የፓን አፍሪካኒዝም ጥንስስ እና የኅብረቱ ግብ፤

እንደ አውሮፓውያኑ የጊዜ ቀመር በ1812 በምዕራብ ቨርጂኒያ ግዛት ቻርለስ እንደተወለደ ታሪክ የሚያወሳን ማርቲን ሮቢን ሰን ዴላኒ፤ አባቱ በቅኝ አገዛዝ ዘመን ከአፍሪካ አኅጉር በባርነት የተወሰደ ነው፤ የግለሰቡ ልዩ መታወሻው ጥቁር አሜሪካዊያን ወደ አኅጉራቸው አፍሪካ እንዲመለሱ የሚያበረታታ ንቅናቄን ማስጀመሩ ነው፤ በአሜሪካን ወታደራዊ ተቋም ውስጥ የመጀመሪያው ጥቁር አፍሪካ አሜሪካዊ ሹም የነበረው ዴላኒ፤ በዘመኑ የነበረው የባርነት ቀንበር እና የጥቁር የበታችነት አሳሳቢ እና ተሰፋ የሚያስቆርጥ ስለመሆኑ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ደጋግሞ ያነሳም ነበር። አቋሙ ይህን ያህል ተጽዕኖ ፈጣሪ እንዲሆን ያስቻለው ቤተሰቦቹ ለልጃቸው ከቆዳ ቀለም ማንነታቸው ያለፈ ሐሳብ እና ማንነት እንዲይዝ አድርገው ማሳደጋቸው ነው።

ከ200 ዓመታት በፊት ወደዚህች ምድር የመጣው ማርቲን ዴላኒ የባሪያ ንግድን የሚቃወም፣ የሰብኣዊ መብት ተሟጋች፣ የሕክምና ባለሙያ፣ ወታደር፣ ጋዜጠኛ እና የጥቁር ነፃነት አቀንቃኝ ነበረ ይለናል ከማኅበራዊ ድረ ገጽ ያገኘሁት መረጃ። ማርቲን በበርካታ የጥቁር ነፃነት ንቅናቄዎች ላይ ተሳታፊ፤ በአሜሪካ ውስጥ በየሳምንቱ ይታተም በነበረው ዘ ሚኒስትሪ ጋዜጣ ላይ ያለ ማቋረጥ የጻፈ፤ ከኒውዮርኩ የጥቁር መብት ተሟጋች ፍሬድሪክ ዳግላስ ጋር ዘ ኖርዝ ስታር በሚል በበርካቶች ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፈ ስለ ጥቁሮች ነጻነት እና እኩልነት የሚሞግት ጋዜጣ በማሳተም ፋና ወጊ የነበረ፤ ጥረታቸው ቀጥሎ ከ1865 እስከ 1872 የጥቁር አፍሪካ አሜሪካውያን የነፃነት ቢሮ Freedmen’s Bureau በመምራት ከ4 ሚሊዮን የሚበልጡ ጥቁር አሜሪካውያን ከባርነት ነፃ እንዲወጡ አድርገዋል።

ልክ እንደ ማርቲን ሁሉ ዛሬ ለበርካታ አፍሪካውያን ቀና ብሎ መራመድና ለጥቁሮች እኩልነት በታገለ የፓን አፍሪካኒዝም ፅንሰ ሐሳብ አራማጅ በመሆን የአሌክሳንደር ኩርሜል ስም ይነሳል። በ1819 በኒውዮርክ የተወለደው አሌክሳንደር ኩርሜል በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ትምህርቱን ያጠናቀቀ ሲሆን፤ በ1853 ወደ ሊቢያ በመሄድ የሰው ልጅን እኩልነት እና የጥቁሮችን ነፃነት የሰበከ የፓን አፍሪካ ንቅናቄ መስራች እና አራማጅ ነበር። ለ20 ዓመታት በሊቢያ በቆየበት ወቅት አሌክሳንደር አፍሪካውያን አንድ ሐሳብን በማንገብ ለነፃነታቸው እንዲቆሙ ሰርቷል። አፍሪካውያን ለአፍሪካ የሚል ፅንሰ ሐሳብ በማራመድም እሱን ተክተው ለንቅናቄው ፈርጥ ለሆኑት እነ ማርከስ ጋርቬይ፤ ፓወል ላውረንስ ዱንባል እና ዱ ቦንሲ መንገድ ከፍቷል።

እንዲህ እያለ የተቀጣጠለው የጥቁሮች የነፃነት ማዕበል እየላቀ ሄዶ በ1980 የጥቁሮች ትግል የብሔርተኝነት (ናሽናሊዝምን) አስተሳሰብ እና መርህ ይዞ ንቅናቄው ዓለም አቀፋዊ እንዲሆን ተደረገ። አዲሱ የብሔርተኝነት አስተሳሰብ በ20ኛው ክፍለ ዘመን የአውሮፓ ኅብረት እንዲሁም ራሱን ከአውሮፓ ኅብረት ያገለለው የአውሮፓ ፖለቲካል ዶክትሪን እንዲመሰረት ምክንያት ሆኗል። የኋላ ኋላም በ1920 በዓለም ላይ ሰላምን ለማስፈን እና አገራት የእርስ በእርስ ጦርነትን ለማራቅ በፓሪስ ሊግ ኦፍ ኔሽንስ መቋቋም ምክንያት ሆኗል።

አፍሪካውያን ለነፃነታቸው በታገሉባቸው ዓመታት ውስጥ አንድነታቸውን ለማጠናከር ፓን አፍሪካኒዝም የላቀ አስተዋፅኦ እንደነበረው፤ ንቅናቄውን የጀመሩት የመጀመሪያዎቹም ቢሆኑ አፍሪካ አንድ ሆና ማየትን ከመሻት በመነጨው ሕልማቸው ውስጥ ከባርነት እና ቀኝ ግዛት ነፃ ከመውጣት ባሻገር ተያይዞ ማደግን እና ከድህነት አዘቅት ውስጥ መውጣትን አልመው ታግለዋል። ፓን አፍሪካኒዝም አፍሪካውያን እንዲሁም ከአፍሪካ የተሰደዱ ሁሉ ተመሳሳይ ፍላጎት አላቸውና አንድ ሊሆኑ ይገባል የሚልን ሐሳብ ያራምዳል።

ፓን አፍሪካኒዝም ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴን፣ ዩዌሪ ሞሶቬኒ፣ ኩዋሜ ንክሩማህን፣ ሞአመር ጋዳፊን ብሎም ቶማስ ሳንካራን እና ሌሎች ለአፍሪካ አንድነት የቆሙ አፍሪካውያንን አፍርቷል። እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር ሐምሌ 9/2002 በደርባን ደቡብ አፍሪካ የአፍሪካ ኅብረት ሲመሰረት ይህንን የአንድነት ስሜት አንግቦ ነው። አፍሪካ ለአፍሪካውያን ትሆን ዘንድ አፍሪካውያን ደግሞ ባላቸው እና በሚኖራቸወ ሁሉ ለአፍሪካ እንዲቆሙ በመጠየቅ የፓን አፍሪካኒዝም ፅንሰ ሐሳብ ዛሬም እንዲዳብር ሆኗል። በአፍሪካ ኅብረት በርካታ ሐሳቦች ይስተናገዳሉ።

ለአፍሪካ እና አፍሪካውያን የሚበጁ ቴክኖሎጂ፣ የባሕል እና የሳይንስ የልህቀት ትስስሮች ይመሰረታሉ። በ2024 ከጦርነት እና ሰላም እጦት ነፃ ለመሆን፣ ከርሃብ እና ኋላ ቀርነት ለመላቀቅ እምርታዊ ለውጥ የምታስመዘግብ፤ በአዲስ አስተሳሰብ አዳዲስ ግቦችን የተለመች አፍሪካን ለመገንባት መሪዎቿ በኅብረቱ መዲና አዲስ አበባ ጉባኤያቸውን ያደርጋሉ። በዚህ ስብሰባቸው አለፍ ሲልም በአጀንዳ 2063 የተያዙ ግቦችን ገቢራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ፍኖተ ካርታዎች ገቢራዊነታቸው እንዴት እየሄደ ነው የሚለው እየተመዘነ አቅጣጫዎች ይቀመጣሉ።

ጋዜጠኛ ኤልያስ መሠረት በበኩሉ፤ ትውልደ- አፍሪካውያን የጋራ ጥቅም፣ እጣ ፈንታ እና ታሪክ ባለቤት መሆንን የሚገልፅ ሲሆን ለዚህም ትብብርን እና በጋራ መስራትን ያበረታታል። ታዲያ በዚህ ሀሳብ ዙርያ በቀደመው ግዜ ታላላቅ ገድሎች የተፈፀሙ ቢሆንም አሁን፣ አሁን ግን ስም ብቻ እየሆነ እንደመጣ በርካታ የአፍሪካ ፀሀፊያን ያነሳሉ። እነ ስቲቭ ቢኮ፣ ጁሊየስ ኔሬሬ እና ማርከስ ጋርቬይ ያነገቡት እና ብዙ መስዋዕት የከፈሉለት መርህ የት ደረሰ ብለው የሚጠይቁ በርካቶች ናቸው። ከቅርብ ግዜያት ወዲህ ግን አፍሪካውያን ከውጭ ሀገራት ይደርስብናል ያሉትን ጫና እና ጣልቃ ገብነት ለመከላከል የፓን አፍሪካኒዝም መርህን ደጋግመው ሲያነሱ ተስተውሏል፣ የአፍሪካ ሀገራትም በመርሁ ዙሪያ ሲተባበሩ ተስተውሏል። እርግጥ ነው አንዳንድ ታዛቢዎች ይህ “የመንግስታት መደጋገፍ ብቻ” እንደሆነ ጠቅሰው “ነግ በኔ” በሚል እሳቤ እንደሚመራ ለማስረዳት ይሞክራሉ።

ኢትዮጵያ በቀደሙት ዓመታት ፓን አፍሪካኒዝምን ካራመዱ እና ከፍ ካደረጉ ሀገራት መሀል አንዷ ነበረች፣ ለዚህም ቀዳማዊ ኃይለስላሴ የነበራቸው ድርሻ እጅግ የጎላ ነበር። በቅርብ ዓመታት ግን ይህ መርህ በአብዛኛው ተረስቶ ነበር፣ ለዛም ይመስላል ብዙ ትኩረት ተሰጥቶት የማያውቀው። ሌላው ቀርቶ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት እንደሚደረገው ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት ባንዲራን በየኤምባሲያቸው እና የመንግስት ቢሮዎቿ ከፍ አድርገው ከሚያውለበልቡ ቀደምት ሀገራት መሀል ተጠቃሽ አይደለችም (ከጥቂት ኤምባሲዎቻችን ውጪ ማለት ነው)።ታዲያ አሁን የመጣው የመተባበር መንፈስን ይበልጥ አጠናክሮ ለመቀጠል ትልቅ እድል የመጣ ይመስላል። ፓን አፍሪካኒዝም ለችግር ግዜ ብቻ ሳይሆን ሁልግዜ በአፍሪካውያን ሊነሳ እና ሊተገበር የሚገባው መርህ ይመስለኛል። ኢትዮጵያውያን ስለ መርሁ በደንብ ተረድተው ብዙ ሊሰሩ የሚችሉበት መድረክ ነው ሲል ጋዜጠኛ ኤልያስ ያሳስባል።

ቅኝ ገዢዎችና ተስፋፊዎች ጥቁሮች የራሴ መብት፣ የግሌ ሀብት፣ የእኔ ሀሳብ የሚሉት ነገር እንዲኖራቸው አይፈልጉም።እኔ ካልኩት ውጭ በሚል የበታች አድርገው ረግጦ መግዛትን ፖሊሲያቸው አድርገው ኖረዋል። ይህ አብዝቶ ያስጨነቃቸው ጥቁሮች በሀገረ አሜሪካ የነፃነት ጩኸት ማሰማት ጀመሩ፤ የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ። ንቅናቄው በዋናነት የቅኝ ግዛት መስፋፋትን ወይም የነጮች የበላይነትን በመዋጋት የአፍሪካን አንድነት ለማጠናከር የታሰበ ነው። ፓን አፍሪካኒዝም በአሜሪካ ምድር ይጠንሰስ እንጂ፤ የንቅናቄው መንፈስና ብርታት ኢትዮጵያ እንደነበረች ታሪክ ያወሳል።

ለዚህም ነው ኢትዮጵያ የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ኩራት የጀግንነት ተምሳሌት ተደርጋ የምትገለጸው። የፓን አፍሪካኒዝም ግቡ ጠንካራ አፍሪካዊት ሀገር መመስረት ነበርና ለነጮች ያልተንበረከከችና ቅኝ ያልተገዛች ብቸኛ ነፃነቷን ጠብቃ ያለች ሀገር ኢትዮጵያ መሆኗን አምነው ተንቀሳቅሰዋል። የአፍሪካ ሀገሮች የማዕዘን ድንጋይ ሆና መታየቷ ከጎኗ እንዲቆሙ አድርጓቸዋል። በዚህም የኢትዮጵያ ነፃነት የአፍሪካ ብሎም የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ተደርጎ ይወሰዳል። በተመሳሳይ ጉዳቷን ጥቃቷም የእነርሱ ሕመም ነው። አሁን ያለው ኢትዮጵያን ደካማና የተበተነች ሀገር በማድረግ የአፍሪካን ነፃነት ለመንጠቅ እየተደረገ ያለውን የእጅ አዙር ጦርነት በፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ መዋጋት እንደሚያስፈልግ ምሁራን ለኢዜአ ይናገራሉ።

በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር ዓለማየሁ አብርሃም እንደሚሉት ኢትዮጵያ ጥቁር ሆና በታሪክ ነጮችን በማሸነፍ የጥቁሮችን ነፃነትና የእችላለሁ መንፈስ በደማቅ ቀለም ጽፋለች። ይህ ደማቅ ታሪኳ ለመላው ጥቁሮች የአንድነት እንቅስቃሴ (ፓን አፍሪካኒዝም) ስንቅ ነው ይላሉ። ኢትዮጵያ ያላት ጀግንነት በታሪክ የሚቀር በትውልድ የሚቋረጥ አይደለም ያሉት መምህር አለማየሁ፣ በአድዋ ጦር ግንባር ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዙፋናቸውን ትተው በመዝመት ተዋግተው ጣሊያንን አሳፍረዋል።

ምዕራባውያን እነርሱ እንደፈለጉ የሚያዙትና የሚጋልቡት መንግሥት በአፍሪካ እንዲፈጠር ይፈልጋሉ፤ ኢትዮጵያ ደግሞ አይሆንም የእኛ ጉዳይ እኛ እናውቃለን በማለት ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትን መወከሏ ምቾት አልሰጣቸውም ይላሉ ምሁሩ። ቀድሞ ኢትዮጵያን በመበተን አፍሪካን እንደፈለጉ የማድረግ ዓላማ ይዘዋል። የፓን አፍሪካኒዝም አስተሳሰብ ማራመድ ያስፈልጋል ይላሉ መምህር ዓለማየሁ። በሌላ በኩል በዩኒቨርሲቲው የሥነ ዜጋ ትምህርት ክፍል መምህር ሙሉቀን አየለ እንደሚሉት፤ ሌሎችን ለነፃነት የምታስተባብር አፍሪካዊት ሀገር በክብር እንድትኖር በነጮች አይፈለግም። በመሆኑም ፓን አፍሪካኒዝም በተጠናከረ እንቅስቃሴ መጀመር አለበት። እንደ ግለሰብ ሳይሆን እንደ ሀገር አፍሪካን እየተከፋፈሉ ግዛታቸውን ሲያስፋፉ አፍ እያላቸው የማይናገሩ፣ አቅም እያላቸው ምንም የማይቻሉ አድርገው ይገዙ ነበር።

ዛሬ ደግሞ በቀጥታ መግዛትና መዝረፍ አልቻሉም። ያመረቱትን ሸቀጥና የፖለቲካ ፍልስፍናና እሳቤዎቻቸውን ሊያራግፉብን ይሻሉ። እኛ እናውቅላችኋለን፤ የሚበጃችሁ የእኛን ሀሳብ መቀበል ለእኛ ታዛዥ መሆን ነው ሊሉን ይዳዳሉ። ግን ይሄ ዘመን ያለፈበት ጉዳይ መሆኑን ሊረዱት አልቻሉም ወይም አልፈለጉም። የኢትዮጵያ ሕዝብ አድዋን በአጎዋ አይለውጥም። ማንነቱንም አሳልፎ አይሰጥም። ምክንያቱም ኢትዮጵያዊ ነውና! አዎ ጮኽ ብለን እንናገራለን አፍሪካ በእጅ አዙር ቅኝ አስተዳደር አትገዛም። የራሷ ፍልስፍና፣ የራሷ ማንነት ያላት አህጉር ናትና! ለዚህ ደግሞ በቀደምት አፍሪካውያን የተጠነሰሰው ፓን አፍሪካኒዝም ማሳያ ነው። ጊዜው የአፍሪካ ትንሳኤ የሚታወጅበት ነው። ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ ዋጋ በመክፈል ላይ ናት ይላሉ አስተያየት ሰጪው።

ወቅታዊ የአፍሪካ ችግሮችን ለመፍታት በፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ መሰባሰብና ለጋራ ጉዳዮች በጋራ መሥራት ያስፈልጋል። ዲፕሎማቶቹ ፓና አፍሪካኒዝም፤ መላው አፍሪካዊ አንዱ ለሌላው የቆመና ተቀራራቢ ታሪክ፣ ባሕልና ተመሳሳይ ችግሮች ያሉበት ሕዝብ መሆኑን አመላካች አስተሳሰብ ነው። በዚህ አስተሳሰብ በመቃኘትም አህጉሪቱ ከጸጥታ መደፍረስ ጀምሮ የሚፈትኗትን የተለያዩ ችግሮች ለመፍታት የጋራ ርብርብ እንደሚያስፈልግ ኢዜአ ያነጋገራቸው ዲፕሎማቶች ይገልጻሉ።

የዛምቢያው ዲፕሎማት ዶክተር አንድሪው ሲሉሜሲ፤ ፓን አፍሪካኒዝም አፍሪካውያኖች አንድ መገኛ ያላቸው መሆኑንና እጣፈንታቸውን በጋራ ሊወሰን የሚችል መሆኑን፤ በተጨማሪ አፍሪካውያን በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ያላቸውን ሥፍራ የሚያመላክትና በጋራ በመሥራት የምንፈልጋትን አፍሪካ እውን ለማድረግ የሚያነሳሳ፤ አፍሪካ የሚያጋጥማትን ችግሮች ለመፍታት በፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ የተቃኘ አጋርነትና አንድነት በመፍጠር ለጋራ ዓላማ መረባረብ እንደሚገባ፤ የምንፈልጋትን አፍሪካ እውን ለማድረግ በተናጠል ሳይሆን በጋራ ጉዳዮች ላይ ተቀራርበን መስራት እንደሚጠበቅበን ሊሰመርበት ይገባዋል። ከዚህ አኳያ የአፍሪካ ኅብረት አህጉሪቱን ሊጠቅማትና ትልሟን ሊያሳካላት የሚችሉ ስትራቴጂዎችን በመንደፍ መንቀሳቀስ እንዳለበት ጠቁመዋል።

ደቡብ ሱዳናዊው ዲፕሎማት ጆን ዮሄንስ በበኩሉ ፓን አፍሪካኒዝም የአፍሪካ ሕዝቦች በተለያዩ አኅጉራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ እንዲቆሙና ትብብራቸውን እንዲያጠናክሩ የሚያደርግ እሳቤ መሆኑን፤ ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት አህጉሪቱን በተለያየ መልኩ እየፈተኑ ያሉትን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍትሄ ለማበጀት በጋራ መረባረብ እንደሚገባም፤ ወጣቶችን ተሳታፊ የሚያደርግ የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ለትውልድ እንዲተላለፍ ማድረግ፤ ይህን ማድረግ ከተቻለ አኅጉሪቱ ላይ በርካታ ለውጦች ማምጣት እንደሚቻል፤ በተለይም የአፍሪካ ኅብረት እንዲህ ያሉ አኅጉራዊ አጀንዳዎች ላይ ከዚህ ቀደም የነበረውን ሚና ይበልጥ በማጠናከር ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ሲል አሳስቧል።

ሻሎም ! አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን የካቲት 7/2016

 

 

Recommended For You