ለአፍሪካውያን ብሩህ ነገዎች ከመሪዎቿ ብዙ ይጠበቃል

በሀገራችን በ1955 ዓ.ም አንድ ኩነት ሆነ። ይህ ኩነት ማንም ይሆናል ብሎ ያላሰበው ከመሆኑም በላይ አስደናቂም አስደማሚም ነበር። ወቅቱ አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት በቅኝ ግዛት እሳት ውስጥ የነበሩበት፤ አፍሪካዊ እንደ ሙሉ ሰው ተቆጥሮ ሃሳቡ ተደምጦ ጥያቄውና ፍላጎቱ ታይቶ ይሁንለት፤ ይደረግለት የሚባልለት ወቅት አልነበረም።

ከዛ ይልቅ አፍሪካውያን ተፈጥሮ ያደለቻቸውን የተፈጥሮ ሀብት ቦጥቡጦ ለመበልጸግ፤ ዜጎችንም ባሪያ አድርጎ መግዛት የብዙዎቹ ምዕራባውያን ሃሳብና ዓላማ ብሎም ተግባር ነበር። በዚህ መካከል ግን ትልቅ ሀሳብን ያነገበችው ኢትዮጵያ የቅኝ ግዛት ቀንበርን አልሸከምም እኔ ከማንም አላንስም በሀብትና በንብረቴ የማዘው ራሴ ነኝ ዜጎቼም በባርነት የሚማቅቁበት አንዳችም ምክንያት የለም ስትል በዓለም አደባባይ ላይ ወጣች። ይህ ለብዙዎች ትንግርት ቢመስልም ሆኖና ተችሎ የተመለከቱት ሐቅ ሆነባቸው።

ይህች ተምሳሌት የሆነች ሀገር በጠንካራ መሪዋ አማካኝነት በዓለም አደባባይ ስሟን የሚያስጠራ ቀና የሚያደርጋት መሰሎቿንም ቀና የሚያደርግና ካሉባቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮች መንጥቆ የሚያወጣ ሃሳብ ይዛ ብቅ አለች። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምሥረታን። የዛሬ 61 ዓመት እነ ኬንያታ፣ ኃይለሥላሴ፣ ንክሩማ፣ ኔሬሬ እና ገማል አብዱል ናስር የተባበረችዋን አፍሪካ ለመመሥረት የመሠረት ድንጋይ አኖሩ! የተባበረች አፍሪካ፣ ከቅኝ ግዛት ነፃ የወጣች አፍሪካ ፣ የበለፀገች አፍሪካ አልመው ፣ ይኸው ስድስት አስርተ ዓመታትን አስቆጠሩ።

በእርግጥ አንድነቱ ወደ ኅብረት ይደግ እንጂ ዛሬም ድረስ የተመሠረተበትን ዓላማ ከግብ አድርሷል ለማለት የማያስደፍሩ ብዙ ምክንያቶች አሉ። አፍሪካ ኅብረት ሲመሠረት የቆመለት የነፃነት የሉዓላዊነት ከድህነትና የመውጣት ሕልም ብዙም እልፍ ሲል አልታየም። አፍሪካና አፍሪካውያን ዛሬም የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ናቸው። አፍሪካውያን ዛሬም ከእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ተላቀዋል ብሎ አፍን ሞልቶ ለመናገር የሚያበቃ ሁኔታ አይታይም።

አፍሪካውያን ዛሬም ከስደትና የነጮቹን ደጃፍ ከመርገጥ አልወጡም። ለምን ቢባል እንደ ስሙ ኅብረት በማጣታችን ነው። ሲቋቋም እንደነበረው አፍሪካውያን ተረዳድተንና ተፋቅረን እንደ አንድ ሆነን መቆም ስላቃቸው ነው። በእኔ አረዳድ እነ አፄ ኃይለሥላሴና ሌሎቹም ጠንካራ አፍሪካውያን መሪዎች ያቆዩትን የትብብርና የአንድነት ስሜት ይዘን ቀጥለናል ለማለት አልደፍርም። እንደ ቀደሙት አባቶቻችን ሀሞተ ኮስታራ ሆነን ለነጮች የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት እምቢ አልገዛም ማለት ተስኖናል ።

ዛሬም ግን አፍሪካን የአፍሪካውያን የማድረጉ እድል ሙሉ በሙሉ ከእጃቸን ወጥቷል ለማለት አይቻልም። ዛሬም ቢሆን ሀብታችንን በሚገባ አልምተን፣ ከእርስ በእርስ ፍጅት “ከመፈንቀለ መንግሥት፣ ከመፈናቀልና ከማፈናቀል፣ ከጎታች አስተሳሰብ ወጥተን ችግሮቻችንን ልዩነቶቻችንን በጠረጴዛ ዙሪያ የምንፈታ ስልጡን ሕዝቦች መሆን ከቻልን ጊዜው አለን። ለዚህ እነሱ (ምዕራባውያኑ) እንደሚሉን ችግረኛ ደሃ ሳንሆን ተፈጥሮ ለእነሱ ያላደለቻቸውን በረከቶች ሁሉ የተሰጠችን የተመረጥን ድንቅ ሕዝቦች መሆናችንን መጀመሪያ ማመን ይገባናል፤ ከዛም ሀብታችንን እንዴት ነው መጠቀም ያለብን የሚለውን ደግሞ ሰከን ብሎ ማሰብ ይጠይቃል ።

ከሁሉ በላይ አስቸጋሪው ሀብት ሳይሆን የሀብት ፍትሐዊ ክፍፍል ነውና፤ እንዴት ነው በፍትሐዊነት ለሁሉም የሚዳረሰው፤ በምን መልኩ ነው የሥራ እድል የሚፈጠረው፤ እንዴት ባለው መንገድ ነው የዘመኑ ቴክኖሎጂዎችን አፍልቀን ኑሯችንን ፤ ሕይወታችንን የምናቀለው፤ በምን መልኩ ነው በየጊዜው ፈልገንም ሳንፈልግም ከሚመጣብን ጦርነትን ከምናባክነው ሀብት የምንድነው? በቀናነት መጠየቅ፤ ለተግባራዊነቱም መጣር ይገባናል።

የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ በየዓመቱ ይደረጋል ይህ ምንልባትም ለእኛ ለኅብረቱ መሥራቾች በጣም ትልቅ ነገር ነው፤ ምክንያቱ ደግሞ የኅብረቱ መቀመጫ አዲስ አበባ መሆኑ የሚያማቸው ብዙ ጠላቶች ስላሉን። ግን ደግሞ እነዚህ መሪዎች በዓመት ለአንድ ጊዜ ተገናኝተው ምን አድርገው ነው ወደመጡበት መመለስ ያለባቸው? የሚለው እንደ አፍሪካዊ ሊያሳስበን ይገባል።

በተለይም አሁን በደረሰንበት ጊዜ እነዚህ መሪዎች በአንድ ላይ ቁጭ ብለው ሊወያዩባቸው፤ ሊፈቷቸው አቅጣጫ ሊያስቀምጡባቸው የሚገቡ በርካታ የቤት ሥራዎች ያሉበት ጊዜ ነው። አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት በእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ናቸው፤ ሕዝቡም ስደትን እንደ አማራጭ አይቶ በዓለም ላይ እየተሰደደ ግማሹም ባሕር ለማቋረጥ በሚያደርገው ጥረት እዛው እየሰመጠ የአውሬ እራት እየሆነ ነው። በዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ ራሳቸውን አግዝፈው ከሚባለው በላይ ሀብት ሰብስበው ጆሯቸውንም አይናቸውንም ደፍነው የታዩ አፍሪካውያን መሪዎች አሉ።

የዘንድሮው የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ የእርስ በእርስ እልቂት እና ፍጅት የሚያበቃበትን፤ አህጉራችን ለዜጎቿ የመከራ ዋሻ ከመሆን ወጥታ ያላትን ሀብት ተጠቅማ ካለችበት ድህነትና ኋላቀርነት የምትወጣበት፤ ከተናጠል የልማት ጉዞ ወጥታ የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ባደረገ መንገድ መጓዝ የምትችልበትም መልካም አጋጣሚ መፍጠር የሚችል ቢሆን እመኛለሁ ።

አበው ሲተርቱ “ሸክላ ሰሪ በገል ትበላለች” ይላሉ ይህ አባባል ትልቅ ነው በተለይም ለእኛ አፍሪካውያን፤ ምክንያቱ ደግሞ ሁሉ በእጃችን ሁሉ በደጃችን ሆኖ ተስማምተን ተደማምጠን ተፋቅረን መጠቀም ስላቃተን ብቻ ሌሎች በሀብታችን እየበለጸጉ እኛ ሁሌም “በገል” መብላታችንን ያሳያል። ይህ ሁኔታ ሊቀየር፤ ሊቀየርም ብቻ ሳይሆን እንደ አፍሪካ አንድ ሆነን በኅብረት ቆመን ተባብረንና በልጽገን የምንታይበት ጊዜ ሊቃረብ ይገባል።

አፍሪካውያን “እንኳን ደህና መጣችሁ”! መምጣ ታችሁ አስደሳች ነው። ነገር ግን መምጣታችሁን መሰብሰባችሁን በፍሬያማ ንግግሮች ውሳኔዎች በጠንካራ አቋሞች አስደግፋችሁ እንደ እነ ቀደሙት የኅብረቱ መሥራቾች በአንድነት የሚዘከር፣ የሚነገርና የሚወደስ ለትውልድ የሚቆይ ታሪክ ጸሐፊ ያድርጋችሁ። አበቃሁ!

እፀገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን የካቲት 7/2016

 

 

Recommended For You