ኢትዮጵያ ዘላቂ የምጣኔ ሀብት እንድታስመዘግብ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን መደገፍና ተወዳዳሪ ማድረግ እንደሚገባ ይታመናል። በተለይም የሥራ-አጥ ቁጥሩ እየጨመረና የዋጋ ንረቱ እያሻቀበ ባለበት በዚህ ወቅት ወደ ኢንቨስትመንት የሚመጡ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን በመደገፍ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ማበራከት ለነገ የሚተው ተግባር አይደለም። ይህን የተረዳው የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በከተማው ያለው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ትርጉም ያለው ሥራ እየሠራ ይገኛል።
በንግድ እንቅስቃሴዋ ትልቅ ዝና ያላትና የበረሃዋ ንግስት በመባል በምትታወቀው ድሬዳዋ ከተማ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ሥራዎች ተከናውነዋል። ከተማ አስተዳደሩ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት በኢንቨስትመንት ዘርፍ 250 የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለመስጠት አቅዶ 244 ፈቃድ በመስጠት የዕቅዱን 90 በመቶ ማሳካት መቻሉን ተመላክቷል። የድሬዳዋ ኢንቨስትመንት የጥናትና ፕሮሞሽን ቡድን መሪ የሆኑት አቶ አበራ መንግሥቱ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት፤ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ያለው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ አበረታች የሚባል ነው። አስተዳደሩ በዕቅድ ይዞ እየሠራቸው በሚገኙ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ሥራዎች የተሻለ አፈጻጸም አስመዝግቧል። በመሆኑም በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ውስጥ የዕቅዱን ከ90 በመቶ በላይ መፈጸም ችሏል።
በእነዚህ ወራት ካከናወናቸው ተግባራት መካከል ሰፊውን ድርሻ የሚይዘው አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃዶችን መስጠት ሲሆን አጠቃላይ በበጀት ዓመቱ 500 የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለመስጠት እንዲሁም በስድስት ወር 250 ፈቃድ ለመስጠት አቅዶ ሲሰራ ቆይቷል። በመሆኑም በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ለ244 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ በመስጠት የዕቅዱን 90 በመቶ አሳክቷል።
ቡድን መሪው እንደሚሉት፤ የተሰጡት የኢንቨስትመንት ፈቃዶች በአራት የተለያየ ዘርፎች የሚመደቡ ናቸው። እነሱም በማምረቻ ወይም በኢንዱስትሪ ዘርፍ 87፣ በአገልግሎት 140፣ በኮንስትራክሽን አራት፣ በግብርና 13 አጠቃላይ 244 የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጥቷል። ፈቃድ የወሰዱ ባለሃብቶች ያስመዘገቡት ካፒታልም 38 ቢሊዮን 873 ሚሊዮን 489 ሺ 400 ብር ነው።
ከተማ አስተዳደሩ ፈቃድ ከሰጣቸው መካከል አንዱ በውጭ አገር ለሚኖሩ የድሬዳዋ ተወላጅ ሲሆን፤ ይህም ከተማ አስተዳደሩ ትልቅ ትኩረት ከሰጣቸው ተግባራት መካከል ተጠቃሽ ነው የሚሉት አቶ አበራ፤ እነዚህ የድሬዳዋ ተወላጅ የሆኑ ዲያስፖራዎች በትውልድ ቦታቸው ኢንቨስት ማድረግ እንዲችሉና አሻራቸውን እንዲያኖሩ በርካታ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ያስታውሳሉ። የተለያዩ የማስተዋወቅ ሥራዎችም ተሰርተዋል። በመሆኑም በአሁን ወቅት ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ድሬ ናፍቆት በሚባል ፈቃድ ያገኙ ሲሆን፤ ይህም አፈጻጸሙን ከፍ ማድረግ ችሏል ይላሉ።
የኢንቨስትመንት ፈቃድ ያገኙት የአገር ውስጥ ባለሃብቶች ግንባታቸውን አጠናቅቀው ወደ ሥራ ሲገቡ በርካታ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ ያመላከቱት አቶ አበራ፤ በቋሚነት 7ሺ242 ለሚደርሱ ዜጎች እንዲሁም በጊዚያዊነት 12ሺ653 ለሚደርሱ ዜጎች በድምሩ ለ19 ሺ 901 ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ነው ያሉት። የኢንቨስትመንት ፈቃድ ካገኙ 244 የአገር ውስጥ ባለሃብቶች መካከል 184 ወንዶች፣ 31 ሴቶች እንዲሁም 29 የግል ማኅበራት ይገኙበታል።
ፈቃድ የወሰዱ እነዚህ ባለሃብቶችም በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው ሀገራዊ በሆነው የምጣኔ ሃብት ዕድገት ላይ የበኩላቸውን ድርሻ ያበረክታሉ ተብሎ ይታመናል። በተለይም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግና ተኪ ምርቶችን በማምረት ረገድ ኢንቨስትመንት ትልቅ ድርሻ አለው። በመሆኑም አሁን ላይ መሬት የተሰጣቸው ባለሃብቶች በቶሎ ወደ ሥራ የሚገቡበት መንገድ የሚመቻች መሆኑን ያስረዱት አቶ አበራ፤ ባለፈው በጀት ዓመት ስድስት የሚደርሱ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ወደ ሥራ መግባት እንደቻሉ ከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል።
ወደ ሥራ የገቡት የተለያዩ ፕሮጀክቶች ሲሆኑ፤ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩት አራት በአገልግሎት ዘርፍም እንዲሁ ሁለት በድምሩ ስድስት ባለሃብቶች መሆናቸውን ያመለክታሉ። ዘንድሮም በተመሳሳይ ፈቃድ የወሰዱ ባለሃብቶች ቶሎ ግንባታቸውን ጨርሰው ወደ ምርት መግባት እንዲችሉ ከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ ድጋፎችን ያደርጋል ይላሉ።
‹‹ከተማ አስተዳደሩ ፈቃድ ከመስጠት ባለፈ ፕሮጀክቶች በታቀደላቸው ጊዜ ወደ ምርት እንዲገቡ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል›› ያሉት አቶ አበራ፤ ማንኛውም ባለሃብት ፈቃድ ወስዶ እንዲጠፋ ሳይሆን በፍጥነት ወደ ሥራ መግባት የሚችልበትን ምቹ ሁኔታ ከተማ አስተዳደሩ የሚያመቻች መሆኑን ያስረዳሉ። ከዚህ ቀደም የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው መሬት ተሰጥቷቸው መሬቱን አጥረው የተቀመጡ 88 የሚደርሱ ባለሃብቶች እንደነበሩ ነው የጠቆሙት።
ከተማ አስዳደሩ እነዚህን ባለሃብቶች በማወያየት፤ ወደ ሥራ ለመግባት ማነቆ የሆነባቸው ችግሮች ተለይተው መፍትሔ በመስጠት በፍጥነት ወደ ሥራ መግባት አንዲችሉ ተደርጓል። የከተማ አስተዳደሩ ክትትልና ድጋፍ ተጠናክሮ የሚቀጥል በመሆኑ በቀጣዮቹ ስድስት ወራት የሚኖረው አፈጻጸም የተሻለና መቶ በመቶ መፈጸም እንደሚቻል ያመለክታሉ።
‹‹ሰላም የኢንቨስትመንት መሰረት ነው፤ በተለይም ለኢንቨስትመንት ሰላም ወሳኝ ነው። ሰላም ከሌለ ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት አይቻልም። ኢንቨስትመንት ማስፋት ካልተቻለ ደግሞ ዘላቂ የሆነ የምጣኔ ሃብት ዕድገት ማስመዝገብ አይታሰብም›› ያሉት አቶ አበራ፤ አስተዳደሩ ለኢንቨስትመንት ዘርፉ እየሰጠ ባለው ክትትልና ድጋፍ የበኩሉን ሚና እየተወጣ እንደሆነ ያነሳሉ። እንደ ሀገርም በሰላም ዙሪያ ብዙ ሥራ ሊሠራ ይገባል ሲሉ ይናገራሉ።
በዚህ ረገድም በግማሸ በጀት ዓመቱ ለተመዘገበው የኢንቨስትመንት ውጤት ከተማዋ ሰላማዊ በመሆኗ እንደሆነ ያመላከቱት አቶ አበራ፤ ከሌሎች ክልልች በተሻለ ሁኔታ ድሬዳዋ ላይ ያለው ሰላም የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴውን አፋጥኖታል ባይ ናቸው። ‹‹ትንሿ ኢትዮጵያ እንደሆነች የሚነገርላት ድሬዳዋ ሰፈር እንጂ ብሔር የላትም ይባላል። ለዚህም አንዱ ማሳያ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ከ80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች መካከል 73 ያህሉ ድሬዳዋ ውስጥ የሚኖሩ ናቸው›› ይላሉ። እነዚህ ሕዝቦችም በሰላም፣ በፍቅር፣ በመቻቻል፣ በመተሳሰብ፣ በአንድነትና በጋራ በመኖር ለሌች አብነት ሆነው መቆየታቸው ነው ያስታወሱት።
የመሰረተ ልማት ለኢንቨስትመንቱ አመቺ ሁኔታን መፍጠር ሌላው አብይ ጉዳይ መሆኑን አንስተውም፤ ‹‹መንገድ፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ውሃ፣ ቴሌኮምና ሌሎች መሰረተ ልማቶች በከተማዋ በመዘርጋት ባለሃብቶችን ለመሳብ ጥረት ተደርጓል›› ይላሉ። መሰረተ ልማቶች ማሟላት የቻለ የኢንዱስትሪ መንደር በከተማዋ መኖሩ ባለሃብቶችን የሚጋብዝ እንደሆነ ያስረዳሉ። በከተማ አስተዳደሩ ከተገነባው የኢንዱስትሪ መንደር በተጨማሪ ክላስተር ኮፕሬሽን መኖሩን ጠቅሰው፤ በእነዚህ መሰረተ ልማት በተሟላላቸው የኢንዱሰትሪ መንደሮች ውስጥ አስተዳደሩ ሼዶችን ሰርቶ ለባለሃብቱ የሚያስረክብ ሲሆን፤ ባለሃብቱም በቀላሉ ገብቶ ማምረት የሚያስችለው ይሆናል ሲሉ ያብራራሉ።
በሌላ በኩል ከተማዋ ለወደብ ቅርብ መሆኗም ትልቅ ዕድል የፈጠረላት መሆኑን ይጠቁማሉ። ‹‹የጅቡቲ ወደብ ከድሬዳዋ በ313 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። አዲስ አበባ ደግሞ በ515 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ በመሆኑ ድሬዳዋ ለጅቡቲ ቅርብ ናት። ይህም ከተማዋን ለኢንቨስትመንት ምቹ አድርጓታል›› በማለት ይናገራሉ።
እንደ ቡድን መሪው ማብራሪያ፤ ድሬዳዋ ለጅቡቲ ለወደብ ቅርብ በመሆኗ ባለሃብቶቹ ማሽኖችን ሲያስገቡ በቀላሉ ማስገባት ይችላሉ። ሌሎች ወደ ሀገር ውስጥ ለሚገቡና ለሚወጡ ምርቶችም እንዲሁ አመቺና ቀላል ነው። በተጨማሪም ድሬዳዋ በአራት ክልሎች የተከበበችና ጂኦግራፊያዊ አቀማመጧ የተመቸ ሲሆን፤ ኦሮሚያ፣ ሱማሌ፣ ሐረሪና አፋር ክልሎች ድሬዳዋን አካበው ያቀፉ ክልሎች ናቸው። እነዚህ አራት ክልሎች ደግሞ በግብርና ምርቶች ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ በመሆናቸው ለፋብሪካ አስፈላጊ የሆኑ ማንኛውንም ግብዓት ከእነዚህ አራት ክልሎች ማግኘት የሚቻል በመሆኑ ከተማዋ የኢንዱስትሪ ማዕከል አድርጓታል።
በተለይም ነጻ የንግድ ቀጣና መኖሩ በራሱ ኢንቨስትመንቱን ለማበረታታትና ለመሳብ ትልቅ አቅም እንደሆነ ያስረዳሉ። ነጻ የንግድ ቀጣናው ድሬዳዋ ላይ በመሆኑ ወደፊት ባለሃብቱ ያለማንም ቀስቃሽ ወደ ድሬዳዋ በመምጣት ማልማት የሚችልበት ዕድል እንደሚኖረው፤ ይህም ነጻ የንግድ ቀጣናው የውጭ ባለሃብቶችን በመሳብ ለውጭ ኢንቨስትመንት ትልቅ አቅም እንደሚሆን ነው ያመለከቱት።
‹‹ነጻ የንግድ ቀጣናው ምንም እንኳን በፌዴራል መንግሥት የሚተዳደር ቢሆንም ለከተማ ዕድገት ትልቅ ድርሻ አለው ያሉት›› አቶ አበራ፤ ነጻ የንግድ ቀጠናን ጨምሮ ከተማ አስተዳደሩ የሚሰጠው የኢንቨስትመንት ፈቃድ በከተማ አስተዳደሩ በሚያስተዳድረው የኢንዱስትሪ መንደር ውስጥ ለሚሰማሩ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ሲሆን፤ ለውጭ ባለሃብቶች ፈቃድ የሚሰጠው የፌዴራል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መሆኑን ያስረዳሉ።
እንደእሳቸው ማብራሪያ፤ ድሬዳዋ ከተማ ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆነች ከተማ በመሆኗ በከተማዋ በርካታ ፋብሪካዎች ተከፍተው አገልግሎት እየሰጡ ነው። ሶስት ሲሚንቶ ፋብሪካዎችን ጨምሮ የውሃ ፋብሪካ፣ ዘይት ፋብሪካ፣ ፓስታ፣ ማካሮኒ፣ ሳሙናና ሌሎች ፋብሪካዎች በሥራ ላይ ናቸው። እነዚህ ፋብሪካዎችም ምንም አይነት የገበያ ችግር የሌለባቸው ሲሆኑ ይህም ማለት የድሬዳዋ ሕዝብ ቀደም ሲል ጀምሮ የኢንዱስትሪ ምርቶችን መጠቀም የጀመረ በመሆኑና አሁንም ድረስ በስፋት እየተጠቀመ በመሆኑ በከተማዋ በርካታ ፋብሪካዎች ይገኛሉ።
በቅርቡም ድሬዳዋ ከተማ ካሏት የኢንቨስትመንት አማራጮች መካከል አንዱና ትልቁ በሆነው የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ማምረቻ ተመርቆ ወደ ሥራ ገብቷል። ማምረቻው በሰዓት ከ220 ቶን በላይ የኮንስትራክሽን ግብቶችን የማምረት አቅም ያለው ነው። ፋብሪካው በአካባቢው ለሚኖሩ ወጣቶች የሥራ እድል በመፍጠር ትልቅ ድርሻ ያለው ይኖረዋል። በተጨማሪም የአካባቢውን ማኅበረሰብ የኤሌክትሪክ ኃይልና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ተጠቃሚ ማድረግ ያስችላል። ይህም ከተማ አስተዳደሩ ለባለሃብቶች አስፈላጊውንና የተቀላጠፈ ምላሽ መስጠት በመቻሉ የተመዘገበ ውጤት እንደሆነ ነው አቶ አበራ ያመላከቱት።
እንደቡድን መሪው ማብራሪያ፤ ፋብሪካው በመጀመሪያው ምዕራፍ የምርት ሒደት 50 ለሚደርሱ ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል መፍጠር ችሏል። በቀጣይም ፋብሪካው በሙሉ አቅም ወደ ምርት ሲሸጋገር ለተጨማሪ ዜጎች የሥራ እድል የሚፈጥር ይሆናል። ፋብሪካው የማምረት አቅሙ ከፍተኛ የሆነ ዘመናዊ ማሽኖችን የሚጠቀምና በርካታ የግብአት አማራጮችን ከጥራት ጋር የሚያቀርብ ድርጅት በመሆኑ ከድሬዳዋ አልፎ የአጎራባች ከተሞችና ክልሎችን የምርት ፍላጎት ጭምር ማሟላት የሚያስችል ነው።
‹‹የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ለኢንቨስትመንት ዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ በመሆኑ በዘርፉ የጎላ ችግር አላጋጠመም›› የሚሉት አቶ አበራ፤ በቅርቡም የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን ማምረት የሚችል ፋብሪካ ተመርቆ ወደ ሥራ መግባቱን ይገልፃሉ። አክለውም ‹‹ማንኛውም ሰው ድሬዳዋ ከተማን ቢጎበኛት ያተርፋል እንጂ አይከስርም። በተለይም የአገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች ወደ በረሃዋ ንግስት ድሬዳዋ ከተማ ቢመጡና መዋለንዋያቸውን ቢያፈሱባት በብዙ ያተርፋሉ›› በማለት ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን የካቲት 7/2016