ለዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ቻምፒዮና ዝግጅቱ ተጠናክሮ ቀጥሏል

በዓለም አትሌቲክስ ዓመታዊ የውድድር መርሀ ግብር መሰረት የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ ቻምፒዮና ከሳምንት በኋላ በስኮትላንድ አዘጋጅነት በግላስኮ ከተማ ይካሄዳል። የመም ሩጫ እና የሜዳ ተግባራት ውድድሮች ብቻ የሚስተናገዱበት የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና ዘንድሮ ለ19ኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን፤ ለሶስት ቀናትም ይቆያል። በቻምፒዮናው በ29 ውድድሮች አትሌቶች ለአሸናፊነት የሚፋለሙም ይሆናል፡፡

በቻምፒዮናው በስኬታማነት ተጠቃሽ ከሆኑት የአትሌቲክስ ሀገራት አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያም እንዳለፈው ጊዜ በሜዳሊያ ሰንጠረዡ ቀዳሚ ሆና ለማጠናቀቅ ብሄራዊ ቡድኗ ዝግጅት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያ በየሁለት ዓመቱ በሚካሄደው ውድድር በርካታ ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ከዓለም ቀዳሚ ሀገራት ጋር የምትሰለፍ ሲሆን፤ ከአፍሪካ ደግሞ የሚስተካከላት የለም፡፡ በዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና 268 ሜዳሊያዎችን በማስቆጠር ከላይ የተቀመጠችው አሜሪካ በሩጫ እና በሜዳ ተግባራት ውድድር እጅግ በርካታ አትሌቶችን ታሰልፋለች፡፡

ከዓለም የትኛውም የአትሌቲክስ ውድድር የታገደችው ሩሲያ በበኩሏ አስቀድማ በሰበሰበቻቸው ሜዳሊያዎች ቁጥር(145) በደረጃ ሰንጠረዡ በሁለተኛነት ተቀምጣለች፡፡ ሦስተኛዋ ሀገር ኢትዮጵያ ደግሞ በመድረኩ 59 ሜዳሊያዎችን አግኝታለች፡፡ ከእነዚህ መካከልም 31የወርቅ፣ 13የብር እና 15 የነሃስ ሜዳሊያዎች ናቸው፡፡

እአአ በ2022 የሰርቢያዋ ቤልግሬድ አዘጋጅ በነበረችበት 18ኛው ቻምፒዮና ደግሞ ኢትዮጵያ 4የወርቅ፣ 3 የብር እና 2የነሃስ በጥቅሉ 9 ሜዳሊያዎችን በማስቆጠር አሜሪካና ቤልጂየምን በማስከተል ከዓለም አንደኛ ሆና ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው፡፡ ይህንንም ተከትሎ ከቀናት በኋላ ማለትም ከየካቲት22 እስከ 24/2016ዓም በሚካሄደው ውድድር ላይ ኢትዮጵያ በርካታ ሜዳሊያዎችን በማግኘት በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ተቀምጣ ንግስናዋን ታስጠብቃለች በሚል ይጠበቃል፡፡

ይህ የሆነበት ዋነኛው ምክንያት ደግሞ ቻምፒዮናው ከመካሄዱ ሳምንታት አስቀድሞ በበርካታ የዓለም ሀገራት በሚካሄዱ የዓለም የቤት ውስጥ ቱር ውድድሮች በመካፈል በሚያስመዘግቡት አስደናቂ ስኬት ነው፡፡ በተለይ የወርቅ ደረጃ ባላቸው ውድድሮች በተለያዩ ርቀቶች ተወዳድረው አሸናፊ ከመሆን ባለፈ የቦታውን ፈጣን ሰዓት ጭምር በማሻሻል ብቃታቸውን ሲያስመሰክሩ ቆይተዋል፡፡ በዓለም አቀፉ ተቋም ወርቅ ደረጃ ከተሰጣቸው ውድድሮች የመጨረሻውም ነገ ማድሪድ ላይ ከተካሄደ በኋላ የቱር ውድድሩ የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡

አትሌቶች በቱር ውድድሩ የሚያስመዘግቡት ሰዓት የቻምፒዮናውን ሚኒማ የሚያሟላ ከሆነ ሀገራቸውን የመወከል ዕድል የሚያገኙ ሲሆን፤ በተሳትፏቸው የሚያስመዘግቡት ነጥብ ተደማምሮ የተሻለ ከሆነ ደግሞ በቀጥታ ውድድሩ ላይ የሚያሳትፋቸውን የይለፍ ካርድ(wild card) ይወስዳሉ፡፡

በዚህም መሰረት የቻምፒዮናውን መስፈርት ማሟላት የቻሉ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ከየካቲት 11/2016ዓ.ም አንስቶ ልምምድ ማድረግ የጀመሩ መሆኑን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መረጃ ይጠቁማል፡፡ 8 ሴቶች እና 5 ወንድ በድምሩ 13 አትሌቶችን ያቀፈው ብሄራዊ ቡድኑ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ መም ዝግጅታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ ቡድኑ በውድድሩ የሚካፈልባቸው ርቀቶችም በሁለቱም ጾታ 1ሺ500 ሜትር እና 3ሺ ሜትር እንዲሁም በ800 ሜትር ሴቶች መሆኑ ታውቋል፡፡

በተለያዩ ርቀቶች የዓለም ቻምፒዮና፣ የክብረወሰን ባለቤቶችን፣ በውድድሩ ልምድ ያላቸውና ከዚህ ቀደም ውጤታማ የነበሩ እንዲሁም ወጣት አትሌቶችን ያቀፈው ቡድኑ እንዳለፈው ቻምፒዮና ውጤታማ እንደሚሆን ይታመናል፡፡ በቤት ውስጥ ቻምፒዮና ኢትዮጵያ የምትታወቀውና በተለይም ውጤታማ የሆነችው በ1ሺ500 ሜትር ርቀቶች ሲሆን፤ የቻምፒዮናው ክብረወሰንም በሁለቱም ጾታዎች የተያዘ ነው፡፡

አስደናቂ የሆነው የ3ሺ ሜትር ወንዶች ክብረወሰን በአንጋፋው ጀግና አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ እአአ በ1997 ፓሪስ ላይ የተመዘገበው 7:34.71 የሆነ ሰዓት እስካሁን ሊሻሻል አልቻለም፡፡ በ1ሺ500 ሜትር ደግሞ ቤልግሬድ ላይ አትሌት ሳሙኤል ተፈራ የገባበት 3:32.77 የሆነ ሰዓት ነው፡፡ ቤልግሬድ ላይ በሴቶችም 1ሺ500 ሜትር በጀግናዋ አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ 3:57.19 የሆነ ክብረወሰን ተመዝግቧል፡፡

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን የካቲት 14/2016

Recommended For You