አረንጓዴ አብዮት ያስፈልገናል

በ2016 በጀት ዓመት ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ታርሷል ። ከዚህም ከ120 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል። በስፋት እየለማ የሚገኘው የስንዴ ምርት ለሸማቹ ተደራሽ የሚሆንባቸው፤ ምርቱ የሀገር ፍጆታን በአግባቡ እንዲሸፈን ከማድረግ በተጨማሪ ለውጭ ገበያ እንዲቀርብ የማድረግ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል፤ መኸርን ጨምሮ በበጋ መስኖ የሚለማው ስንዴ ለታለመለት ዓላማ እንዲውልና ገበያን ማረጋጋት እንዲችል አቅጣጫ መቀመጡን፤ በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ኢሳያስ ለማ ሰሞኑን ለፋና ቴሌቪዥን ጠቁመዋል፡፡

ከስንዴ በተጨማሪም ሌሎች ምርቶችም የሀገር ውስጥ ገበያውን እንዲያረጋጉ የተቀናጀ ርብርብ ይደረጋል ተብሎ ይታመናል። ወደ ውጭ ከመላክ በፊት የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ለማሟላት ጥረት ሊደረግ ይገባል። ለዚህ ደግሞ የግብርና ሚኒስቴር ከአምናው ክፍተት ተምሮ በተለይ የስንዴ ምርት በቀጥታ ለሸማቹ እንዲደርስ በማድረግ ገበያው እንዲረጋጋ አበክሮ መንቀሳቀሱ ይበል የሚያሰኝ ነው።

ባለፈው የምርት ወቅት ከውጪ የሚገባውን ስንዴ ሙሉ በሙሉ በማቆም፣ በተወሰነ ደረጃ ወደ ውጭ መላክ ብንጀምርም፣ ዱቄት አምራቾች ኢንዱስትሪዎቻችን በስንዴ ምክንያት ሥራ ለማቆም መገደዳቸውን መግለጻቸው አልቀረም። በዱቄት ግብዓት እጥረትና በሌሎች ምክንያቶች አጠቃላይ ገበያው የስንዴ ረሀብተኝ እንደሆነ ነው፤ ለዚህም ስንዴን ግብዓት አድርገው የሚመረቱ ሸቀጦች ላይ የሚታየው የዋጋ ንረት አንድ ማሳያ ነው። ይህ ሀገራዊ እውነታ አንድ የሀገሬን ቱባ ባሕል አስታወሰኝ ።

“የአውድማ አግማስ ቅመሱ ፤”አዎ ! ምርቱ እረድኤትና በረከት እንዲኖረው፣ ግርማ ሞገስና አግማስ እንዲኖረው ምርቱ ተሰብስቦ ወደ ጎተራ ከመግባቱ በፊት ገብስ ቆሎ ከተወቀጠ ኑግ ጋር ተቀላቅሎ ወይም በአዋዜና በቅቤ የተቀባ እንጀራ የዶሮ ዓይን ከሚመስል ጠላና አረቄ ጋር ይቀርብና የቀዬው ሽማግሌ ወይም ቄስ አልያም ሼህ መርቆ ይቀመሳል። መንግሥትም ከኤክስፖርቱ በፊት ወይም ጎን ለጎን አጉራ ዘለል የሆነው የግብይት ሥርዓት አደብ አስገዝቶና ደላላውን ከግብይት ሥርዓቱ አስወገዶ ለሸማቹ የአውድማ አግማስ ቅመሱ ለማለት እየተዘጋጀ መሆኑ ተገቢ ውሳኔ ነው። በዘላቂነት መዋቅራዊና ተቋማዊ ችግር የሚስተዋልበትን የግብይት ሥርዓት በማያዳግም ሁኔታ የመፍታት ግዴታም አለበት። በተረፈ በስንዴ ምርት ላይ የመጣው እምርታ በልኩ እውቅና ሊሰጠው ይገባል። አንድምታውንም ሰፋ አድርጎ መመልከትን ይጠይቃል ።

ሉዓላዊነቷንና ነፃነቷን ጠብቃ ሳታስደፍር የኖረች ጥንታዊት ኢትዮጵያ። ቅኝ ያልተገዛች ብቸኛ አፍሪካዊት ሀገር። እስካፍንጫው የታጠቀን ቅኝ ገዢን ከአንድም ሁለት ጊዜ ድል ያደረገች። በፀረ ቅኝ ግዛት ትግሉ ቀንዲል የሆነች። የፓን አፍሪካኒዝምና የብላክ ኮንሽየስ ዋልታና ማገር፤ የራሷ ፊደልና የዘመን አቆጣጠር ያላት፤ የሚሉ እውነቶች ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በተነሱ ቁጥር አብረው የሚወሱ ቢሆንም ድህነቷ፣ ኋላቀርነቷና በምግብ እህል ራሷን አለመቻሏና ተመጽዋችነቷ ጋርዶባት ፤ ጥላውንና አዚሙን ጥሎባት፤ አንጸባራቂ ገጽታዋን አጠልሽቶባት ይገኛል ።

ድርቅና ረሀብ በተነሳ ቁጥር ስሟ አብሮ ይነሳል። በመዝገበ ቃላት ላይም ሆነ በሌላ መጽሐፍ ላይ የረሀብ ምሳሌ ሆና ስትጠቅስ ማንበብ ምን ያህል ቅስም ሰባሪና አንገት አስደፊ እንደሆነ ለኢትዮጵያውያን መንገር ለቀባሪ እንደማርዳት ነው ። ተረጅነትና ተመጽዋችነት ሀገር ፊት ግንባር ላይ ያለ ለምጽ ነው። ቢያንስ ላለፉት 50 ዓመታት ይህ ማንነቷ ኢትዮጵያንም ሆነ ዜጎቿን በሄዱበት እንደ ጥላ ሲከተል ኖሯል። በዓለም አደባባይ በኩራት ደረታችንን ነፍተን፣ አንገታችንን ቀና አድርገን እንዳንራመድ ቀይዶ ይዞን የነበረው የተመጽዋችነት ሰንሰለት ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመበጣጠስ ከጫፍ ደርሰናል ።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ፣ የኩታ ገጠም ግብርና፣ የበጋ ስንዴ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት፤ የሜካናይዜሽን ግብርና፤ የህዳሴው 4ኛ የውሃ ሙሌትና 2ኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት መጀመር፣ ወዘተረፈ. የሀገራችንን ተስፋ ከወዲሁ እያለመለመ ይገኛል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ባለፈው ዓመት በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን የዱግዳና ቦራ ወረዳዎችን የመኸር የስንዴ ኩታ ገጠም እርሻን በጎበኙበት ወቅት፤ በያዝነው አዲሱ ዓመት ስንዴን ለውጭ ሀገር ገበያ ለማቅረብ የተያዘው ግብ እጅግ ተስፋ የሚሰጥ ደረጃ ላይ ይገኛል ማለታቸው ትልቅ ሀገራዊ ብሥራት ነበር። እሳቸው እንዳሉት ባለፈው የምርት ዓመት 38 ሚሊዮን ኩንታል ወደ ውጭ ለመላክ የሚያስችል አቅም ተፈጥሯል ።

ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ስመለስ፤ ኢትዮጵያውያን በዚህ ልክ መሥራታችን ብሔራዊ ክብራችን እና የሀገር ሉዓላዊነታችንን ከማስከበር ጋር በቀጥታ የተገናኘ መሆኑን፤ የመንግሥትም ዋንኛ ትኩረት ከዚህ በፊት የነበረውን ረሀብ የተፈጥሮ ሀብታችንና ያለንን ጉልበት በአግባቡ በመጠቀም ስንዴን ከሀገር ቤት ፍጆታ አልፈን ወደ ውጭ ወደ መላክ መቀየር እንደሆነ ፤ የመሬት መራቆትን ወደማልበስ ለማሸጋገር የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ ተደርጎ እየተሠራ መሆኑን መግለጻቸው አይዘነጋም። በ2013/14 የምርት ዓመት በበጋ መስኖ 600ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት 26 ሚሊዮን ኩንታል መመረቱን፤ በአጠቃላይ የበልግን ሳይጨምር በመኸር 110 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ተመርቷል።

ይህ ታሪካዊ እመርታ የሀገራችንን ገጽታ፣ ግብርናዊ ስሪትና የሥነ ልቡና ውቅር የሚቀይር ወሳኝ መታጠፊያ/ክሪቲካል ጃንክቸር/ ነው። ለሌሎችም ሁለንተናዊ ኢኮኖሚያዊ ብልጽግና መስፈንጠሪያ ሆኖ ስለሚያገለግል በቀላሉ የሚታይ ስኬት አይደለም። በአጠቃላይ ሀገራችን ለግብርናና አረንጓዴ ኢኮኖሚ የሰጠችው ትኩረት፤ በዓለማችን ላይ ከተከሰተው የአየር ጠባይ ለውጥ፤ የዓለም ሕዝብ ቁጥር በእጅጉ እያሻቀበ በመምጣቱ የግብርና ምርት ውጤቶች በእጅጉ እየተፈለጉ ካለበት ወቅት ጋር መገጣጠሙ ዓለማቀፍ አንድምታ እንዲኖረው አድርጓል ። ያለንበት ዘመንም ሆነ መጪው ጊዜ ለግብርና ምቹ ነው ። ለዚህ የሚበጅ የግብርና መሠረተ ልማት ግንባታ ላይ ትኩረት እንደተሰጠው ሁሉ፤ ይሄን የሚመጥን የግብይት ሥርዓት፣ ተጠያቂነትና የሕግ የበላይነት በንግዱ ዘርፍ ተግባራዊ ካልተደረገ ምርትና ምርታማነት የቱንም ያህል ቢጨምር ገበያውን ማረጋጋትና ሸማቹንም አምራቹንም ተጠቃሚ ማድረግ አይቻልም ።

በተደጋጋሚ በዚህ ዓምድ ላይ እንደምለው መጪው ዘመን ለግብርና ኢኮኖሚው ብሩህ እንደሆን እየተለፈፈ ይገኛል። አፍሪካም ሆነች ሀገራችን የሰፋፊ የእርሻ መሬቶች፣ የተፈጥሮ ሀብት፣ የሰፊ ገበያ፣ በመልማት ያለ የሰው ኃይል፣ …፤ እምቅ አቅም potential ያላቸው መሆናቸው አይን ማረፊያ አድርጓቸዋል። እ.አ.አ በ2050 የዓለም ሕዝብ ቁጥር 10 ቢሊዮን ይደርሳል ተብሎ ተተንብዮአል። የቻይናና የሕንድ ኢኮኖሚ እድገትን ተከትሎ የመሸመት አቅም መጎልበት ጋር ተያይዞ የሚያሻቅበው የምግብ ሸቀጦችን ፍላጎትን ለማርካት፤ በዓመት ከ100 ትሪሊዮን ዶላር በላይ የሚያገላብጠው ግብርና የዓለም ኢኮኖሚ መሪነትን በቅርብ ከኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ይረከባል ተብሎ ስለሚጠበቅ፤ ትኩረቱ ባልታረሰው የአፍሪካ ድንግል መሬት ላይ መሆኑ ዘመኑን ይዋጃል። ሀገራችን ለግብርናውና ለአረንጓዴ አሻራ የሰጠችው ትኩረት ትክክለኛና ስትራቴጂካዊ ውሳኔ ነው።

የዓለም ሕዝብ ቁጥር እድገት አሁን ከሚገኝበት ሰባት ነጥብ አምስት ቢሊዮን፤ በክፍለ ዘመኑ መጨረሻ 11 ቢሊዮን ይደርሳል ተብሎ መተንበዩ፤ በዓለም በተለይ በቻይና፣ በሕንድና በሌሎች ታዳጊ ሀገራት እየተመዘገበ ካለው ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ጋር የምግብ ፍላጎት እጅግ ጨምሯል። እድገቱን ተከትሎ የመግዛት አቅም ከፍ በማለቱ እና የመጣው የአመጋገብ ለውጥ ፍላጎቱን አንሮታል። ባለፉት 20 እና 30 ዓመታት በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ቻይናውያን፣ ሕንዳውያን፣ ብራዚላውያን፣ ኢንዶኔዣውያን፣ ማሌዣውያን፣ ወዘተረፈ ከድህነት ወደ መካከለኛ ገቢ ማደጋቸው በግብርና ውጤቶች ፍላጎት ላይ መሠረታዊ ለውጥ አምጥቷል።

በተቃራኒው የሚታረስ መሬትና የውሃ እጥረት እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ በአናቱ ተጨምሮ ከዓመት ዓመት ፍላጎቱን ማሟላት አዳጋች እያደረገው መጥቷል። የዓለም ሙቀት መጨመርና የደኖች መጨፍጨፍ፤ የአፈር መሸርሸርንና የመሬት መራቆት፣ በረሃማነት፣ ድርቅ፣ ሰደድ እሳት፣ ጎርፍ የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚውን እያሽመደመደው ነው። በዚህ የተነሳ ፍላጎቱንና አቅርቦቱን ማጣጣም ከጊዜ ወደ ጊዜ አዳጋች እየሆነ መጥቷል። እንደ ኮቪድ 19 ያለ የተፈጥሮ አደጋ ሲከሰት ደግሞ ችግሩ ክፉኛ ይባባሳል። የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት ቀደም ባለ ጊዜ ይፋ እንዳደረገው ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ 265 ሚሊዮን ሕዝብ ለከፋ የምግብ እህል እጥረት ተዳርጎ ነበር።

ከባድ ውሽንፍር፣ የጎርፍ መጥለቅለቅ፣ ድርቅ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ ዓይነት የተፈጥሮ አደጋዎች በተከሰቱ ቁጥር የምግብ እህል እጥረት ከፍ ሲልም ረሀብ ይከሰታል። በመላው ዓለም አንድ ቢሊዮን ሕዝብ በምግብ እጥረት ሳቢያ ለተለያዩ የጤና እክሎች ተዳርጓል። ወደ አገራችን ስንመጣ 47 በመቶ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የከፋ የምግብ እጥረት እንዳለበት መረጃዎች ያትታሉ። ከወረርሽኙና ከድርቅ ጋር ተያይዞ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ወገናችን ለምግብ እህል እጥረት መጋለጡን መንግሥት ይፋ አድርጓል። ግብርና ለሀገሪቱ ጥቅል ብሔራዊ ምርት ድርሻው 47 በመቶ ቢሆንም እድገቱ የሚጠበቀውን ያህል አይደለም።

ሀገራችን የወጣት፣ 85 በመቶ የሚሆነው ሕዝቧ በገጠር የሚኖር፣ ዓመቱን ሙሉ የሚፈስሱ ወንዞች፣ የሁለት ጊዜ የዝናብ ወቅት፣ የሚታረስ ሰፊ መሬት፣ ታታሪ ሕዝብ ያላት እና ቀደምት ከስድስት ሺህ ዓመታት የሚሻገር የእርሻና የግብርና ታሪክ ያላት ምድር ብትሆንም ራሷን እንኳ በቅጡ መመገብ አልቻለችም። በስንዴውና በዘይቱ ሲገርመን ሽንኩርትና ምስር ከውጭ እያስገባን ነው። በእኛው ዓባይ የለማ የግብጽ ብርቱካን በአለፍ ገደም ገበያው ላይ ብቅ እያለ ነው። ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ግን ከዚህ አዙሪት ለመውጣት በመንግሥት በኩል ፍላጎትና ቁርጠኝነትን እየተመለከትን ነው። ዛሬም ተረጂ፣ ዛሬም ስንዴና ዘይት ከውጭ አስመጪ መሆናችን ቁጭት የፈጠረ ለለውጥ ያነሳሳ ይመስላል። እዚህ ላይ 97 በመቶ የሚሆነው ዘይት ከውጭ የሚገባ መሆኑን ልብ ይሏል።

ቀድሞውኑም በኢኮኖሚያዊ አዋጭነትና በጥናት ባልተመሠረተ አግባብ ግብርናው የሚገባውን ያህል ድጋፍ ሳያገኝ ከፈረሱ ጋሪው እንዲሉ በግብታዊና በፖለቲካዊ ውሳኔ የዩኒቨርሲቲና የኢንዱስትሪ ፓርክ መዓት አግተልትለን ለምሩቃኑ ሥራ ለፋብሪካው ጥሬ ዕቃ ማቅረብ አልቻልንም። ለዚች አገር ነፍስ መዝሪያዋም መሞቻዋም ግብርና ነው። ግብርና ላይ ከተሳካልን ሌሎችን ዘርፎች ይዞ መነሳትና መውጣት ይቻላል። ለቀደሙት 27 ዓመታት ከፕሮፖጋንዳ ባለፍ የሀገራችንን ሥነ ምሕዳር ታሳቢ ያላደረገ የዘመቻ ሥራ መሠራቱ ዛሬ ላይ ጥሎናል። ቆም ብለን ትንፋሽ ስበን የመጣንበትን መንገድ ገምግመን በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ የሚስተዋለውን መዋቅራዊና ተቋማዊ ችግር ቀርፈን ትኩረታችን ግብርናው ላይ ሊሆን ይገባል።

የሕልውናችን መሠረት የሆነውን አየር ንብረታችን እንዲያገግም በአምስት ዓመታት ውስጥ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ችግኝ ለመትከል ግብ ጥሎ ካለፉት አምስት ዓመታት ጀምሮ ወደ ተግባር መገባቱ የኑሮአችንና የኢኮኖሚያችን የጀርባ አጥንት ለሆነው ግብርና መልካም ዜና ነው። በሚቀጥሉት አምስትና አስር ዓመታትም የሀገራችንን አየር ንብረትና ሥነ ምሕዳር /ኢኮሎ/ ፍጹም ይቀይረዋል። ይህ በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ላይ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት መስፈንጠሪያ ነው። ይህ በሒደት እውን እስኪሆን የለውጥ ኃይሉ ስንዴን ከውጭ ማስገባትን ለማስቀረት፣ ግብርናውን ሜካናይዝድ ለማድረግ፣ መሬት ጦም እንዳያድር፣ የኩታ ገጠም አሠራርን ለማስፋፋት የሚያደርገው ጥረት ይበል የሚያሰኝ ሆኖ ወጥ በሆነና ስፋት ባለው አግባብ እንደየሥነ ምሕዳሩ በመላ ሀገሪቱ ተግባራዊ ማድረግ ላይ ግን ይበልጥ ሊሠራ ይገባል።

እንደ አገር ያለን ሀብት የሚታረስ መሬት፣ ውሃና የሰው ኃይል ነውና ለግብርናው ቅድሚያ ሰጥተን ልንረባረብ ይገባል። ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረግ ሽግግር ያለ ግብርናው ጽኑ መሠረት እውን ሊሆን አይችልምና። ስለሆነም ያለንን ሀብት ሁሉ አቀናጅተን ግብርናው ላይ ልንረባረብ ይገባል። የአረንጓዴ አብዮት በማቀጣጠል አንገታችንን ሲያስደፋን ሲያሸማቅቀን ከኖረው ረሀብ፣ ቸነፈርና ድህነት ይህን ተከትሎ ከማይለየን ተረጂነት መላቀቅ አለብን። አብዮትም ብርቃችን አይደለም። አንድ ሁለት ጊዜ አብዮት ሁሉን ነገራችን ነቅሎ መቀመቅ አውርዶናልና። ለዚህ ነው ቃሉን ስንሰማ እንደ ኮሶ መድኃኒት የሚያንገሸግሸን። አረንጓዴ አብዮት ግን ረሀብን፣ ችጋርን፣ ቸነፈርን፣ ተመፅዋችነትን ከስሩ መንግሎ የሚጥል ዶዘር ነው።

ከቀደሙት ሁለት የደም፣ የጥፋት ወይም የቀይ አብዮቶች አንዱ አረንጓዴ አብዮት ቢሆን ኑሮ የሀገራችን መለያ ከሆነው ረሀብ እስከ ወዲያኛው በተለያየን። ዛሬ ለምንገኝበት የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት ባልተዳረግን። አሁንም በሕዝብና በሀገር ኢኮኖሚ እንዲሁም ገፅታ ላይ ስር ነቀል ለውጥ የሚያመጣውን የአረንጓዴ አብዮት ለማካሄድ አልረፈደም። እንግዲህ የ«አረንጓዴው አብዮት» ሥርወ–ሐረግ ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንቃኝ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለው የአሜሪካ የዓለምአቀፍ ትብብር ድርጅት / ዩኤስኤአይዲ/ አስተዳዳሪ የነበሩት ዊሊያም ጋውድ እኤአ በ1968 የአብዮቱን አረንጓዴ ችቦ በለኮሱበት ሥነ ሥርዓት ፤ «… ይህ አዲስ አብዮት ነው። የሶቪየት ኅብረቱ ቀይ አብዮት አልያም የኢራን የሻህ ነጭ አብዮት አይደለም። አረንጓዴ አብዮት ብየዋለሁ። …»

የአረንጓዴ አብዮት የ2ኛውን የዓለም ጦርነት ተከትሎ የተከሰተውን የምግብ እና የአግሮ ኢንዱስትሪ ግብዓት እጥረት ለማሟላት በ1950ዎቹና 60ዎቹ ተለኩሶ የተቀጣጠለ አብዮት ነው። ምርጥ ዘርን፣ ማዳበሪያን፣ ፀረተባይ ኬሚካልን፣ አስተማማኝ የውሃ አቅርቦትን በማረጋገጥ በተለይ የስንዴንና የሩዝ ሰብልን ምርትን በእጅጉ ማሳደግ ያስቻለ አረንጓዴ አብዮት ነው። አረንጓዴ አብዮት በብራዚል፣ በሕንድ፣ በፊሊፒንስ፣ ወዘተረፈ ፈንድቶ ጎተራውን ሙሉ አድርጎታል። እኛም የሀገራችንን ሥነ ምሕዳርና ብዝኃ ሕይወት ከግምት ያስገባ አረንጓዴ አብዮት ያስፈልገናል። ረሀብን፣ ቸነፈርንና ችጋርን በቃ ! ልንለው ይገባል።

ሁላችንም ከፖለቲካ ተንታኝነትና ከሴራ ፖለቲካ አራጋቢነት ወጥተን፤ ፖለቲካውን ለፖለቲከኞች ትተን፤ አረንጓዴ አብዮትን እንቀላቀል። እናቀጣጥል። ግብርናውን እናግዝ፤ ግብርናውን እናግዝ፤ በጓሮአችን አትክልት እናልማ፤ ችግኝ እንትከል፤ የተከልናቸውን ችግኞች እንንከባከብ። የተገኘውን ውጤት ወደኋላ እንዳይመልሰን ተግተን በኃላፊነት መንፈስ እንንቀሳቀስ። በዜጎቿ ብርቱ ጥረት፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከተረጅነትና ከተመጽዋችነት ተላቃ በምግብ እህል ራሷን ችላ ስንዴ ለውጭ ገበያ ታቀርባለች ! አሜን ።

ሻሎም ! አሜን ።

አዲስ ዘመን  የካቲት 3 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You