ከኢትዮጵያኒዝም እስከ አፍሪካ ሕብረት

እ.ኤ.አ ከ1884-1885 በጀርመኑ ቻንስለር ኦተቨን ቢስማርክ መሪ ተዋናይነት በበርሊን ከተማ አንድ ጉባዔ ተካሄደ፡፡ “ተመሳሳይ ክንፍ ያላቸው ወፎች በአንድ ላይ ይበራሉ” እንዲሉ ጉባኤውን ያካሄዱት የአውሮፓ ኢምፔሪያሊስቶች ነበሩ፡፡ በጉባኤውም ቅኝ ገዥ አውሮፓውያን “በመካከላችን ምንም አይነት ሽኩቻ እና ጥላቻ ሳይኖር እንዴት አድርገን አፍሪካን እንቀራመት” ሲሉ መክረዋል፡፡ የአፍሪካን ሁሉን አቀፍ ነጻነቷን አርቀው ለመቅበር ተማምለዋል፡፡

መሀላቸውን እውን ለማድረግ ኢምፔሪያሊስቶቹ መላ አፍሪካን በወረራ ያዙ፡፡ መጋዘኖቻቸው ሞልተው እስኪያፈሱ ድረስ የአፍሪካን የተፈጥሮ ሀብቶች ያለማንም ከልካይ ዘረፉ፡፡ አፍሪካ በውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ዜጎቿ ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቻው በጽንፈኛ ነጮች ተደፈጠጡ፡፡ ይህን ተከትሎ “ባለመድሃኒቱን በሽተኞች ይፈልጉታል” እንዲሉ በአራቱም የዓለም ጫፎች የሚገኙ ጥቁር አፍሪካውያን ለነጻነታቸው መድሃኒት ፍለጋ ተራራውን ገደሉንም መቧጠጥ ያዙ። ቧጠውም አልቀረ ለበሽታቸው መድሃኒት ባይሆንም ማስታገሻ ማግኘት ቻሉ፡፡

የነጻነት ታጋይ አፍሪካውያን የሚያደርጉት ትግል “ያለምግብ መጋቢ፣ ያለውሃ ዋናተኛ” እንዳይሆንባቸው በማሰብ የነጻነት ትግላቸውን ለማሳለጥ የሚረዷቸውን የተለያዩ ድርጅቶችን እና ንቅናቄዎችን መሰረቱ፡፡ በድርጅቶቻቸው ጥላ ስር ሆነው ለነጻነታቸው መታገል ጀመሩ፡፡ ከንቅናቄዎች መካከል “ኢትዮጵያኒዝም”(ETHIOPIANISM) አንዱ እና የመጀመሪያው ነው፡፡ ኢትዮጵያኒዝም በዘመናዊው የቅኝ ግዛት ዘመን ለኃይማኖት እና ለፖለቲካዊ ነፃነት የተነሱትን እንቅስቃሴዎች ያቀፈ፤ ከሰሃራ በታች ባሉ አፍሪካውያን የተደረገ የሃይማኖት እንቅስቃሴ ነው። እንቅስቃሴው የተጀመረው እ.ኤ.አ. በ1880ዎቹ ሲሆን የጀመሩትም በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ “የሚሽነሪ” ሰራተኞች ናቸው፡፡

ዋና ዓላማውም ከአውሮፓውያን ተጽዕኖ ነፃ የሆኑ የመላው አፍሪካ አብያተ ክርስቲያናትን ለማቋቋም የታለመ መሆኑን የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ በነገራችን ላይ ኢትዮጵያኒዝም “በኃይማኖት ብቻ ሊገለጽ የማይችል መሆኑን ፖለቲከኞች እና የታሪክ ጸሐፊዎች ያስረዳሉ። ቃሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመው በደቡብ አፍሪካ የቀድሞው «የዌስሊያ» ቤተክርስቲያን አገልጋይ ማንጌና ሞኮን እኤአ በ1892 የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን (Ethiopian Church) ሲመሰርት ነው፡፡

በደቡብ አፍሪካ የተጀመረውን ንቅናቄ ተከትሎ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የንቅናቄውን ዓላማ የሚያስቀጥሉ አብያተ ክርስቲያናት ተከፈቱ፡፡ ከእነዚህ መካከል በናይጄሪያ የአፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ተብለው የሚጠሩት-የኔቲቭ ባፕቲስት ቸርች እ.ኤ.አ 1888፣ የቀድሞዋ የአንግሊካን ዩናይትድ ቤተኛ አፍሪካ ቤተክርስቲያን እ.ኤ.አ1891 እና የተባበሩት አፍሪካ የሜቶዲስት ቸርች እ.ኤ.አ1917 ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በካሜሩን ተወላጅ ባፕቲስት ቤተክርስቲያን እ.ኤ.አ1887፣ በጋና በናቲቭ ባፕቲስት ቤተክርስቲያን እ.ኤ.አ1898፣ የአሜሪካ ኔግሮ ቤተ እምነት በሮዴዥያ ቅርንጫፍ እ.ኤ.አ1906 ፣ በኬንያ የክርስቶስ ቤተክርስቲያን እ.ኤ.አ1957 እና ሌሎችም የኢትዮጵያንዝም ንቅናቄን ተከትሎ የተከፈቱ አብያተ ክርስቲያናት ናቸው፡፡

በንቅናቄ “Africa for the Africans” “አፍሪካ ለአፍሪካውያን” የሚለው መፈክር በሰፊው ተቀንቅኗል። የአፍሪካውያን የዕምነት ነጻነት እንዲረጋገጥ እና በፖለቲካው ዘርፍም የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እንዲረጋገጥ ሰፊ ስራ ተሰርቷል፡፡ የኢትዮጵያኒዝም ንቅንናቄ መሪዎች እና ተከታዮቻቸው የአፍሪካውያን ኩራት የሆነችውን ኢትዮጵያ “አፍሪካዊት ጽዮን” “Afri­can Zion” እያሉ ይጠሯት እንደነበር፤ ንቅናቄያቸውን ኢትዮጵያኒዝም ብለው እንዲሰይሙ ያደረጋቸው አንደኛው ምክንያት ይኸው ስለመሆኑ የተለያዩ የታሪክ ድርሳናት ያትታሉ፡፡

እ.ኤ.አ በ1896 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን በአጼ ምኒሊክ እየተመሩ ወራሪውን የአውሮፓ ኢፔሪያሊስት ጣልያን በአድዋ ጦርነት ድል መንሳታቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያኒዝም ንቅናቄ በከፍተኛ ደረጃ ጎመራ። የኢትዮጵያኒዝም የተሰኘውን ቃል የሚጠቀሙ አፍሪካውያን ቁጥር በእጅጉ ጨመረ፡፡ እዚህ ላይ አንድ ልብ ሊባል የሚገባው ቁም ነገር ያለ ሲሆን ይህም በኢትዮጵያኒዝም እና በኢትዮጵያ ያለው ቁርኝት ምን እንደሚመስል ነው፡፡ ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው የኢትዮጵያኒዝም ንቅናቄ ኢትዮጵያን “አፍሪካዊት ጽዮን” “African Zion” እያሉ የጀመሩት ስለመሆኑ እና የአድዋን ድል ተከትሎ ኢትዮጵያኒዝም (Ethio­pianism) ከኃይማኖታዊነት ትግል ባለፈ ለጥቁሮች ፖለቲካዊ ነጻነት ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ነው፡፡

“አብዮት በፍጥነት እና በጥልቀት በሰላማዊ ጊዜ የማይታመን የማይመስለውን በፖለቲካ እድገት ማምጣት ያስችላል፡፡ ከሁሉም በበለጠ አብዮት ፖለቲካዊ ከፍታን የሚያመጣው ለመሪዎች ብቻ ሳይሆን ለሰፊው ሕዝብ ጭምር መሆኑ ነው፡፡ ” ይህ የሌሊን አባባል በኢትዮጵያኒዝም ንቅናቄ የተፈጠረውን የፖለቲካዊ ጽንሰ ሃሳብ አረዳድ ዕድገት በትክክል ገላጭ ነው፡፡ ኢትዮጵያኒዝም (Ethiopianism) የፈጠራቸው መነቃቃቶች እና የፖለቲካ ጽንሰ ሃሳብ አረዳድ በሌላው ዓለም የሚኖሩ ጥቁር ሕዝቦች ሌሎችን ንቅናቄዎች እና ድርጅቶች እንዲመሰርቱ እርሾ ነበር፡፡ ከእነዚህ የሕዝብ እንቅስቃሴዎች መካከል ፓን አፍሪካኒዝም በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ ነው፡፡

ፓን አፍሪካኒዝም (Pan Africanism) ከሁለት ቃላት የተዋቀረ ነው፡፡ ፓን (Pan) የሚለው ቃል የግሪክ ሲሆን ሁሉም (All) የሚል ትርጉም አለው። ስለሆነም ፓን አፍሪካኒዝም (Pan Africanism) ማለት ደግሞ ሁሉም አፍሪካ (All Africa) የሚል ትርጉም ይሰጣል፡፡ ፓን አፍሪካኒዝም (Pan African­ism) የተሰኘው ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ የተጀመረው ሁለት ዐብይ ጉዳዮችን ለማሳካት ነው፡፡ የመጀመሪያው የአፍሪካውያንን አንድነት (African Unity) ለማምጣት ያለመ ነው፡፡

ይህ ሲባል ከአፍሪካ ውስጥ የሚኖሩትን አፍሪካውያንን ብቻ ሳይሆን የዘር ሀረጋቸው ከአፍሪካ የሚመዘዙትን በመላው ዓለም የሚኖሩ ጥቁር ሕዝቦችን አንድ ለማድረግ ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ ሌላኛው የፓን አፍሪካኒዝም ዓላማ ደግሞ ሁሉም በውጭ የሚኖሩ አፍሪካውያንን በተለይም በሰሜን አሜሪካ፣ በላቲን አሜሪካ እና በትሪንዳድ (West indies) የሚኖሩ ጥቁሮችን የጋራ ወድማማችነት (Common Brother­hood ) ለመፍጠር ትኩረት ያደረገ ነው፡፡

ፓን አፍርካኒዝም የሚለው ጽንሰ ሀሳብ የተወለደው ወይም የተፈጠረው ከአፍሪካ ውጭ ሲሆን የፈጠሩትም የዘር ግንዳቸው ከአፍሪካ የሚመዘዝ በአሜሪካ እና በካሪቢያን የሚገኙ ጥቁሮች ናቸው፡፡ እነዚህ ሕዝቦች ከእናት አህጉራቸው አፍሪካ በግፍ የተወሰዱ ስለነበሩ በሚኖሩባቸው ሀገራት ራሳቸውን እንደባይተዋር የሚቆጥሩ ነበሩ፡፡ እንደዚህ እንዲያስቡ ያበቃቸው ደግሞ በጽንፈኛ ነጮች የሚደርስባቸው መገለል እና መድሎ ነበር፡፡

ይህን ተከትሎ እነዚህ ዜጎች ከሌሎች ሕዝቦች ጋር እኩል እንዲሆኑ አጥብቀው ይፈልጉ ነበር። በምዕራባውያን የተነጠቁትን ፍትህ ለማግኘት አጥብቀው ታገሉ፡፡ በፓን አፍሪካኒዝም የመጀመሪያዎቹ እንቅስቃሴዎች በጥቁርነት የሚደርስን ዘረኝነት የሚቃወሙ ነበር፡፡ እንቅስቃሴ መሬት የረገጠ ለማድረግ መሪዎቹ በተለያዩ ክፍለ ዓለማት በርካታ ኮንፈረንሶችን አካሂደዋል፡፡ የመጀመሪያው ፓን አፍሪካኒዝም ስብሰባ የተካሄደው በእንግሊዝ ለንደን እ.ኤ.አ በ1900 ነው፡፡ ስብሰባውም የተደራጀው በትሪንዳዱ (West indies) የሕግ ባለሙያው ሲልቬስተር ዊሊያምስ ነበር፡፡ ይህ ኮንፈረንስ ከኢትዮጵያኒዝም ንቅናቄ ከተጀመረ ማግስት በመሆኑ ከጥቁር ሕዝቦች ጋር ተያይዘው የሚነሱ በርካታ ጥያቄዎችን ለመመለስ ጥረት ተደርጎበታል፡፡

ፓን አፍሪካኒዚም ሁለት ታዋቂ መሪዎች የነበሩት ሲሆን አንደኛው በሀገረ አሜሪካ ነዋሪ የነበረው ተመራማሪ እና ጸሐፊ ዶክተር ዱ ቦይስ ነው፡፡ ዶክተር ቦይስ የፓን አፍሪካኒዚም አባት በመባል ይታወቃል፡፡ ሌላኛው የፓን አፍሪካኒዝም መሪ ደግሞ ጃማይካዊው ማርከስ ጋርቬይ ሲሆን አሜሪካ ይኖር የነበረ የነጻነት ታጋይ ነው፡፡ ሕይወቱ ያለፈውም በጽንፈኛ ነጮች በተፈጸመበት የጭካኔ ግድያ ነበር፡፡

ጋርቬይ የዓለም አቀፍ ኔግሮ አሶሴሽን (Univer­sal Negro Association) መስራች እና መሪ ነበር፡፡ ሁለቱም የፓን አፍሪካኒዝም መሪዎች ቢሆኑም ሁለቱም ግን በአፍሪካውያን የወደፊት እጣ ፋንታ ላይ መሰረታዊ ልዩነቶች ነበሯቸው፡፡ ዱ ቦይስ ከአፍሪካ ውጭ የሚኖሩ አፍሪካውያን በአፍሪካ ውስጥ ለሚኖሩ አፍሪካውያን በመታገል የመላ የጥቁር ሕዝቦችን መብት ማስጠበቅ ይቻላል የሚል ነበር፡፡ ጋርቬይ በበኩሉ የአፍሪካውያንን መብት ለማስከበር ከአፍሪካ ውጭ የሚገኙ ጥቁር ሕዝቦችን በሙሉ ወደ አፍሪካ መመለስ አለባቸው የሚል ነው፡፡

ጋርቬይ ወደ አፍሪካ መመለስ (Back to Africa Movement) ያደራጅ ነበር፡፡ ይህን ለማሳለጥ ይረዳው ዘንድ ዩኒቨርሳል ኔግሮ ኢምፕሩቭመንት አሶሴሽንን (Universal Negero Improvement Association) እኤአ በ1914 አቋቁሞ ሰርቷል፡፡ እኤአ 1945 ለፓን አፍሪካኒዝም አዲስ እና ወሳኝ ምዕራፍ የተከፈተበት ወቅት ነበር፡፡ በዚህ ዓመት አምስተኛው የፓን አፍሪካኒዝም ስብሰባ በእንግሊዟ ማንቸስተር ከተማ ተካሂዶ ነበር፡፡ ይህ ኮንፈረንስ በሁለት መልኩ የተለየ ያደርገዋል፡፡

ከዚህ በፊት በነበሩ ኮንፈረንሶች ከአፍሪካ የመጡ ግለሰቦች እና ቡድኖች ተሳትፈው የማያውቁ ሲሆን በዚህ ኮንፈረንስ ግን ከአፍሪካ የመጡ በርካታ የነጻነት ታጋዮች ተሳትፈው ነበር፡፡ ከእነዚህ መካከል የጋና ፕሬዚዳንት ኩዋሜ ኑክሩማህ እና የኬንያ ፕሬዚዳንት ጆሞ ኬንያታ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህ ታዋቂ ግለሰቦች በስብሰባው የተገኙት የጋና እና የኬንያ መሪ ሳይሆኑ በፊት ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ቁልፍ ሚና የተጫወቱ ናቸው፡፡ ሁለተኛው የዚህ ኮንፈረንስ ወሳኝነት ደግሞ ሁሉም አፍሪካዊ ለአፍሪካ ነጻነት ሊተባበር ይገባል የሚል አቋም የተያዘበት እና አፍሪካን ነጻ ለማውጣት መሬት የረገጠ እንቅስቃሴ የተጀመረበት መሆኑ ነው፡፡

ጉባኤውን ተከትሎ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ነጻ ወጡ፡፡ ነጻ ለመውጣታቸው ትልቁ ሚስጥር ተደርጎ የሚወሰደው ከቅኝ ገዥ ሀገራት ጎን በመሆን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተሳትፎ የነበራቸው አፍሪካውያን በጦርነቱ የነበራቸውን ልምድ መጠቀም መቻላቸው ነው፡፡ ምንም እንኳን በርካታ ሀገራት ከቅኝ ገዥዎች ነጻ ቢወጡም የአውሮፓ ኢፔሪያሊስቶችን ሴራ ለመበጣጠስ አቅም ያለው አልነበረም፡፡ ነጻ የወጡ ሀገራት ሁሉም (All Africa) “ሁሉም አፍሪካ” የሚለውን አፍሪካኒዝም መርህ መላበስ ተሳናቸው፡፡ ይባስ ብሎም አፍሪካውያንም ካዛብላንካ እና ሞኖሮቢያ ተብለው ለሁለት ጎራዎች ተከፈሉ፡፡

“እርስ በዕርስ የማይስማማ ሕዝብ ለጠላት አመቺ ነው” እንዲሉ በሁለት ጎራ የተከፈሉት አፍሪካውያንም ለአውሮፓ ኢምፔሪያሊስቶች ሁሉን ነገር ሰርግ እና ምላሽ አደረገላቸው፡፡ ኢምፔሪያሊስቶቹ አፍሪካውያን አንድ እንዳይሆኑ የክፋት መርዛቸውን (poison Evil) በረቀቀ መልኩ በአፍሪካውያን ላይ ተፉ፡፡ በዚህ ጊዜ ነው እንግዲህ! “ሰው ማለት ሰው በጠፋ ጊዜ ሰው ሆኖ መገኘት” የተባለውን አባባል አጼ ኃይለሥላሴ በተግባር የፈጸሙት፡፡

አጼ ኃይለሥላሴ የአውሮፓውያንን ሴራ ቀድመው በመረዳት በሁለት ጎራ የተከፈሉትን አፍሪካውያንን አንድ በማድረግ የፓን አፍሪካኒዝም መርህ የሆነውን ሁሉም አፍሪካ (All Africa) በማስቀጠል የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረት አድርገዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ለጥቁር ሕዝቦች ነጻነት በተደጋጋሚ በምሳሌነት ሲጠቀሱ በተመለከትኩ ቁጥር በ1927 ዓ.ም የኦስትሪያ ኢትዮጵያ ዲፕሎማት የነበረው ፕሮችስካ የባሩድ በርሜል በተሰኘው መጽሀፍ ላይ ያሰፈረውን አንድ ሃሳብ ያስታውሰኛል፡፡

ፕሮችስካ እንዲህ ይላል “ሁሌም ኢትዮጵያን የቀን ተቀን የፖለቲካ ማዕከል ያደረጋት የአውሮፓውያን የቅኝ ገዢነት መስፋፋት ጉጉት ሳይሆን ያገሬው ዜጎች በዓለም ላይ ካለው የፖለቲካል ኢኮኖሚ ሁኔታ ጋር ራሳቸውን ለማጣጣም ያላቸው ፍላጎት እና ስልጣኔያቸው እንደ አውሮፓዊያን መሆኑ ነው፡፡” በመጨረሻም በታሪክ ቅብብሎሽ አባቶቻችን ያቆዩትን ጠንካራ የነጻነት ተምሳሌትነት አሻራ እንዳይደበዝዝ የአሁኑ ትውድልም የበኩሉን መወጣት የውዴታ ግዴታው ሊሆን ይገባል። እንላለን ሰላም!

 

 

ሙሉቀን ታደገ

አዲስ ዘመን  የካቲት 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You