የሴቶች መዋቢያ ‹‹ሜክ አፕ›› በባለሙያዎች እይታ

ለውበት መጨነቅ ፣ ቆዳን መንከባከብ የሚባሉ ርዕሶች በቀጥታ ከሴቶች ጋር የሚገናኙ ይመስላል:: እንደ ሀገራችን ባህልም ብዙ አይነት መዋቢያዎች ሴቶች በቤታቸው ቆዳቸውን የሚንከባከቡባቸው የሚያሳምሩባቸው በውበታቸው ጎልተው እንዲታዩ የሚያደርጉባቸው ልማዶች ብዙ ናቸው:: ታዲያ ሰለጠነ በምንለው ዓለም በውበት አጠባበቅ ዙሪያ ላይ የሚሰጡ አይነታቸውም ብዙ ነው:: በርካታ ባለሙያዎችም ይገኛሉ:: ሴቶችም በቤታቸው ከሚያደርጓቸው ልማዶች ባለፈ በአካባቢያቸው ከሚገኙ ከትናንሽ የውበት ሳሎኖች ወደ ትልልቅ የውበት ሳሎኖች በማምራት የቆዳቸውን ንጽህናና ውበት ይጠብቃሉ::

ራስን የማስዋብ ነገር ሲነሳ አሁን ባለንበት ዘመን በተለይ ሴቶች ቆዳቸውን ለመንከባከብና አምረው ለመታየት በዘመናዊ መንገድ የተሰሩ ምርቶችን ይጠቀማሉ:: በባለሙያዎች እና በተጠቃሚዎች ዘንድ ውበትን ያጎላል የሚባልለት በሌሎች ጎራ ደግሞ ራስን ይቀይራል ሰዎች በራሳቸው ውበት እንደማይተማመኑ ማሳያ ነው የሚባልለት ‹‹ ሜክ አፕ ›› ወይንም በገጽ ላይ የሚቀቡ ምርቶችን መጠቀም እየተለመደ መጥቷል::

በሀገራችን እነዚህን መዋቢያ ምርቶች የሚጠቀሙ ሴቶችም እየተበራከቱ መጥተዋል:: በተመሳሳይ አገልግሎቱን የሚሰጡ የውበት ሳሎኖችም በየሕንጻዎቹ በዝተው ይታያሉ:: በዛሬው የፋሽን ገጻችን እነዚህን የገጸ ቅብ መዋቢያ ምርቶቸ ለሽያጭ ከሚያቀርቡ እና በውበት ሳሎን ውስጥ አገልግሎቱን ከሚሰጡ ባለሙያዎች ጋር ቆይታ አድርገናል::

‹‹ኤምኬ የውበት ሳሎን›› በመሀል አራት ኪሎ አምባሳደር የገበያ አዳራሽ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፤ የሜክ አፕ ባለሙያዋ ቅድስት ሙሉነህ የጥፍር ሥራ ሜክ አፕ እና ሌሎች አገልግሎቶችን በውበት ሳሎኗ ትሰጣለች:: ሙያውን ከልጅነቷ ጀምሮ ትወደው የነበረ በመሆኑ በኋላ በትምህርት የተደገፈ ስልጠናን በመውሰድ የራሷን የውበት ሳሎን ከፍታ አገልግሎቱን እየሰጠች ነው:: ከዚህ ቀደም በነበራት ልምድ እንስቶች ስለ ሜክ አፕ የነበራቸው እውቀት እምብዛም አልነበረም ፤ መሰራት ሲፈልጉም ውስን ለሆኑ ፕሮግራሞች በባለሙያዎች ምርጫ ይሰራሉ:: ‹‹አሁን ላይ ሜክ አፕ የሚሰሩ ደንበኞቻችን በብዛት መሰራት የሚፈልጉትን አይነት ጠንቅቀው የሚያውቁ ናቸው›› በማለትም ግንዛቤው እየተሻሻለ ምምጣቱን ታነሳለች።

የውበት ሳሎኑ መስራች ቅድስት እንደምትለው እንስቶቹ የሚጠቀሙት የመዋቢያ መሳሪያዎች እንደየቆዳ ቀለማቸውና የቆዳቸው አይነት ደረቅ፣ ወዛም ተብሎ ይለያል:: ምርቶቹ ውበትን የሚያላብሱ ቢሆንም ፊታችን ጥርት ያለ ለመሆን መዋቢያ ምርቶቹ የሚያመጡትን ውጤት እንደሚቀንሰው ቅድስት ትናገራለች::

ደንበኞቿ ወደ ኤምኬ የውበት ሳሎን የሚመጡት ጥሪዎች ሲኖሩባቸው አልያም የእርግዝና ጊዜያቸውን በፎቶ ማስቀረት ሲፈልጉ መሆኑን ትናገራለች:: የሠርግ ሥነ-ሥርዓቷን የምታካሂድ ሙሽሪት ከሆነች ደግሞ ደንበኞቿ ወደሚገኙበት ቦታ የመስሪያ እቃዎቿን ይዛ በመሄድ ከነ ሚዜዎቿ አገልግሎቱን ትሰጣለች:: ደንበኞቿ ሜክአፕ ለመሰራት ወደ እሷ ሲመጡ በመጀመሪያ የቆዳ አይነታቸውን በመጠየቅ ያላቸውን የቆዳ ቀለም በማየት የሚስማማውን ምርት ታዘጋጅላቸዋለች፤ ፊታቸውን በሚስማማቸው መታጠቢያ ማጽዳት የመጀመሪያው ሥራ ነው ::

አንድ ሙሉ ሜክ አፕ ለመስራት የሚያገለግሉ ግብዓቶች ከ10 በላይ መሆናቸውን የምታነሳው ቅድስት ቀለል ያለ ሜክ አፕ ለመስራት ግን ውስን ግብዓችን እንደምትጠቀም ትገልፃለች:: በሙያው ረጅም ጊዜ የቆየችው ቅድስት ከዚህ ቀደም የነበረው ፋሽን ቀጭን ቅንድብ፣ ጎላ ብለው የሚታዩ የተለያየ ቀለም ያላቸው የዓይን ሻዶው እና ደማቅ የከንፈር ቀለም (ሊፒስቲክ ) ነበር :: ነገር ግን በአሁን ሰዓት የምርቶቹ መሻሻል የፋሽን መለዋወጥ ሰዎች በአብዛኛው መሰራት የሚፈልጉት ፍፁም ከቆዳ ቀለማቸው ጋር ተመሳሳይ የሆነ እና ተፈጥሯዊ ውበታቸውን የሚያጎላ የሜክ አፕ አይነት ነው:: የአንድ የሜክ አፕ ባለሙያ ችሎታው የሚለካውም በእንስቷ አይን ላይ የሚጠቀማቸው ምርቶች መጠንና ጠንቃቃ መሆን እንደሆነ ቅድስት ጠቅሳለች ::

ቅድስት ቀለል ያለ ሜክአፕ ሰርቶ ለማጠናቀቅ ከ45 ደቂቃ እስከ አንድ ሰዓት የሚወስድባት ሲሆን፤ የሙሽሮችና የሚዜዎች ከሆነ ደግሞ እስከ አንድ ሰዓት ተኩል ጊዜን ይወስዳል :: ለዚህም ደግሞ ቀለል ያለ ሜክ አፕ ለሚሰሩ ደንበኞች ከሁለት ሺህ ብር ጀምሮ ለሙሽሮች እስከ 10 ሺህ ብር የሚደርስ ክፍያ ትጠይቃለች:: ዋጋውም እንደስራው እና እንደየውበት ሳሎኑ ይለያያል :: ሜክአፕ ራሱን የቻለ ጥበብና ውበት ይኑረው እንጂ ቅድስት ሜክ አፕ የተሰሩ እንስቶች ማታ ሳያስለቅቁት በፍጹም መተኛት እንደሌለባቸው ገልጻለች:: ዘርፉ በርካታ የሥራ እድልን እየፈጠረ በመሆኑ ሙያውን የሚስተምሩ ትምህርት ቤቶች ተበራክተው ይገኛሉ::

የመዋቢያ ምርቶች በአጠቃላይ ከተለያዩ ሀገራት የሚገቡ ሲሆን፤ ጊዜያቸው ያላለፈባቸው ምርቶች መሆናቸውን ማጣራትም መረሳት የሌለበት ጉዳይ መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ:: ታዲያ እነዚህ ምርቶች እያስመጡ የሚያቀርቡ እንዳሉ ሁሉ በሀገራችን የተሰራ ምርት ማቅረብ የጀመረ ‹‹ሄላዝ ቢውቲ ››የሚባል ካምፓኒ አለ። የተለያዩ የመዋቢያ ምርቶችን የሚያቀርብ ሲሆን፤ ለየት የሚያደርገውም ለኢትዮጵያውያን እና ለአፍሪካውያን ቆዳ ተብለው የተሰሩ ምርቶችን ማቅረቡ እንደሆነ ባለሙያዎች ይገልፃሉ::

የሜክ አፕ ባለሙያዋ አብሳላት አበራ የዚህ ሀሳብ ተጋሪ ነች። ‹‹ከውጭ የመጡ መዋቢያዎችን በምንጠቀምበት ወቅት የተለያየ ቁጥር ያላቸውን ምርቶች ቀላቅለን ለመጠቀም እንገደዳለን ፤ ሄላዝ ግን ለኛ ቆዳ ተብሎ የተሰራ በመሆኑ እንደዛ ማድረግ አይጠበቅብንም›› ትላለች:: በሄላዝ ቢውቲ የሚገኙ አስፈላጊ የሚባሉ መዋቢያዎች ሲሆኑ የከንፈር ቀለም፣ ፋውንዴሽን ፣ ኮንሲለር ፣ ፓውደር ሁሉም ምርቶች ይቀርባሉ:: ምርቶቹም ሀገር በቀል በመሆናቸው ኢትዮጵያዊ ስሞችን ይዘዋል ‹‹ውቢት ፣ በርቺ ፣ ደፋር ፣ ጀግኒት›› እንዲሁም የተለያየ ስሞች፣ የወራት ስያሜዎች ከመስከረም እስከ ጳጉሜ የተሰየሙ ሀገራዊ ስያሜዎችን የያዙ ምርቶችን ያቀርባሉ:: እነዚህን ምርቶች በአብዛኛው ለመግዛት የሚመጡት ሴቶች ሲሆኑ በጥቂቱ ስጦታ መስጠት የሚፈልጉ ወንዶችም ለመግዛት ወደ ሱቁ ይመጣሉ::

የውበት አጠባበቅ ባለሙያዎች ሜክ አፕ መጠቀም ላይ የተለያየ መክረ ሀሳብ የሚሰጡ ሲሆን፤ ሁሉም ግን ባእድ ምርቶችን በፊት ቆዳ ላይ በምንጠቀምበት ወቅት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ። ለምርቶቹ አዲስ የሆኑ ተጠቃሚዎችም በቆዳቸው ላይ ከማድረጋቸው በፊት ባለሙያዎችን እንዲያማክሩ ያሳስባሉ።

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You