ሕገ-ወጥ ተግባር ሲፈጸምባቸው የተገኙ 49 ማሳጅ ቤቶች ታሸጉ

አዲስ አበባ፡- በመዲናዋ ይሠሩ የነበሩ 49 ማሳጅ ቤቶች ሕገ-ወጥ ተግባር ሲፈጸምባቸው በመገኘቱ መታሸጋቸውን የአዲስ አበባ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን አስታወቀ።

ባለሥልጣኑ የማሳጅ ቤቶችን ሕጋዊነት ለማረጋገጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር ትናንት ውይይት አካሂዷል። የተቋሙ የምግብና ጤንነት ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ሚሬሳ ሚዴቅሳ እንደገለጹት፤ መሥሪያ ቤቱ ባለፉት ስድስት ወራት በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ 161 ማሳጅ ቤቶች ላይ የቁጥጥርና የክትትል ሥራ ሠርቷል።

በቁጥጥር ሥራው 125 ማሳጅ ቤቶች ከተቀመጠላቸው ስታንዳርድ ውጪ አገልግሎት ሲሰጡ መገኘታቸውን ጠቁመው፤ ከዚህ ውስጥ 76 ያህሉ ሕገወጥ አሠራራቸውን እንዲያስተካክሉ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው አመላክተዋል። 49 ያህሉ የማሳጅ ቤቶች ደግሞ ጥፋታቸው ከፍ ብሎ በመገኘቱ እንዲታሸጉ ተደርጓል ያሉት አቶ ሚሬሳ፤ ከዚህ ውስጥ የሦስቱ ማሳጅ ቤቶች ፍቃድ ሙሉ በሙሉ ተሠርዟል ብለዋል።

ቁጥጥር በተደረገባቸው ማሳጅ ቤቶች ውስጥ ሱስ አስያዥና የአደንዛዥ ዕፆች ተገኝተዋል፤ የወሲብ ንግድ ሲፈጸምባቸው የነበሩና ሺሻ ሲያስጨሱ የተገኙ ማሳጅ ቤቶች መኖራቸውንም አስታውቀዋል። የተወሰኑ ማሳጅ ቤቶች ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት እንደሚሠሩ የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ በቅጣቱ ተምረው የሚገኙ ተቋማትን ወደ አገልግሎታቸው የመመለስ ሥራ እንደሚሠራ ተናግረዋል።

አገልግሎቱን የሚሰጡ ተቋማት በቀጣይም ሕግና ሥርዓቱን ተከትለው እንዲሠሩ አቶ ሚሬሳ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። በባለሥልጣኑ የቁጥጥር ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ አሰፋ ተሬሳ በበኩላቸው፤ ማሳጅ ለጤና ጠቃሚ ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት ሕገ ወጥ ተግባራት ሲከናወንባቸው በመገኘቱ ቁጥጥሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ሕገወጥ ማሳጅ ቤቶቹ በአምራቹ ዜጋና በማኅበረሰቡ ባሕል ላይ የሚያሳድሩትን ጫና ለመቅረፍ የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት ሊሠሩ እንደሚገባ ገልጸዋል። ማሳጅ ቤቶች ከተቋቋሙበት ዓላማ ውጪ አገልግሎት መስጠታቸው አግባብ አለመሆኑን ተናግረው፤ በዘርፉ አገልግሎት ለሚሰጡ ባለሙያዎች ሥልጠና በመስጠት ማብቃት እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።

በጉዳዩ ላይ የውይይት መድረክ መዘጋጀቱ ኅብረተሰቡ ስለማሳጅ አገልግሎት ምንነት ያለውን ግንዛቤ ለማሻሻል፣ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍና ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ እንደሚረዳ አቶ አሰፋ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ የማሳጅ አገልግሎት ሰጪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ሳምሶን ሲሳይ በበኩላቸው፤ ማኅበሩ ለዘርፉ የሚመጥኑ ባለሙያዎችን እያሠለጠነ መሆኑን ገልጸው፤ በዘርፉ የተሻለ ውጤት እንዲገኝ ማኅበሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትኩረት እንደሚሠራ አመላክተዋል።

አማን ረሺድ

አዲስ ዘመን የካቲት 8 /2016

 

Recommended For You