አፍሪካውያን ትልልቅ አእምሮዎችን ማክበር እና ማወደስ አለብን!

አፍሪካውያን በቀደሙት ዘመናትም ሆነ አሁን ከፍ ያለ የሃሳብ ልዕልና ያላቸው መሪዎችን ማፍራት ችለዋል። እነዚህ መሪዎች ከፍ ያሉ ሃሳቦችን በማንሳት ለአህጉሪቱ እና ለሕዝቦቿ ብሩህ ነገዎችን ለመፍጠር በቁርጠኝነት ተንቀሳቅሰዋል። ሕይወታቸውን የጠየቀ መስዋእትነትም ከፍለዋል። ለእነዚህ መሪዎች ተገቢውን ክብር መስጠት ስላልተቻለ ዛሬም አፍሪካ የባለ አእምሮ ችግር ያለባት አህጉር አድርገው የሚገምቱ ጥቂት አይደሉም።

በተለይም የምዕራባውያን መገናኛ ብዙሃን በስፋት አፍሪካንና ሕዝቦቿን ከሚያዩበትና ከሚዘግቡበት የተጣመመ (የተዛባ) ትርክት አንጻር፣ ዓለምአቀፉ ኅብረተሰብ ስለ አህጉሪቱ ያለው እሳቤ በእጅጉ የተሳሳተ ነው። ይህ ደግሞ በአህጉሪቱ ዛሬዎች ላይ እየፈጠረ ያለው ሁለንተናዊ ተጽእኖ ቀላል አይደለም።

በአብዛኛው የምዕራቡ ዓለም የመገናኛ ብዙኃን የሚሠሯቸው ዘጋቢ ፊልሞች የአፍሪካ መሪዎችን አስተሳሰብ ከፍታ ሳይሆን ክፋትና ዘራፊነት … ወዘተ ነው። ከዚህ አልፈው ትውልዶችን ማሻገር የሚያስችሉ አፍሪካውያን ጥልቅ አእምሮዎች መናገር እና እነሱን ማወደስ አይፈልጉም።

እንደ አጼ ምኒልክ ያሉ የታላቅ ሕዝብ ታላቅ መሪ፣ እንደ ኩዋሜ ኒኩሩማ ያሉ የነፃነት ታጋዮችን፣ እንደ ጁሊየስ ኒሬሬ ያሉ ዴሞክራት መሪዎችን፣ እንደ አጼ ኃይለሥላሴ ያሉ የአህጉሪቷን አባቶችን … ወዘተ አንስተው ለዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ለመናገርና ለማሳወቅ ድፍረቱ የላቸውም።

ይህ ዛሬ ላይ ጭምር ያልተሻገርነው አፍሪካዊ ችግራችን በዋንኛነት እኛን የሚመለከት ስለመሆኑ ለመናገር የሚከብድ አይደለም። እኛ አክብረን ከፍ ያላደረግናቸውን አእምሮዎቻችንን ሌሎች እንዲያከብሩዋቸው፤ በአደባባይ እንዲያወድሷቸው መጠበቅ የዋህነት፤ ከዚያም በላይ ከእኛ አንጻር ቂልነት ነው።

የዚህ ጽሑፍ ዓላማ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለብንን ክፍተት ማየት ሳይሆን ክፍተቱን ለመሙላት መሞከር ነው፣ ለዚህም ሳምንቱ የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ የሚካሄድበት መሆኑን እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ የኅብረቱ መሥራች እና የነፃነት ታጋይ የነበሩ የአፍሪካ መሪዎችን እናስታውስ፤ እናወድስ።

የአፍሪካ መሪዎች የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን የመሠረቱት ብዙ የውስጥ እና የውጭ ጫናዎችን ተቋቁመው ነው። በዚህ የመሰባሰብ ሂደት ኢትዮጵያ እንደ አንድ ነፃ መንግሥትና ሕዝብ፤ ከዚያም ባለፈ ዘመናት ያስቆጠረ የሀገረ መንግሥት ትርክት ባለቤት በመሆን፤ ያበረከተችው አስተዋጥኦ በኅብረቱ ምስረታ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ነው።

የወቅቱ የኢትዮጵያ መሪ የነበሩት ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ኅብረቱን ለመመስረት በተደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው። አሁን ላለው አፍሪካዊ ትውልድ ባለ ውለታ ስለመሆናቸውም የታሪክ ተመራማሪዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መፈጠሩ በራሱ ያበረከተውን አስተዋጽኦ ለተረዳው ማረጋገጫ የሚጠይቅ አይደለም።

የዛየር (ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ) መሪ የነበረው ፓትሪስ ሉሙምባ ያሉ የነፃነት ታጋዮች አፍርታለች። ሉሙምባ ለዛየራውያን ጥልቅ ህልም አልሞ በህልሙ ምክንያት ለሞት የተዳረገ አፍሪካዊ ባለ ጥልቅ አእምሮ ነው። ይህን ተጨባጭ እውነታ ከመናገር ይልቅ አፍሪካውያን ሳይቀር መናገር የሚፈልጉት የሚቀናቸውም፤ የዛየር አምባገነን መሪ ስለነበረው ሞቡቱ ሴሴ ሴኮ ነው፡፡

በእርግጥ ብዙ የአፍሪካ መሪዎች አምባገነኖች ናቸው። ሥልጣን የሚለቁት በተፈጥሮ ኃይል ወይም በመፈንቅለ መንግሥት ነው። ዳሩ ግን አፍሪካ ለዓለም አርዓያ የሚሆን ሥራ የሠሩ እና የሚመሰገኑ መሪዎችም አሏት። ለዚህም፤ የታንዛኒያ መሪ የነበሩት ጁሊየስ ኒሬሬ ሥልጣን የለቀቁት በራሳቸው ፈቃድ ነው።

ከ32 የአፍሪካ አንድነት መሥራቾች አንዱ የነበሩት የካሜሮኑ መሪ አህማዶ አህዲጆ ‹‹አሁን ያለሁበት የጤና ሁኔታ ሀገር ለመምራት የሚያስችል አይደለም›› በማለት በራሳቸው ፈቃድ ሥልጣን የለቀቁ ናቸው። በተመሳሳይ ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት መሥራቾች አንዱ የነበሩት የሱዳኑ መሪ ኢብራሂም ሥልጣናቸውን በፈቃዳቸው ለቀዋል። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን የነዚህ አፍሪካውያን ታሪክ አይታወቅም።

በ21ኛው ክፍለ ዘመን የዓለም የሥልጣኔ እና የዴሞክራሲ ቁንጮ ናት የምትባለው አሜሪካ ብዙ የምርጫ ማጭበርበር ሲወራባት፤ የአፍሪካዊቷ ሀገር ታንዛኒያ መሪ ጁሊየስ ኒሬሬ ግን በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ሥልጣን በራሳቸው ፈቃድ ለቀው ለዓለም ምሳሌ ሆነዋል። ሆኖም ግን አፍሪካ ውስጥ የሚደረግን በጎ ነገር ማመስገን የማይቀናቸው የምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃኖች፤ ጁሊየስ ኒሬሬን ለማመስገን ቃል አላገኙም።

ከዚያ ይልቅ ዘጋርዲያን ጨምሮ አብዛኞቹ የምዕራባውያን ጋዜጦች በክስተቱ ዙሪያ ከሠሯቸው ዘገባዎች፤ ኒሬሬ በሀገሩ ሕዝብ የማይወደድ፣ ሶሻሊዝምን አሰርጻለሁ ብሎ ሀገሩን ድህነት ላይ የጣለ አድርገው ነው። እውነታው ግን ከዚህ በተጻራሪ ኒሬሬን የሀገሩ ሕዝብ ‹‹ሙዋሊሙ›› እያለ ይጠራው እንደነበር ነው።

ሙዋሊሙ ማለት በእስዋሂሊ ‹‹መምህራችን፣ አባታችን›› እንደማለት ነው። ‹‹ዴሞክራሲ በራስህ ሀገር ዓውድ የምታዳብረው እንጂ እንደ ኮካ ኮላ ከውጭ የምትገዛው አይደለም›› በሚለው ንግግሩ የሚታወቀው ኒሬሬ ፤ ሶሻሊዝምን እንደ ወረደ መቀበል ሳይሆን ከታንዛኒያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር እንዲጣጣም ያደረገ አፍሪካዊ ባለ ትልቅ አእምሮ፤ በሀገሩ ሕዝብም ምስጋና የሚቸረው ነው።

እነ ኔልሰን ማንደላ፣ ኩዋሜ ኒኩሩማህ፣ ጆሞ ኬንያታ፣ ሴዳር ሴንጉር፣ ኬኔት ካውንዳ የመሳሰሉት የአፍሪካ መሪዎች የውጭ ወራሪን በመታገል ለአፍሪካ ሀገራት ነፃነት ውለታ የዋሉ ናቸው። እንደነ ሳሞራ ማሼል፣ ሮበርት ሙጋቤ የመሳሰሉት በአገዛዛቸው «አምባ ገነን» የነበሩ ቢሆንም ሀገራቸውን ከውጭ ብዝበዛ ነፃ ለማድረግ ሲጋፈጡና ሲታገሉ የነበሩ ናቸው።

እንደነ ቶማስ ሳንካራ የመሳሰሉት ‹‹አፍሪካዊ ቼ ጉቬራ›› የሚል ቅጽል ስም የተሰጣቸው አብዮተኞችንም አፍሪካ አፍርታለች። እነዚህን ማስታወስ፤ ሃሳባቸውንና ከዚህ ለመነጨው ሥራቸው እውቅና መስጠት፤ ማክበርና ማወደስ የዚህ ትውልድ ኃላፊነት ነው። የራሱን ጀግኖች ለማወደስ አቅም የማይኖረው ትውልድ ራሱን ጀግና ያፈራል ብሎ ማሰብ «ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ እንደሚባለው» ከመሆን ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም ።

ሚሊዮን ሺበሺ

አዲስ ዘመን  የካቲት 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You