
አዲስ አበባ፦ የሚሠራና የሚተጋ እጅ ሀገር እንደሚቀይር ጅግጅጋ ከተማ ጥሩ ማሳያ ናት ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሰሞኑን በሶማሌ ክልል የተለያዩ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በወቅቱ፤ ጉብኝቱ ብዙ ትምህርት የተገኘበት መሆኑን ጠቁመው፤ የሚሠራና የሚተጋ እጅ ሀገር እንደሚቀይር ጅግጅጋ ከተማ ጥሩ ማሳያ ናት ብለዋል። የሶማሌ ክልል በምሥራቁ ቀጣና ለሀገሪቱና ለጎረቤት ሀገራት ትልቅ የገበያ ማዕከል ሆኖ ማገልገል እንደሚችል የሚያሳይ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በአጠቃላይ በሶማሌ ክልል በተገኘው ሰላምና አመራሩ ባደረገው ጥረት ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚ መነቃቃት መታየቱን ገልጸዋል።
በክልሉ የመሠረተ ልማት ግንባታ፣ በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በገቢና በበጀት ዕድገት እየታየ መሆኑን አንስተው፤ ይህ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አቅጣጫ አስቀምጠዋል። በሶማሌ ክልል የተጀመሩት የልማት ሥራዎች ከለፋን፣ ከሠራን፣ ከጣርንና ሰላማችንን ማረጋገጥ ከቻልን ባጠረ ጊዜ ውስጥ የሰውን የሕይወት ደረጃ ከፍ ማድረግ እንደሚቻል ያሳያሉ ሲሉ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳመለከቱት፤ ከሦስት ዓመታት በፊት ጅግጅጋ ምናልባትም ሰባትና ስምንት ኪሎ ሜትር የሚሸፍን አንድ የአስፋልት መንገድ ያላት ከተማ ነበረች። አሁን ላይ ከ40 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍን የመኪና፣ የብስክሌትና የእግረኛ መንገድ ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ ነው። ከመንገድ አንፃር በሶማሌ ክልል ከ2 ሺህ ኪሎ ሜትር ያላነሰ መንገድ እየተገነባ ነው።
ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት ውስጥ በሶማሌ ክልል 68 ከተሞችና በርካታ ወረዳዎች የ24 ሰዓት መብራት እያገኙ መሆኑን አስታውቀዋል። በጤናው ዘርፍም ከለውጡ በፊት በክልሉ ዘጠኝ ሆስፒታሎች ብቻ ነበሩ፤ ከለውጡ በኋላ ግን 11 ተገንብተዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በጅግጅጋ የተመለከትነው ግዙፍና ሁሉም ነገር የተሟላለት ሆስፒታል ለጎረቤት ሀገራትም አገልግሎት የሚሰጥ ነው ሲሉ አስረድተዋል።
የግሉ ዘርፍ ከተማ ውስጥ እየገነባ ያለው ህንፃ፣ የቤቶች ግንባታና አጠቃላይ የከተማው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሥራ ዕድል እንዳለ ያመላክታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህም ክልሉ የተሟላ መንግሥት ሆኖ ሰዎችን ማገልገል የሚያስችለውን ብቃት እየፈጠረ መሆኑን ያሳያል ብለዋል። በጅግጅጋ ከተማ በቀጣይ ብዙ ዛፍ መትከል፣ አካባቢውን ማጽዳትና ከዲዛይን ውጪ ያሉ ቤቶችን ማስተካከል እንደሚገባ ጠቁመው፤ ይህ ከሆነ ጅግጅጋ በሚቀጥሉት አምስትና 10 ዓመታት አማራጭ ዋና ከተማ መሆን እንደምትችል ገልጸዋል።
በጉብኝታቸው የእድሳት ሥራ የተከናወነለትን የጅግጅጋ ሼህ ሀሰን ያባሬ ሪፈራል ሆስፒታልን፣ ሸበሌ ዞን ቤርዓኖ ወረዳ እየለማ ያለውን የመስኖ ልማት ሥራ፣ አዲሱን የክልሉን ምክር ቤት ሕንፃና ሁለተኛው ዙር የጂግጂጋ ከተማ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የሥራ እንቅስቃሴን ተመልክተዋል። በሶማሌ ክልል ጎዴ ከተማ አዲስ የተገነባውን ኡጋስ ሚራድ አውሮፕላን ማረፊያን መርቀው የከፈቱ ሲሆን የተለያዩ የልማት ሥራዎችንም ጎብኝተዋል።
በተጨማሪም ከቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጋር የጅግጅጋ ዱቄት እና ዳቦ ፋብሪካን አስመርቀዋል፤ ፋብሪካው በቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት እየተሠሩ ካሉ ደሃ ተኮር ሥራዎች አንዱና በመላው ሀገሪቷ እየተሠሩ ከሚገኙ 12 መሰል ፋብሪካዎች ስምንተኛው መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን የካቲት 6/2016