በማውቀው፣ ሰማይ ቤት ድረስ ይዛው በምትሄደው ቀይ ቀለም ደምቋል። በዚህ ሁሉ ውስጥ ዓይኖቿ ይስቃሉ፣ ጠንበለል አካሏ ይቁነጠነጣል።
‹ነገ ሲሆን ሁሉም ሌላ ነው…የአሁን ማለዳዎች በኋላ የሚመሹ ናቸው። ነገ በሚደበዝዙ አጋጣሚዎች ልትለያት አንድ ቀን የቀረህን ጓደኛህን አታሳዝናት› ስትል ሰማኋት። ልቤ አራራልህ አለኝ። በሕይወቴ ሁሉም ቦታ ያለች ሴት ሆና ግን ጨከንኩባት። የነፍሴ ቦታ ቢታይ..የልቤ ስፍራ ቢፈተሽ እሷ ብቻ ናት ግን ፊት ነሳኋት። ዓይኖቿ ይማጸኑኛል…ዓይኖቼ ይሸሻታል።
ከየት እንዳመጣሁት የማላውቀው እንቢ ልላት የሚያስችል ብዙ ኃይል ነበረኝ። ዕድሜ ለትቸር ሞገስ እንደ አራስ ነብር እንድፈራት አድርጎኛል። በዚያ በመጨረሻ ሰዓት አንድ ፎቶ እንነሳ ብላ ከነጋውኗ ፊቴ ስትቆም ትቻት ነበር የሄድኩት። ያ ቀን ሁሌም ይቆጨኛል። ምነው እሺ ባልኳት ስል አስባለሁ። ዛሬ ላይ ከእሷ ይልቅ እኔ ነበርኩ ያ ፎቶ የሚያስፈልገኝ እላለሁ። ከእሷ ጋር ለመታረቅ ያ ቀን ትክክለኛ ጊዜ ነበር። ያን ያክል ለምን እንደጠላኋት አላውቅም። በጣም የሚገርመው ደግሞ በሸሸኋት በነዚያ ሁሉ ቀን ውስጥ ልታናግረኝ ስትከተለኝ እንደነበረ አስታውሳለሁ።
አሁን ላይ ልቤ ይቅር ብሏት ቢሆን ኖሮ እላለሁ። አሁን ላይ አንድ አይደለም ከእሷ ጋር ለቁጥር የሚታክቱ ፎቶዎች ኖረውኝ ቢሆን እላለሁ። በተለያየንባቸው አስር አመታት ውስጥ ሳላስባት የቀረሁበት ጊዜ አልነበረም። እሷም ይሄን ስለምታውቅ ነው መሰለኝ ትናንትና ዛሬ አንድ ዓይነት አይደሉም ያለችኝ። ከሰው ልጅ ቀድሞ ሕይወት የገባት ሴት ትመስለኛለች። ትናንት ላይ ሆና ዛሬዬን አይታልኛለች። ባሳለፍኩት አስር አመታት ውስጥ ነፍሴ እንደ እሷ የተራበችው ሰው የለም። እኔም በእሷ የተራቆትኩትን ያክል በምንም አልተራቆትኩም። አሁን የት እንዳለች አላውቅም ይሄ ሁሉ ዘመን አልፎ እንኳን ከውስጤ አልደበዘዘችም…ፊቴ ቆማ አንድ ፎቶ እንነሳ እንዳለችኝ እኔም አንድ ቀን ፊቷ ቆሜ እባክሽ ፎቶ እንነሳ የምልበት ቀን ይመጣል እላለሁ።
ምድር ላይ ዳግም እኔና እሷ እዚያ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ፣ እዚያ ክፍል፣ እዚያ አዳራሽ በር ላይ ብንፈጠር እላለሁ። እዚያ ክፍል በትቸር ሞገስ ብንማር እላለሁ። ስለ እሷ የማይሆን ነገር አስባለሁ..
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን የካቲት 15/2016