የዓድዋ ፊት-አውራሪ ጀግኖች

የየካቲት ወር በአትዮጵያ ታሪክ ጉልህ ሥፍራ አለው። የኢትዮጵያውን የነፃነት ተጋድሎ ታሪክ በደምና አጥንት የተፃፈበት ወር ነው፤ ከእነዚህ አበይት የታሪክ ክስተቶች አንዱ የዓድዋ ድል ነው፡፡ የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ክብር ማኅተም፤ የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ቀንዲል ነው፡፡ የመላው ዓለም ተፈጥሯዊ ግብር እና ሰብአዊ ክብር የታደሰው፤ በእውነት በፍትህ እና በህልውና ላይ የተቃጣው ጥቃት ድባቅ የተመታው በዓድዋ የጥቁር ህዝቦች ታላቅ ድል ነው፡፡

የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም በግሩም ሥነሥርዓት የተደራጀ ግዙፍ የኢትዮጵያ ሠራዊት የማይታሰበውን ፈጽሟል። ወራሪው የጣሊያን ኃይል ላይ ድባቅ በመምታት ድልን ተቀዳጅቷል። ስግብግብነት በተጠናወተው የአውሮፓውያን መስፋፋት፤ ኢትዮጵያ ነጻነቷን በተሳካ መልኩ አስጠብቃለች ሲሉ ያነሳሉ፤ ዝነኛው የታሪክ ፕሮፌሰር ራይሞንድ ዮናስ፦ «የዓድዋ ጦርነት፤ በዘመነ ቅርምት የአፍሪቃ ድል» በተሰኘው መጽሐፋቸው። ሃያ ዘጠኝ ሺህ ፈረሰኞችን ጨምሮ ከመቶ ሺህ እስከ መቶ ሃያ ሺህ የሚገመት አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር በባዶ እግሩ የተጓዘ የኢትዮጵያ የገበሬ ሠራዊት፤ በወታደራዊ አካዳሚ የሠለጠነውን የአውሮፓ ወራሪ ጦር የካቲት 23 ማለዳ አሥራ አንድ ሰዓት ግድም ገጥሞ ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ ማሸነፉን አረጋግጧል ይለናል የታሪክ ተመራማሪው ጆርጅ በርክሌይ፡፡

የዓድዋ ጦርነትና ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በተሰኘና ዳኘው ኃይለሥላሴ ወደ አማርኛ በተረጐሙት መጽሐፍ ላይ፤ የኢትዮጵያ ገበሬ ሠራዊት ፈረሱ ላይ ሆኖ የጋሻውን እምብርት መሬት ላይ እያጠቀሰ ጐራዴውን አየር ውስጥ እየቀዘፈ በተቆጣና በቆረጠ መንፈስ በጀግንነት ተዋግቷል። ጦርነቱ በተጀመረ ከአምስት ሰዓት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ሃምሳ ስድስቱም የኢጣሊያ መድፎች ሙሉ ለሙሉ ተማርከዋል፡፡ የቅኝ ገዢውን ወራሪ ሠራዊት ከመሩት ጀኔራሎች ጄኔራል አልቤርቶኒ ሲማረክ የሠራዊቱ ዋና አዛዥ ጄኔራል ባራቴሪ ከጥቂት አጃቢዎቹና በሽንፈት ከተበታተኑ የጣሊያን ወታደሮች ጋር ሸሽቷል፡፡

በዚህ ድብልቅልቅ ያለ ውጊያ ከሃምሳ ስድስቱ የጣሊያን መድፎች በተጨማሪ ብዙ ሺህ ቀላልና ከባድ መትረየሶች እንዲሁም የነፍስ ወከፍ ጠመንጃዎች በአሥር ሺዎችና በመቶ ሺዎች ከሚቆጠሩ መሰል ጥይቶቻቸው ጋር ተማርከዋል፡፡ በአጠቃላይ ምርኮው ወደ አዲስ አበባ የተጓጓዘው በአምስት መቶ አጋስሶች ተጭኖ ነው፡፡ ታላቁ የጥቁር ሕዝቦች ድል የዓድዋ ድል በመላው ዓለም ፖለቲካ ላይ ከፍተኛና ዋነኛ ለውጦች አምጥቷል፡፡

የእንግሊዝ ጋዜጦች በዓድዋ ድል ማግስት የዓለም ታሪክ ተገለበጠ ታላቅ የትውልድ ኃይል በአፍሪካ ተቀሰቀሰ … ብለው ፃፉ፡፡ ዘመናዊት ኢትዮጵያን የፈጠሩ የተባሉት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በሌሉበት እና በአካል ባልተገኙበት የነፃነት ተጋድሎ መሪዎች ጉባኤ የአፍሪካ ብሎም የመላው ዓለም ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተጋድሎ መሪ ተደርገው ተመርጠዋል።

በዚህ ለነፃነት፣ ለፍትህና ለእኩልነት በተደረገው ተጋድሎ በግንባር ቀደምትነት የሚነሱ 12 የጦር መሪዎች አሉ። የእነዚህ የሀገር ባለውለታ አባቶች ገድል በዚህ ፅሑፍ እናስነብባችኋለን። በመጀመሪያ የምናገኛቸው ፊት አውራሪ ገበያው ገቦ ጉርሙ ወይም በጀግንነት ስማቸው አባ ጎረው ናቸው። እኚህ ሰው ከአድዋ ጦርነት አስቀድሞ ከነበረው ከአምባለጌ ጦርነት ጀምሮ ለሀገራቸው ነፃነት ትልቅ ተጋድሎ ያደረጉ አዋጊና ተዋጊ ሰው ናቸው። በመድፍ ተኳሽነታቸው የሚታወቁት ፊት አውራሪ ገበያው ከጠላት ጋር በጀግንነት ሲዋጉ ቆይታው በጦርነቱ የመጨረሻ ቀን በክብር ተሰውተዋል።

ሌለኛው የዓድዋ ጀግና ልዑል ራስ መኮንን ወልደሚካኤል ጉዲሳ ናቸው። በጀግንነት ስማቸው ደግሞ አባ ቀኘው። እኚህ ጀግናም ከአምበላጌ ጦርነት ጀምሮ እስከ ዓድዋ ጦረኛ በማዝመት ፈረሰኛና እግረኛ በመምራት ተዋጊቶ በማዋጋት ለሀገራቸው ሉዓላዊነት ትልቅ ጀብዱ የፈፀሙ ሰው ናቸው። እኚህ ሰው ከዚህ በተጨማሪ ወራሪው ጣልያን የውጫሌን ውል አስታኮ ኢትዮጵያን ለመውረር ስመጣ ጉዳዩን በሰላም እልባት እንዲያገኝ ለማድረግ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ያደረጉ ሰው ናቸው። ጦርነቱ አይቀሬ ሲሆን ግን በጀግንነት ተፋልመው ሀገራቸውን ከወራሪ ታድገዋል።

በሦስተኛነት የምናነሳቸው ደግሞ ንጉሥ ተክለሃይማኖት ተሰማ ጎሹ ናቸው። በጀግንነት ስማቸው ደግሞ አባ ጠና ይሰኛሉ። ንጉሥ ተክለሃይማኖት ከአድዋ ጦርነት አስቀድሞ በነበሩ በተለያዩ ዓውደ ውጊያዎች ተሳትፎ አድርገዋል። በዓድዋ ጦርነት ደግሞ ፈረሰኛን ከእግረኛ አዋህደው በመምራት ጠላትን በጀግንነት ተፋልመው ያርበደበዱ ለሀገራቸው ነፃነት መስዋዕትነት የከፈሉ ጀግና ናቸው።

ሌለኛው ሰው ደግሞ ንጉሥ ሚካኤል አሊ ልበን ናቸው። የጀግንነት ስማቸው ደግሞ አባ ሻንቆ ይሰኛል። እኚህም ሰው በተመሳሳይ ከዓድዋ ጦርነት ባሸገር በተለያዩ አውደ ውጊያዎች ማለትም በመቀሌ፣ በአምባለጌ ጦርነቶች እግረኛና ፈረሰኛ ጦር ድንቅ በሆነ ሁኔታ በመምራት ለሀገራቸው ውድ ዋጋ የከፈሉ ጀግና ኢትዮጵያዊ ናቸው።

በአምስተኛ ደረጃ ላይ የምንመለከታቸው ደግሞ ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ ሮባ ናቸው። አባ ነፍሶ በተሰኘው የፈረስ ስማቸው የሚታወቁት እኚህ ጀግና የንጉሥ ምንልክ የግምጃ ቤት በጅሮንድም ነበሩ። እኚህ ጀግና ሰው በተመሳሳይ በመቀሌና በዓድዋ ጦርነቶች እግረኛና ፈረሰኛ ጦር በመምራት ለሀገራቸው በጀግንነት የተፋለሙ ሰው ናቸው። “ገበያው ቢሞት ተተካ ባልቻ መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ” ተብሎ የተገጠመላቸው ደጃዝማች ባልቻ በዓድዋ ጦርነት ሽንፈት ተከናንቦ የተመለሰው የጣሊያን ጦር ኢትዮጵያን ከዓመታት በኋላ ደግም ስወረት በወቅቱ ከንጉሥ ኃይለሥላሴ ጋር ስምምነት ባይኖራቸውም ከራሳቸው ጉዳይ ሀገራቸውን በማስቀደም ደግም በጀግንነት ተፋልመው የተሰው ጀግና ናቸው።

ራስ ወሌ ብጡል ኃይለማርያም ደግሞ ሌላኛው ሰው ናቸው። በጀግንነት ወይም በፈረስ ስማቸው አባ ጠጣው የሚሰኙት እኚህ ሰው ጀግና ጦረኛ እንደነበሩ ይነገርላቸዋል። እንደ ሌሎች የኢትዮጵያ ጀግኖች ሁሉ ጦራቸውን ከአምበላጌ እስከ ዓድዋ ዘምተውና አዝምተው ለሀገራቸውና ሕዝባቸው ሉዓላዊነትና ነፃነት ትልቅ ዋጋ የከፈሉ ጀግና ናቸው። ራስ ወሌ የእቴጌ ጣይቱ ወንድም ሲሆኑ፤ ደጀኑን ጦር ከደብረ ታቦር ተነስተው እየመሩ በቅድሚያ የዘመቱት በአምባላጌ ግንባር ነበር።

በሰባተኛ ላይ የምናነሳቸው ጀግና ደግሞ ፊት አውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ ሁንዱል ናቸው። አባ መቻል በተሰኘው የጀግንነት ስማቸው የሚታወቁት እኚህ ሰው በጦር አማካሪነታቸውም ይታወሳሉ። እኚህ ሰው ፊት አውራሪ ገበያው በጦር ሜዳ በጀግንነት ስሰው የሳቸውን ቦታ ተረክበው ጦር በማዝመት ድል የተቀዳጁ ጀግና ናቸው። በፈረስም በእግርም ተዋግተውና አዋግተው ለሀገር ነፃነት የተዋደቁ ሰው ናቸው።

ፊት አውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ በጦረኝነታቸው ወደር ከሌላቸው ውድ ኢትዮጵያዊ ጀግኖች መካከል አንዱ ናቸው። በዓድዋ የጦርነት ውሎ በርከት ያለ ሠራዊት ይዘው ጉልህ የጀግንነት ተጋድሎ አድርገዋል። እኚህን ሰው በፍርድ አዋቂነታቸው ስማቸውም ሀብቴ አባ መላ ይሉዋቸዋል። አባ መላ አጼ ምኒልክ ካረፉ በኋላ የስልጣን ሽኩቻ እንዳይነሳ በማለት ሀገሪቷን በማረጋጋት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል።

ራስ አሉላ እንግዳ ቁቢ ሌላኛው የዚህ ታሪክ አካል ጀግና ናቸው። በጀግንነት ስማቸው አባ ነጋ ይሰኛሉ። በስለላ ታሪካቸው የሚታወቁት እኚህ ሰው በተለይ የጣሊያን ጦር አሰላለፍ ምን ይመስላል የሚለውን በደንብ በመረዳት የኢትዮጵያ ጦር የተሻለ ቦታ ይዞ እንዲጠብቅና በወራሪው የጣሊያን ጦር ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እንዲያደርስ ጉልህ አስተዋጽኦ የነበራቸው ሰው ናቸው። ተዋግተውና አዋግተውም በጦር ሜዳ ጀብዱ የፈፀሙ የጦር መሪ ናቸው።

ሌለኛው ጀግና ደግሞ ራስ መንገሻ ዮሐንስ ምርጫ ናቸው። በጀግንነት ስማቸው አባ ግጠም ይሰኛሉ። እኚህ ሰው ከአድዋ አስቀድሞ በነበሩ አውደ ውጊያዎች የተሳተፉ ናቸው። በተለይ በሁናትና ሰናፍ ግምባር ትልቅ ታሪክ የሰሩ ሰው ናቸው። በዓድዋ ጦርነትም በመሪነት ተሳትፈው የተዋደቁና ለሀገራቸው ትልቅ ዋጋ የከፈሉ ጀግና ሰው ናቸው።

ታሪክ በደማቅ ቀለም ከትቦ ካስቀመጣቸው የጦር መሪዎች መካከል ዋቅሹም ጓንጉል ብሩ ገብረመድህን አንዱ ናቸው። በጀግንነት ስማቸው አባ መርከብ ይሰኛሉ። እኚህ ጀግና በተለያዩ አውደ ውጊያዎች የተፋለሙ ሰው ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ የወራሪውን የጣሊያን ጦር መሪ ጄኔራል አልቤርቶኒን ጨምሮ ሌሎች የጠላት ጦር አባላትን በመማረክ ለአድዋ ድል ጉልህ አስተዋጽኦ የነበረቸው የጦር መሪ ናቸው።

ራስ አባተ ቧያለው ንጉሡ ሌለኛው የአድዋ ጀግና የጦር መሪ ናቸው። በጀግንነት ስማቸው አባ ይትረፍ ይሰኛሉ። የልቀ መኳንነት ማዕረግ የነበረችው እኚህ ሰው በመድፍ ተኳሽነተቸው የሚታወቀውና በተለያዩ አውደ ውጊያዎች ትልቅ ተገድሎ የደረጉ የኢትዮጵያ ጀግና ናቸው። እዚህ ላይ አንድ ትለቅ ገድል እናነሳለን እሱም ከዓድዋ በፊት የመቀሌውን ስትራቴጅካዊ የውሃ ምንጭ የመያዝ የራስ አባተ ቧ ያለው እና የደጃዝማች ባልቻ አባ ሳፎን ጀብዱ።

አፄ ምኒልክ ጦራቸው መቀሌ ደርሶ ሰፈሩን ተከፋፍሎ ከያዘ በኋላ በጣልያን ምሽጉ ዙሪያ ራቅ እያለ ሰፈረ። ድንኳን በሚተከልበትና ጭነት በሚራገፍበት ጊዜ አንድ በቅሎ ፈርጥጦ ወደ ጣልያኖች ምሽግ ሮጠ። አንድ ሰው ሊመልሰው ሲሮጥ ባዩ ጊዜ ጣልያኖቹ የመድፍ ተኩስ ጀመሩ። ጣልያኖቹ አብዝተው መተኮሳቸውን ንጉሰ ነገስቱ በተመለከቱ ጊዜ ሊቀ መኳስ (በኋላ ራስ) አባተ ቧ ያለውን እና በጅሮንድ (በኋላ ደጅአዝማች) ባልቻ አባ ሳፎን ሂዱ እናንተም ተኩሱባቸው ብለው አዘዙ እና የምሽቱ ጊዜ በመድፍ ተኩስ አለፈ። ወደ ማታ ንጉሱ እንደገና ሊቀ መኩስ አባተን እና በጅሮንድ ባልቻን ጠርተው “እነዚህን ጣልያኖች ከጉድጓዳቸው ሳላስወጣ የትም አልሄድም እናንተም የጠላት መድፍ ጥይት የማይደርስበትን ስፍራ መርጣችሁ ከዚያ ሆናችሁ ምሽጉን በመድፍ ምቱት” ብለው አዘዟቸው።

ሊቀ መኳስ አባተ ጦራቸውን ይዘው በምሽጉ በስተግራ የጣልያኖችን ቃፊር ጠባቂ አባርረው ምሽግ አበጅተው መድፍና መትረየሳቸውን እንደጠመዱ በጅሮንድ ባልቻም በስተቀኝ በኩል ሌሊቱን ምሽግ ሰርተው መድፍ እና መትረየሳቸውን ጠመዱ። ጣልያኖችም የእነሱን መጠጋት ባወቁ ጊዜ የመድፍ እና የጠመንጃ ተኩስ አበረከቱ። አነጣጥሮ በመተኮስ የተመሰገኑት ሊቀ መኳስ አባተም በሩቅ በሚያሳየው መነጸራቸው ጣልያኖች ታቦቱን አስወጥተው መድፍ በመትከል የመሸጉበትን ቤተክርስትያን ህንፃ በመመልከታቸው አስተካክለው ቢተኩሱ የመድፉ ጥይት በቤተክርስቲያኑ መስኮት ገብቶ የጠላትን መድፍ እግር ሰባበረው። ጣልያኖችም ከተበላሸው መድፋቸው ጭስ እየጨሰ ባዩ ጊዜ በአፀፋው የመድፍ ጥይት ሊቀመኳስ አባተን እና በጅሮንድ ባልቻ ባሉበት ቦታ ላይ እንደ በረዶ አወረዱባቸው። ነገር ግን አንድም ሰው አልቆሰለም። ይህን ውጊያም አፄ ምኒልክ፣ ንጉስ ተክለ ሃይማኖት እና ሌሎችም መኳንንቶች ከድንኳናቸው ወደላይ ካለው ከፍተኛ ስፍራ ላይ ሆነው በመነፀር ይመለከቱ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል።

ራስ ቢትወደድ መንገሻ አቲከም ቢተርፉ ሌላኛው የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ድል የሆነው አድዋ ጦርነት ተሳተፊ የጦር መሪ ናቸው። በጀግንነት ስማቸው አባ ገድብ ይሰኛሉ። በንጉሥ ምኒልክ ይወደዱ የነበሩት እኚህ ሰው የራስ ቢትወደድነት ማዕረግ ያገኙት በጦር ምክራቸው የታወቁ ስለነበር ነው። በዓድዋ ጦርነት እግረኛና ፈረሰኛ አዝምታው ትልቅ ድል የተቀዳጁት እኚህ የጦር ጀግና ከጦርነቱ በኋላም ድሉን ተከትሎ በተካሄደውና አንድ ኢትዮጵያ በፀነችበትን የውጫሌ ውል ደግሞ ውድቅ በሆነበት የአዲስ አበባው ስምምነትና የሰላም ድርድር የተከፈሉ ሰው ናቸው።

የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን ከጥግ እስከ ጥግ ቀፎው እንደተነካበት ንብ ተምመው በአንድ ጥላ ስር እንዲሰባሰቡ ያደረገ ታሪካዊ ክስተት በመሆኑ የኢትዮጵያውያንን ትብብር እና አንድነት ከማሳየቱም በላይ ለመላው የጥቁር ህዝብ የነፃነት ምልክት መሆናችንን ማሳያ ነው።

ከኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ባለፈ የአፍሪካውያን ብሎም ጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ድል የሆነው ዓድዋ የተገኘው እንደ ድር አብረው ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው ነፃነት በተዋደቁ በእነዚህ ፊት አውራሪ የጦር ጀግኖች ነውና ዛሬ ላይ ለእነዚህ አባቶቻችን ክብር እጅ እንነሳለን።

ክብረአብ በላቸው

አዲስ ዘመን የካቲት 6/2016

 

Recommended For You