የምንሻት ታላቋ አፍሪካ የምትፈጠረው በታላቅ ሀሳብና ተግባር ነው ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)

የአፍሪካ ሕብረት እ.ኤ.አ በ1963 መገባደጃ ላይ 32 በሚሆኑ የወቅቱ የአፍሪካ ነጻ መንግስታት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በሚል ስያሜ ተመሰረተ። ከአራት አስርት ዓመታት በኋላ ደግሞ የአሁኑን መጠሪያ ሊይዝ ቻለ። እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2002 የመጀመሪያውን የመሪዎች ጉባኤ ሲያካሂድ ቀድሞ ይዞት ከመጣው ዓላማና ተልዕኮ ጋር የተዋሃደ ተጨማሪ አፍሪካዊ ጉዳዮችን አጀንዳው አድርጎ ቀጥሏል። የ2063 አሁጉራዊ አጀንዳም የዚሁ አካል ነው፡፡

በዘንድሮው የሕብረቱ ጉባኤ ላይም በዋናነት ሰላምና ደህንነት፣ ቀጠናዊ ጥምረትና እድገት መወያያ አጀንዳ ሆኖ ከፊት ተቀምጧል።ሰላምና ደህንነት የወቅቱ አኅጉራዊ ጉዳይ ከመሆኑ አንጻር አጀንዳ መሆኑ ብዙም ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም። በዚህ ዙሪያ ገና ያልተወጧቸው የቤት ስራዎች በርካታ ናቸው፡፡

እነዚህ አጀንዳዎች በቀደሙት የሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ቀርበው ውይይት ቢደረግባቸውም ችግሩ ለዘለቄታው ሊፈታ አልቻለም። በሰላምና ጸጥታ ጉዳች ሕብረቱ ተወያይቶ አቅጣጫ አስቀምጦ መፍትሄ ያላመጣባቸው አስረጂዎች እዚም እዛም አሉ፡፡

ሕብረቱ እንደ ድርጅት ሲቋቋም የመጀመሪያ ዓላማው የአፍሪካውያንን ነፃነት በማረጋገጥ፣ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ ማኅበራዊ ተጠቃሚነት ማጽናት ነው። በተለይም ፀረ ቅኝ ግዛት ትግሉ በድል ከተጠናቀቀ በኋላ፤ ኢኮኖሚያዊ ነጻነትን ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ የመስራት አቅጣጭ ይዞ መንቀሳቀስ ቆይቷል። እስካሁን ባለው ሁኔታ ብዙ ለውጦች ማስመዝገብ ቢችልም የተጠበቀውን ያህል ግን መሄድ አልቻለም።

እንደሚታወቀው አፍሪካ ብዙ የተፈጥሮ ጸጋዎች ባለቤት ብትሆንም አሁንም ይህንን ሀብት ወደሚፈለገው ብልጽግና ለውጣ ለነዋሪዎቿ ለኑሮ የተሻለች ማድረግ አልተቻለም። ከነበረችበትና ካለችበት የኢኮኖሚ ጥገኝነት መላቀቅ አልተቻለም። ይህን ዘመናት አብሮን አየተጓዘ ያለ ችግር ለመለወጥ ከሁሉም በላይ የአፍሪካ ሕብረት ትልቅ አቅም እንደሚሆን ይታመናል።

አፍሪካውያን ባላቸው አቅም የራሳቸውን እድል በራሳቸው እንዲወስኑ ከሁሉም በላይ ቁርጠኝነትን የሚፈልጉ እና የአብሮነት ትስስርን የሚሹ በውይይትና በምክክር የሚፈቱ በርካታ የጋራ ጉዳዮች አሏቸው።በራስ መተማመን ላይ የተመሰረተ ማንነት ከመፍጠር ጀምሮ ስለሰላምና ስለለውጥ ቁጭ ብለው በሰከነ መንፈስ የሚነጋገሩባቸው መድረኮች ያስፈልጓቸዋል፡፡

አፍሪካ ከትላንት እስከዛሬ ሌሎች ባደረሱባት ሰንኮፍ ስር ናት። ይሄን ሰንኮፍ አውልቃ በራሷ መልክና ደም ግባት፣ ችሎታና ጽናት፣ ኢኮኖሚና መርህ፣ ፖሊሲና እቅድ መቆም አለባት።ይሄ እንዲሆን የመጀመሪያው ምዕራፍ ቁርጠኝነት የታከለበት የመሪዎች ውይይትና ውሳኔ ነው።

ቁርጠኝነት በሌለበት ሁኔታ የተደጋገሙ ውይይቶች እና የአቋም መግለጫዎች በራሳቸው የሚያመጡት ነገር አይኖርም። ወቅቱ በበረታ የሀሳብ ሙግት የበረታች አፍሪካን ለመፍጠር ወገብ ማጥበቅ የሚፈለግበት ነው።በተግባር መር አስተሳሰብ ነገሮችን በኃላፊነት መንፈስ ተቀብሎ እና ዋጋ ከፍሎ መራመድን የሚጠይቅ ነው።

ቅኝ ግዛት ካሉት ብዙ መልኮች አንጽር፤ አሁን ላይ በአፍሪካ ምድር እየሆነ ያለው የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ አፍሪካን እና አፍሪካውያንን ብዙ ዋጋ እያስከፈለ ነው። በእርዳታ ስም የሚገቡ እጅ መጠምዘዞች፣ እከክልኝ ልከክልህ አይነት አሳቤዎች የዚህ የቅኝ ግዛት መልኮች አንድ መገለጫዎች ናቸው።

አፍሪካውያን አሁን ላይ በኢኮኖሚው ሆነ በፖለቲካው መስክ ለሚያደርጓቸው የለውጥ ንቅናቄዎች የሌሎችን ፍቃድ ማግኘት ግድ የሚልበት ዘመን ላይ ደርሰዋል። ይህን ተጽእኖ ተቋቁሞ ለመሻገር አፍሪካውን አንድነታቸውን አጥብቀው ከመሄድ ባለፈ ሊኖራቸው የሚችለው ሌላኛው አማራጭ ብዙም አስተማማኝ አይደለም።

የአፍሪካ ሕብረት ይህንን ሕብረት ለመፍጠር አደራ የተጣለበት ትልቅ አህጉራዊ ተቋም ነው። በዚህም የአህጉሪቱን፣ የሕዝቦቿን ፖለቲካዊ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ፤ በአፍሪካ ጉዳይ ላይ ተወያይቶ መግለጫዎችን አውጥቶ ከመለያየት ባለፈ የሚጨበጥ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል ተግባራዊ እርምጃ ይጠበቅበታል።

በዚህ ዓለም እድገትና ስልጣኔን ለማምጣት ዋነኛ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል፤ የተፈጥሮ ሀብትና የሰው ኃይል ተጠቃሽ ናቸው።እንደ እድል ሆኖ ሁለቱም በአፍሪካ ምድር የሚገኙ ናቸው። ይህም ሆኖ ግን በእስካሁኑ አፍሪካውያን በተፈጥሮ ጸጋቸው ሌሎችን ከመጥቀም ባለፈ ራሳቸውን ሲጠቅሙ አይታይም። አሁንን ድንነትና ኋላቀርነት ውስጥ ናቸው።

ይህ ጉዳይ መቋጯ እንዲያገኝ የአፍሪካውያን ፍላጎት ነው።መጪውን ጊዜ በብስለትና በንቃት ቃኝተን ከራሳችን ለራሳችን በሆነ መሪ ሀሳብ ከድህነትና ከተረጂነት የምንወጣበትን መንገድ ማመቻቸት ይኖርብናል። ለዚህ ደግሞ የአፍሪካ ሕብረት የሚኖረው አስተዋፆ መተኪያ የሌለው እንደሚሆን ይታመናል።

እኛ ያቃተን የራሳችንን ሀብት በራሳችን እውቀት መጠቀም ነው። ይህ የሆነው በእውቀት ችግር ስላለብን ብቻ ሳይሆን ከሁሉም በላይ ሀብቶቻችንን አልምተን እንዳንጠየቀም ያለው የውጪ ጣልቃ ገብነት ነው። ይህንን ጣልቃ ገብነት ለማስቆም በጋራ መሰረት ላይ የቆመ ትግል አለማድረጋችን ያልተገባ ዋጋ እንድንከፍል አያደረገን ነው።

ይህ ለዓመታት የመጣንበት መንገድ እንዲያበቃ፤ ከሴራ ፖለቲካ፤ እርሱ ከሚፈጥረው የእርስ በርስ ጦርነት እና ግጭት መውጣት አለብን። በድህነት፣ በኋላ ቀርነት መውጣት የሚያስችለንን አንድነት አቅም መገንባት ይኖርብናል። በተፈጥሮ ሀብቱ የበይ ተመልካች የሆነውን የአህጉሪቱን ሕዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ ስለ አንድነት መትጋት ይጠበቅብናል።

ከመጀመሪያው የሰው ዘር አፈጣጠር ጀምሮ አዲስ ነገር ያለው አፍሪካ ውስጥ ነው።ሌሎች ሀገራት ለዘመናት ሲሰጡን የነበረው ከእኛው የወሰዱትን ነው። ባለን ልክ አጠቃቀም አልቻልንም። ካለፈው በመማር መጪዋን አፍሪካ መታደግ ከሁላችን የሚጠበቅ ይሆናል፡፡

አፍሪካ ራሷን ችላ መቆም አለባት። የአፍሪካ ሕብረት ደግሞ በአንድነቱና በምክረ ሀሳቡ አፍሪካ የምትነሳበትን መላና መፍትሄ መፍጠር ለነገ የማይለው የቤት ስራው ነው። በአፍሪካ ጉዳይ ላይ ወደ ኋላ የማይሉ አዲስ አስተሳሰቦችን፣ አዲስ ትውልዶችን ማፍራት ይጠበቅበታል። በአህጉሪቱ ጉዳይ ላይ የማይናወጥ አቋም መገንባት በይደር የማይተው አበይት ጉዳዩ ሆኖ ከዛሬ ወደነገ መሄድ አለበት፡፡

አፍሪካ ራሷን መፍጠር፣ ታሪኳን እንደ አዲስ መጻፍ፣ በቤቷና በርስቷ ላይ ዳግማዊ ወረራን መፍቀድ የለባትም። ለምንድነው የምንከሽፈው? ተነጋግረን ተወያይተን ለውጥ የማናመጣው ለምንድነው? የአፍሪካ ሕብረት አፍሪካን ከስቃይ መታደግ ያልቻለው ለምንድነው? መግደልና መሞት በዋጀው በአንድ አይነት ርዮተ ዓለም ስለምን? እኚህ ጥያቄዎች መልስ ይፈልጋሉ።

ጥያቄዎቹ በፍጥነት መልስ ሊያገኙ ይገባል። የአፍሪካን ችግሮች በዘላቂነት መቅረፍ የሚቻለው ለነዚህ ጥያቄዎች ተገቢውን መልስ መስጠት ሲቻል ነው። ተጠቃሚነታችን ለሌሎች አሳልፈን መስጠት አይኖርብንም። እጣ ፈንታችን ከእኛው በእኛው ለእኛ ሆኖ እንዲቀጥል አፍሪካ ሕብረት ከመቼውም ጊዜ በላይ በርትቶ መስራት ይኖርበታል።

አህጉሩን ከዘመናዊ ባርነት ለመታደግ፣ ከኢኮኖሚና ከመሰል ጥገኝነት ተላቆ ራስን በቻለ ፖለቲካና የአመራር ክህሎት ወደፊት ለማስቀጠል የአፍሪካን ችግር በአፍሪካውያን በሚል እሳቤ መንቀሳቀስ አንዱና ዋነኛው የመፍትሄ ሀሳብ ነው። የአፍሪካ የነጻነት ትንሳኤ ያለው በአፍሪካውያን ትብብር ውስጥ ነው።

የሕዝቦቿ ተጠቃሚነት የተቀመጠው በሕዝቦቿ አንድነት ውስጥ ነው። ራሳችንንም ታሪካችንንም ከጣልቃገብነት ለመጠበቅ የትብብር መንፈስን መላበስ ይኖርብናል። ‹‹የአንተ ቤት ሲንኳኳ እኔ ቤት ይሰማል..›› እንደሚባለው፤ የአንዱን ሕመም አንዱ በመታመም ራሳችንን ነጻ ማውጣት አለብን።

የትብብር መንፈስ የማይፈጥረው ተዓምር የለም። የአንድነት መንፈስ ልክ እንደ አድዋ ሁሉ አሁንም በአፍሪካ ላይ ጣልቃ ገብነትን የሚሽር ነው።መልስ የሚፈልጉ ብዙ አፍሪካዊ ጥያቄዎች ቢኖሩም የነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች መነሻ ማዕከል ግን አንድነት ነው። በተለይ አሁን ላለንበት ቀጠናዊና አህጉራዊ ተግዳሮት ሕብረት የወለደው አንድነት ግድ የሚልበት ሰሞን ላይ ነን።

የችግሮቻችን መፍቻ ቁልፍ ውይይት ነው። አፍሪካ አንድ ስትሆን ችግሮቻችን አቅም አይኖራቸውም። የተሸነፍነው ችግሮቻችንን በራሳችን መፍታት አቅቶን ለሌሎች አሳልፈን በመስጠታችን ነው። የተረታነው በመነጋገር ወደሰላም ከመምጣት ይልቅ ጦርነትን የመፍትሄ አካል አድርገን ስለተቀበልን ነው። በኢትዮጵያ የነጻነት ተጋድሎ መላውን አፍሪካ ከባርነት ማውጣት ከተቻለ በመላው አፍሪካ አንድነትና ሕብረት ምን ሊፈጠር እንደሚችል መገመት አይከብድም፡፡

አሁንም በጅምር የቆሙ ነጻነቶቻችንን በእጃችን ማስገባት ይኖርብናል። የተሟላ ነጻነት ያስፈልገናል…ገና ከምንፈልገው የነጻነት ጥግ አልደረስንም።ካለ ማንም ርዳታና እገዛ በራሳችን የምንቆምበት ጊዜ፣ በራሳችን እውቀትና ጥበብ ወደ ፊት የምንራመድበት ጊዜ ይናፍቀናል።ይሄ ሁሉ እንዲሆን ፖለቲካና ኢኮኖሚያችንን ለራሳቸው እንዲመች አድርገው ልንሰራው ይገባናል፡፡

አፍሪካውያን ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የሚተርፉ በርካታ ልጆች አሏቸው። መያያዝና መቀራረብ ከቻልን የማንፈታው የችግር ቋጠሮ አይኖርም። የአፍሪካ ሕብረት በሀገራት መካከል የአንድነትና የትብብር መንፈስን በመጓዝ በአጭር ጊዜ የምንናፍቃት አፍሪካ ተፈጥራ ማየት የምንችልበትን እድል መፍጠር ይችላል።

የሕብረቱ መሪዎች በምክረ ሀሳባቸው የአፍሪካ ሕዝባችን የጋራ መሻት እውን ለማድረግ ከፍ ባለ የኃላፊነት መንፈስ መንቀቀሳቀስ ይኖርባቸዋል።ለዚህ የሚሆን ቁርጠኝነት መፍጠር ይጠበቅባቸዋል። የምንፈልጋት ታላቋ አፍሪካ የምትፈጠረው በታላቅ ሀሳብና በታላቅ ተግባር ውስጥ ነው።ይሄ እንዲሆን ታላቅ አቅም የሚፈጥር የወዳጅነት መንፈስን ከሁሉ አስቀድመን እንላበስ። ሰላም!

አዲስ ዘመን  የካቲት 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You