ዲፕሎማሲ እና አሁናዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ

ዲፕሎማቶችና የፖለቲካ ምሁራን እንደሚሉት፤ የዲፕሎማሲው ዘርፍ በዋናነት የሚያተኩረው ወዳጅና ጠላት የሚለውን ሳይሆን ብሔራዊ ጥቅም እና ሉዓላዊነትን ነው። ከዚህ አንጻር ለሀገር ክብርና ጥቅም ሲባል የሚደረሱ ስምምነቶች እና ውሳኔዎች አሉ ፤ ወደፊትም ይኖራሉ፡፡

ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሀገራት ያላቸውን ፀጋዎች ለመጋራት፤ የጎደላቸውን ለማሟላት አስተዋጽኦው የማይተካ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳም ሁሌም ዘመኑን የዋጀ ሁነኛ የዲፕሎማሲያዊ ስትራቴጂዎችንና መርሆችን ነድፎ በአግባቡ መጓዝ ከምንም በላይ ለዛሬው ሆነ ለነገው የሀገር ኃያልነት ወሳኝ ነው፡፡

ዲፕሎማሲ በሀገራትና መንግሥታት እንዲሁም በዓለም አቀፍ ተቋማት መካከል የሚካሄድ ዘርፈ ብዙ የውጭ ግንኙነቶች የሚከወኑበት ሁነኛ ጥበብ ነው፤ የዲፕሎማሲ ዋና ተግባርም በሀገራት መካከል ዓለም አቀፍ ግንኙነቶችን ማስተዳደር እና ሰላማዊ ግንኙነትን ማረጋገጥ ነው፡፡

የንግድ ስምምነት ድርድሮችን፣ በጋራ ችግሮች ዙሪያ ውይይትን፣ አዳዲስ ፖሊሲዎች መተግበርን እና አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍታትን የመሳሰሉ አንኳር የዲፕሎማሲ መርሆችን ተከትሎ መሥራት ነው። ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ አዲስ ሥራ አይደለም፡፡ የሺህ ዓመታት ጉዞ ነው፡፡

በዲፕሎማሲ ግንኙነት ውስጥ ተጋግዞ የመለወጥ መርህ፤ የተሻለውን መምረጥና መያዝ የተለመደ ነው። ከዚህም ባለፈ ወዳጅን ማብዛት፣ ‹‹የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው …›› የሚሉ በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ውስጥ ትልቅ ስፍራ የሚሰጣቸው፤ ሀገራት ትኩረት ሰጥተው የሚንቀሳቀሱባቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ ከቀደመው ዘመን ጀምሮ ገለልተኛ እና ወዳጆችን በማስፋት ላይ የተመሠረተ ዲፕሎማሲ ብትከተልም፤ የዓድዋን ድል ተከትሎ የራሷን ነፃነት ከማስጠበቅ ባለፈ የአፍሪካውያን ነፃነት ጭምር አንቀሳቃሽ ሞተር መሆን መቻሏ፤ በበርካታ የምዕራቡ ዓለም ሀገራት ባልተገባ ዓይን እንድትታይ፤ ከፍ ባለ ያልተገባ ዲፕሎማሲ ጫና ውስጥ እንድትገባ እንዳደረጋት ብዙዎች ይስማማሉ፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ያላት የተፈጥሮ ሀብትና የምትገኝበት ጂኦፖለቲካል አቀማመጥም ፤«የዝሆን ሞት ምክንያቱ የራሱ ጥርስ ነው፡፡» እንደሚባለው በዓለም አቀፍ ደረጃ /ዲፕሎማሲያዊ ጫና እንዲበረታባት፤ በየዘመኑ ላጋጠማት ሀገራዊ ፈተናዎች ምክንያት እየሆነባት ነው፡፡

ሀገሪቱ የዓለም 60 በመቶ ንግድ በሚንቀሳቀስበት የቀይ ባሕር ቀጣና የምትገኝ፤ የረጅም ዘመናት የሀገረ መንግሥት ታሪክ ባለቤት መሆኗም፤ እድገቷን በማይፈልጉ ታሪካዊ ጠላቶቿ እና የነሱን ፍላጎት በማሟላት ተጠቃሚነታቸውን ለማጽናት በሚፈልጉ ኃይሎች በጥርጣሪና በጠላትነት ለመታየት ተገዳለች።

በዚህም ሀገሪቱ እንደ አንድ ሉአላዊት ሀገር አንድ የሆነ ፕሮጀክት ነድፍ ተግባራዊ ለማድረግ ስትነሳ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የተለያዩ ጫናዎች ሲደረጉባት መመልከት የተለመደ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የዓባይን ወንዝ በተመለከተ በሀገሪቱ ላይ እየደረሰ ያለውን ጫና ማየት በቂ ነው።

በኢትዮጵያ እና በግብጽ መካከል በዓባይ ወንዝን ውሃ አጠቃቀምን አስመልክቶ ያለው አለመግባባት ምን እንደሚመስል፤ አሁን ባለንበት የሰለጠነው ዓለም አለመግባባቶቹ ለዘለቄታው በምን መፈታት እንዳለባቸው ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ባእድ ይሆናል ተብሎ አይታሰብም።

ይህም ሆኖ ግን የስዊዝ ካናል ከተከፈተ ማግስት ጀምሮ አንዳንድ ምዕራባውያን ግብጽን በማስደሰት የካናሉ የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን በኢትዮጵያ ላይ በሕግም በሞራልም አግባብነት የሌላቸው የተለያዩ ጫናዎችን ሲፈጥሩ ይስተዋላሉ፡፡ ኢትዮጵያ የራሷ የተፈጥሮ ሀብት በሆነው የዓባይ ወንዝ እንዳትጠቀም ለዘመናት ስታሴር ለኖረችውና ዛሬም እያሴረች ላለችው ግብጽ ሲወግኑ ማየትም የተለመደ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የዓባይን ወንዝ በመጠቀም የዜጎቿን ሕይወት የመለወጥ ሙሉ መብት አላት፤ ይህንን የተፈጥሮ ፀጋዋን በፍትሐዊነት መርህ አልምታ እንዳትጠቀም የሚከለክላት የሕግ ሆነ የሞራል ክልከላ የለባትም። በዚህ ጉዳይ የሚመጡ ተጽእኖዎች የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር በአዲስ ዘመን እሳቤ ብዙ የሚያራምዱ አይደሉም።

በርግጥ ሀገሪቱ የተፈጥሮ ፀጋዎቿን በማልማት ልትፈጥረው የምትችለው ተፅእኖ ፈጣሪነት ስጋጥ ለሚሆንባቸው ኃይላትና ሀገራት፤ ጉዳዩን በዝምታ ያዩታል ተብሎ የሚታሰብ አይደለም፤ የማልማት/ መልማት አስተሳሰቡ በራሱ ሊያመጣ የሚችለው ተግዳሮትም ቀልሎ የሚታይ አይደለም ።

ኢትዮጵያ እነዚህን ጫናዎች ባላት የዘመናት የዲፕሎማሲ ተሞክሮ ለማርገብ ረጅም መንገዶችን ተጉዛለች፤ በዚህም በየዘመኑ ያስመዘገበቻቸው ስኬቶች፤ ዛሬም በዲፕሎማሲው ዘርፍ ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲኖራት አስችሏታል። ብሔራዊ ጥቅሞቿን በማስጠበቅ ሂደትም ዋነኛ አቅም ሆኗታል።

አሁን አሁን «ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ» በሚል መርህ አፍሪካዊ አለመግባባቶች /በዓባይ ወንዝ ውሃ አጠቃቀም ዙሪያ ያለው አለመግባባትም ጭምር /ከአፍሪካዊ ተቋም እና አፍሪካውያን እጅ እንዳይወጣ በማድረግ በአደራዳሪነት ስም ገብተው ጉዳዩን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ሊወስዱ የሚፈልጉ አካላት ፍላጎት እንዳይሳካ አድርጋለች።

በተለይም በቀጣይ በዓባይ ወንዝ ውሃ አጠቃቀም ዙሪያ የሚደረጉ ድርድሮች ፤ ዓለም አቀፍ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ውሃ አጠቃቀም መርህን እና ሕግን በተከተለ መንገድ በአፍሪካውያን እና አፍሪካዊ ተቋም ብቻ እልባት እንዲያገኝ እየሰራች ነው፡፡ ይህ ድል ዝም ብሎ የመጣ ሳይሆን የዘመናት የዲፕሎማሲያዊ ጥበብ/ ተሞክሮ ውጤት ነው፡፡

ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ የገጠሟትን ዓለም አቀፍ ጫናዎችን ለመቋቋም፣ ኢኮኖሚያዊ ግቦቿን ለማሳካት፣ ከሀገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር ለመሥራት በዲፕሎማሲው ዘርፍ የፈጠረችው ስኬት ዋነኛ ተጠቃሽ ነው፡፡ በነዚህ ጊዜያት እንደ ሀገር በርካታ ዲፕሎማሲያዊ ሁነቶች ተከስተዋል፡፡ በዘርፉ የውጭና የውስጥ ተግዳሮቶችን በመቋቋም በርካታ ውጤታማ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡

ክብረ መንግስት

አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You