አፍሪካ ኅብረት ከዴሞክራሲና ከዴሞክራሲ ምርጫ ባህል መጎልበት አንጻር

ዴሞክራሲ በሰፈነበት ሀገር ሕዝብ መብቱ መከበሩን የሚያረጋግጥበት ዓይነተኛ ዘዴ ሕጋዊ ምርጫ ነው። ማንኛውም ምርጫ የሕዝብን ፍላጎት መጠየቂያ ነፃ የሆነ የዴሞክራሲ መንገድ እንጂ የመርሀ ግብር ማሟያ አይደለም፡፡ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ ደግሞ በተለይም በሁነቱ መሸነፍና ማሸነፍ እንዳለ የሚገነዘብ መራጭ ሕዝብ፣ መንግሥትና ተፎካካሪ ፓርቲ ያስፈልጋል፡፡

የማንኛውም ሀገር የመንግሥት ሥልጣን ሊመነጭ የሚገባውም ወቅቱን በጠበቀ መልኩ በሚካሄድ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በአብላጫ ድምፅ የሕዝብ ፈቃድ ማግኘት ሲቻል ነው። ከዚህ ውጪ ሀገር የማስተዳደር መንበረ ሥልጣንን በኃይል የመንጠቅ ተግባር ፀረ ዴሞክራሲያዊ መሆኑም የሚያከራክር አይደለም፡፡

መሻሻሎች እንዳሉ ሆነው፤ ከቅኝ ግዛት ፍቺ አንስቶ በአህጉራችን አፍሪካ ዴሞክራሲያዊ የሥልጣን ሽግግርን እውን ለማድረግ በተለይም ሃሳብን በመሸጥ የመሪነት ወንበር ላይ አሸናፊ ሆኖ መውጣት እንደሚቻል ከማረጋገጥ አንፃር ሰፊ ክፍተቶች እንዳሉ ለመናገር የሚከብድ አይደለም፡፡

በአፍሪካ ከነፃነት ማግስት ጀምሮ በአንድም ይሁን በሌላ በቅኝ ገዥዎች ይሁንታ፤ በመፈንቅለ መንግሥት እና በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ወደ ሥልጣን የመጡ መሪዎችን አስተናግዳለች። በተለይም በቅኝ ገዥዎች ይሁንታ እና በመፈንቅለ መንግሥት ወደ ሥልጣን የመጡ መሪዎች በአህጉሪቱ ለተፈጠሩና እየተፈጠሩ ላሉ ሁከቶችና ብጥብጦች ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው።

የአፍሪካ ኅብረት በአንፃሩ ፀረ ዴሞክራሲያዊ የሆኑ መሰል ሕገ ወጥ ተግባራትን ፈፅሞ እንደማይታገስ በተደጋጋሚ ሲገልፅ ቆይቷል፡፡ ከፍ ሲልም አንዳንድ እርምጃዎችን ሲወስድ ተመልክተናል፡፡ ይህም ሆኖ ግን ተግባሩን ማስቆም አልሆነለትም፡፡

ኅብረቱ ፀረ ዴሞክራሲያዊው መንገድ ፈፅሞ ተቀባይነት የሌለው ስለመሆኑም በተጨባጭ ለማረጋገጥም በቶጎ ሎሜ በአውሮፓውያኑ 2000 ላይ ኢ-ሕገመንግሥታዊ ለውጦችን የሚቃወመውን ”Lomé Convention” ወደ ሥራ አስገብቷል፡፡

በዚህ ኮንቬንሽንም በአንድ ሀገር ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን በኃይል መናድና መንግሥትን መቀየር እጅጉን አጥብቆ የተከለከለ ስለመሆኑና ኅብረቱም መሰል ሕገ ወጥ ተግባር በተፈፀመበት ሀገርና ፈፃሚዎች ላይ ሁለተናዊ የእግድ ውሳኔን የማስተላለፍ ሥልጣን እንዳለው ተመላክቷል፡፡

የዚህ ኮንቬንሽን መውጣትም ፀረ ዴሞክራሲ ተግባሩ እንዲቀንስ በማድረግ ረገድ ተጨባጭ ለውጥን አሳይቷል፡፡ ለአብነት እኤአ 1952 እስከ 2014 በአህጉሪቱ 88 መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የተካሄደ ሲሆን ኮንቬንሽን ከወጣ ወዲህ ግን ቁጥሩ ከ12 አልተሻገረም፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መፈንቅለ መንግCት ማድረግ የተለመደ ብሎም የተፈቀደ ተግባር መመሰል ጀምሯል። ባሳለፍነው አመት ብቻ በኒጀር እና ጋቦን መፈንቅለ መንግሥት ተካሂዷል፡፡ ፈፃሚዎቹም ለሎሜው ኮንቬንሽንም ሆነ ለአፍሪካ ኅብረት ምንም ዓይነት አክብሮት እንደሌላቸው በተጨባጭ በመፈንቅለ መንግሥቱ አሳይተዋል፡፡ ኅብረቱ ግን ለተፈፀመው የሕግ ጥሰት / ኢ-ዴሞክራሲያዊ ተግባር ከቃልና መገለጫ ጋጋታ የተሻገረ እርምጃ ሲወስድ አልታየም ፡፡

ከኅብረቱ ባለፈም ኃያላን መንግሥታት የጂኦ- ፖለቲካ ፍላጎት ፉክክር ለመፈንቅለ መንግሥት ፈፃሚዎቹ የልብ ልብ እየሰጣቸው እንደሆነም ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ የተለያዩ የውጭ ኃይሎችም ለመሻታቸው ተፈፃሚነት እነዚህን ኃይሎች ከፊት እንደሚያሰልፉ፤ ከሕገ ወጥ ተግባሩ ጀርባም በቀጥታም ይሆን በተዘዋዋሪ እጃቸው እንዳለበት በግልፅ እየተስተዋለ ነው፡፡

በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አንዳንድ ምዕራባውያንና የዐረብ ሀገራት በአፍሪካ ያላቸው ፍላጎትና ጣልቃ ገብነት በግልጽ እየታየ መጥቷል። የሀገራቱ በአፍሪካ ጉዳያቸውን የሚያስፈፅምላቸው ተላላኪ መንግሥት መፍጠር ፍላጎትም ፀረ ዴሞክራሲ ተግባሩም ሆነ ጣልቃ ገብነታቸው እንዲጨምር ዓይነተኛ ምክንያት የሆነ ይመስላል።

አንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራትም ፈፃሚዎቹን ከማውገዝ ብሎም በኃይል ለተቀመጡበት መንበር እውቅና ከመንፈግ ይልቅ ቀይ ምንጣፍ አንጥፈው ታላላቅ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉባኤዎች ብሎም የትብብር ስምምነቶች ላይ እንዲታደሙ ሲጋብዟቸው ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡

ከዚህ ባለፈ መፈንቅለ መንግሥት በተካሄደ ማግስት ሀገራት ሕገ ወጥና ፀረ ዴሞክራሲ ስለመሆኑ ከመግለፅና አንድ አቋም ከመያዝ ይልቅ የኅብረቱ ብሎም ቀጣናዊ አባል ሀገራት በተናጠል ጉዞ እግራቸው ወደ መራቸው ለመሮጥ ሲጣደፉም ይስተዋላል፡፡ አንዳንዶች ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትን የመሳሰሉ ከባድ ውሳኔዎች ሲያስተላልፉ፣ ሌሎች በአንፃሩ ‹‹በጠረጴዛ ዙሪያ ችግሩን ለመፍታት ብንጥር ይሻላል›› በሚል ወንበር ስበው ለመደራደር ሲንቀሳቀሱ እየተመለከትን እንገኛለን፡፡

ከሕግ እና ሥርዓት እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ መንገድ ውጪ በመራመድ ሥልጣን ለመያዝ የሚደረግ ሩጫ በተለያዩ ሀገራት ከባድ ቀውሶች ምንጭ የበርካታ ንፁሃን ሞት፣ የሚሊዮኖች ከቤት ንብረት መፈናቀልና ስደት ምክንያት እየሆነ ይገኛል። የአፍሪካ ኅብረት መሰል ፀረ ዴሞክራሲያዊ ተግባርን ማስቆም የሚገባው ትክክለኛው ጊዜ ላይ ያለ ይመስላል፡፡ ኅብረቱም ሆነ አባል አገራቱ በ37ኛው ጉባኤ በዚህ ጉዳይ ላይ ቁርጥ ያለና የፀና አቋም መያዝ ይኖርባቸዋል፡፡

የሎሜው ኮንቬንሽን በአግባቡ ማስፈፀምን ጨምሮ ሌሎች ጠንካራ አቋሞችን ማራመድ አለባቸዋል፡፡ በሕግና ደንብ መሠረት በፀረ ዴሞክራሲ ተግባር ላይ ተዋናይ በሆኑ ግለሰቦችም ሆነ በፓርቲዎች ላይ በማያዳግም መልኩ ተገቢና አስተማሪ ቅጣት ሊያስተላልፉም ይገባል፡፡ ኅብረቱ የተናጠልና ጉራማይሌ ሳይሆን ከቀጣናዊ አባል ሀገራት ጋር ተመሳሳይ የሆነ ፅኑ አቋም መያዝም ይኖርበታል፡፡

አንዳንዶችም የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎች መበራከትን ምክንያት ሲያስረዱ መሪዎች በሥልጣን ዘመን ማብቂያቸው ላይ ሕገ መንግሥት ለማሻሻል ከሚያደርጉት ጥረትና ከምርጫና ውጤት ማጭበርበር ጋር ያስተሳስሩታል፡፡ በእርግጥ በምርጫ ሁነት እኩል ውጤት የሚባል የለም፡፡ አንዱ አሸናፊ ሌላው ተሸናፊ መሆኑም የታወቀ ነው፡፡ በምርጫ ሁነት አግባብ ባልሆነ መልኩ ድምፁን የተቀማ ሕዝብና ፓርቲ ብሎም ግለሰብ ሕገ ወጥ ተግባር ላይ ለመሳተፍ እጅጉን የቀረበ ነው፡፡

ከዚህ የተነሳ ኅብረቱ ምርጫ የሚያጭበረብሩ፣ ኮሮጆ የሚሰርቁና ድምፅ የሚቀንሱ መንግሥታትን አደብ ማስያዝ አለበት፡፡ ከዚህ ባለፈ የሥልጣን ዘመን ማብቂያቸው ላይ ሕገ መንግሥት ለማሻሻል የሚታትሩና የሚያሻሽሉት ላይ ኮስተር ያለ አቋም መያዝ ይኖርበታል፡፡

የውጭ መንግሥታት በመሰል ጉዳዮች ላይ ጣልቃ ከመግባት እንዲቆጠቡም ተፅእኖ ማድረግ ግድ ይለዋል፡፡ ከሁሉም በላይ አፍሪካውያን ኅብረትና አንድነታቸውን እንዲሁም የውስጥ ችግሮቻቸውንም በራሳቸው የመፍታት ጅምራቸው በማጠናከር የውጭ ጣልቃ ገብነትን መቋቋም ይጠበቅበታል፡፡

ዴሞክራሲን ማስፈን ከየትኛውም ሀገር በላይ የሕልውና ጉዳይ ነው፡፡ የዴሞክራሲ ልዕልና እውን ሊሆን የሚችለው በተቋማት፣ መንግሥታት አሊያም በመሪዎች ብቻ አይደለም፡፡ ዜጎች፣ ፓርቲዎች፣ መገናኛ ብዙኃንና ሲቪክ ማኅበራትን ጨምሮ የበርካቶች የጋራ ተሳትፎ ጭምር ነው፡፡ ይህ እንደመሆኑም ከኃይል አማራጭ ይልቅ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና መጠናከር ሁሉም የበኩሉን አስተዋፅኦ ሊያበረክት ይገባል፤ የአፍሪካና የአፍሪካውያን ዕጣ ፈንታ የሚወሰነውም በዚህና በዚህ ብቻ ነው ።

ታምራት ተስፋዬ

አዲስ ዘመን  የካቲት 9 ቀን 2016 ዓ.ም

 

Recommended For You