የአዲስ አበባን የዲፕሎማቲክ መቀመጫነቷን የማጽናት ተጨማሪ ጉዞ

አዲስ አበባ ከተማ በዓለም ሦስተኛዋ የዲፕሎማቲክ መቀመጫ ናት። ይህ ደግሞ እንዲሁ ሳይሆን በከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጥረት የመጣ ነው። አፍሪካ አንድነት ከመመስረቱ ዋዜማ ጀምሮ የነበሩ የኢትዮጵያ መሪዎች የአፍሪካ መቀመጫነቷን ለማስከበር መጠነ ሰፊ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን ሠርተዋል። ሀገሪቱ ለአፍሪካውያን ነጻነት ካበረከተችው አስተዋጽኦ አንጻር፤ለአፍሪካ መቀመጫነት መመረጥ ቢያንስ እንጂ የሚበዛባት እንዳልሆነም በብርቱ ሞግተዋል ።

ይህም ሆኖ አሁንም አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲናነቷንና የዲፕሎማቲክ መቀመጫነቷን ከማስቀጠል ባለፈ፤ለነዋሪዎቹ ዋና ለዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ የተሻለች ለማድረግ ሰፊ ተግባራት እየተከናወኑ ነው። እንደ ስሟም እንድትሆን ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው። በዚህም እየተመዘገበ ያለው ውጤት አበረታች ነው።

ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት አዲስ አበባ የነበራት ገጽታ ምን ይመስል እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። የከተማዋ የተለያዩ ክፍሎች ገጽታዋን በሚያጎድፍ መንገድ በቆሻሻ ተውጠው ማየት የተለመደ ነበር። አብዛኞቹ እነዚህ ስፍራዎች አሁን ላይ ያሉበት ሁኔታ ለብዙዎቻችን አስደማሚ ነው።

በ«ገበታ ለሸገር»ፕሮጀክት የተገነቡት የአድዋ መታሰቢያ ሙዚየም፤ የአንድነትና እንጦጦ ፓርኮች፣ የወዳጅነት አደባባይ ቁጥር አንድና ሁለት፣ የሳይንስ ሙዚየም፣ የወንዝ ዳርቻዎችንና የመንገድ አካፋዮች ፕሮጀክቶች …ወዘተ በከተማዋ ማራኪ ገጽታ ላይ የፈጠሩት አቅም ነዋሪው በተጨባጭ እየታዘበው ያለው እውነታ ነው። ይህም አዲስ አበባ ስሟን የሚመጥን ገጽታ እንድትላበስ ለማድረግ እየተከናወነ ያለውን ተግባር በተጨባጭ የሚያሳይ ነው።

በመዲናይቱ የተገነቡት ፕሮጀክቶች የውጭ ሀገር ቱሪስቶችን በመሳብ ‹‹ ጭስ አልባ ኢንዱስትሪ›› በመባል የሚታወቀውን ቱሪዝምን በማሳደግ ሀገራዊ ገቢን እያሳደጉ ነው። ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች የቆይታ ጊዜ እንዲራዘም በማድረግ ተጨማሪ ገቢ እንዲገኝ ሚናቸው የጎላ ነው። በተጨማሪም ለበርካታ ዜጎች ሥራ ዕድል ፈጥረዋል፤ እየፈጠሩም ይገኛሉ።

እነዚህ ፕሮጀክቶች እንደ ሀገር ያሉትን ሀብቶች በተገቢው ሁኔታ በማልማት ለዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት አስተዋጽኦ ማዋል አስፈላጊ መሆኑን ጉልህ ማሳያ ተደርገው የሚወሰዱ ናቸው። ያሉ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ጸጋዎችን በማልማት መጠቀም ሲቻል የዜጎችን ኑሮ ማሻሻል፤ ሀገርን መለወጥ ይቻላል የሚለውንም መልእክት የተሸከሙ ስለመሆናቸው ነጋሪ አያስፈልጋቸውም።

ላለፉት አምስት ዓመታት አዲስ አበባ ስሟን የሚመጥን ገጽታ እንድትላበስ በርካታ ፕሮጀክቶች ተገንብተዋል፤ እየተገነቡም ነው። ከፕሮጀክቶች መካከል የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ከሀገር አልፎ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የቱሪስት መስህብ እንደሚሆን ይታመናል። ክስተቱ ለጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ትግል ከፈጠረው የመንፈስ ልእልና አንጻር የብዙዎችን ቀልብ የሚስብ ነው ።

ፕሮጀክቱ በውስጡ ኢትዮጵያውያን ዘመናዊ መሳሪያ ታጥቆ የመጣን የጣሊያን ወራሪን ድል የነሱበት ምስጢር፤ አንድነታቸውንና የአይበገሬነታቸውን በሚመጥን መልኩ የሚዘክር ነው። የኢትዮጵያውያን የወል ትርክት መሰረት ሆኖ በትውልዶች መካከል ሊያገለግል የሚችል የታሪካቸው ትልቁ አካል ነው።

ዓድዋ ሲነሳ ኢትዮጵያውያን ብሔር፤ ጎሳ፤ዘር፤ ቀለም፤ ኃይማኖት ሳይሉ በአንድ ጥላ ስር ሆነው ጠላትን ድል የነሱበት የአብሮነት አሻራ ነው። ሀገርንና ህዝብን ከፍታ ላይ ካስቀመጠው የድል ትርክቱ ባሻግር ልዩነቶችን የቱን ያህል ሀገራዊ አቅም እንደሚሆኑም ማሳያ ነው።

የዓድዋ መታሰቢ ሙዚየም ስሙን በትክክል እንዲገልጽ የኢትዮጵያውያንና የአፍሪካውያን የነጻነት አርማና ምልክት ሆኖ እንዲዘልቅ፤ሁሉም ክልሎች ያላቸውን የተለያዩ ቅርሶች እንዲሰጡ ጥሪ ተደርጎላቸዋል። በጥሪው መሰረት በአድዋ ጦርነት ጥቅም ላይ የዋሉ ልዩ ልዩ ቅርሶችን እየሰጡ ነው።

ሙዚየሙ ከትናንት በስቲያ በድምቀት የተመረቀ ሲሆን፤ በቅርቡም ለጎብኚዎች ክፍት እንደሚሆን ይጠበቃል። ዓድዋንና መሰል የጋራ ታሪኮችን በተገቢው መንገድ ለትውልዱ በማስተማር ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን በጽኑ መሰረት ላይ እንዲገነባ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህ ሲሆን ከጥላቻ ይልቅ አብሮነትን በማስፈን ሰላምና ዲሞክራሲ የዳበረባት ሀገር ለመፍጠር ያስችላል።

ባለፉት ስድስት ወራት ከመዲናዋ የተገነቡ ፕሮጀክቶች የከተማዋን ገጽታ ከመገንባት ባለፈ፤ ቱሪስቶች በከተማዋ የሚኖራቸውን ቆይታ በማራዘም፤ ጥልቅ የገቢ ምንጭ እንደሚሆን ይታመናል። ለብዙ ዜጎችም የሥራ እድል እንደሚፈጥር የቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ እንዲራዘም ፤ለብዙ ዜጎችም የሥራ ዕድል በመፍጠር ከፍያለ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይታመናል ።

በሚቀጥለው የካቲት ወር በአዲስ አበባ የሚካሄደውን የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ አስመልክቶ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎችና የሉዑካን ቡድኖች ወደ አዲስ አበባ ይገባሉ። ይህንን ታሳቢ በማድረግም አዲስ አበባ በተሻለ ገጽታ እንኳን ደህና መጣችሁ ለማለት ዝግጅቷን በስፋት ቀጥላለች።

በመዲናዋ ባለፉት ሦስት ዓመታት የተገነቡ ፕሮጀክቶች የጉባኤው ተሳታፊዎችን የቆይታ ጊዜ በማራዘም ተጨማሪ ገቢ እንዲገኝና የኢትዮጵያን ገጽታ ለመገንባት ትልቅ ዕድል ይፈጥራሉ። የጉባኤው ተሳታፊዎች፣ እንደ ወወዳጅነት ፓርክ፤ እንጦጦ ፓርክና መሰል የመዲናይቱን ልዩ ገጽታ በመጎብኘት ጥሩ ጊዜ የሚሳልፉበት ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል ተብሎ ይታመናል።

ፕሮጀክቶቹ አዲስ አበባ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ መዲናና የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫነቷን የማጽናት አንድ እርምጃ ናቸው። መሰል ፕሮጀክቶች በክልል ከተሞች በማስፋት አጠቃላይ የሆነውን የኢትዮጵያን ገጽታ የመገንባት ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

በቀጣይነትም የከተማዋን በአጠቃላይ በሀገሪቱ ውስጥና የውጭ ቱሪስቶችን ቁጥር ለማሳደግ የተለያዩ ሁነቶች ማዘጋጀት፤ በከተማው ውስጥ ያሉ የቱሪስት መስህብ ቦታዎችን በዓለም አቀፍ መድረኮች የማስተዋወቅና ተደራሽነታቸውን የማሳድረግ ሥራ ሊሠራ ይገባል እንላለን።

ግርማ ሞገስ

አዲስ ዘመን የካቲት 5/2016

 

Recommended For You