ታዳጊ ቡድኑ ነገ ደቡብ አፍሪካ ላይ ጨዋታውን ያደርጋል

በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት መጨረሻ በዶሚኒካን ሪፐብሊክ አዘጋጅነት የሴቶች ከ17 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ይካሄዳል፡፡ በዚህ ውድድር ላይ ከስድስቱ አህጉራት የተወጣጡ 16 ቡድኖች የሚካፈሉ ሲሆን፤ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በሦስት ሃገራት ይወከላል፡፡ ኮንፌዴሬሽኑን ለመወከልም 25 ሃገራት ብሔራዊ ቡድኖቻቸውን በማጣሪያ ጨዋታው በማሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ቡድኖች መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያም የሁለተኛ ዙር የመልስ ማጣሪያ ጨዋታዋን ከደቡብ አፍሪካ ጋር ነገ በፕሪቶሪያ ታከናውናለች፡፡

ቡድኑ የሁለተኛ ዙር የማጣሪያ ጨዋታውን አዲስ አበባ ላይ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ከደቡብ አፍሪካ አቻው ጋር በማድረግ በአሸናፊነት ማጠናቀቁ የሚታወስ ነው፡፡ በአሠልጣኝ ራውዳ አሊ እየተመራ ከታኅሣሥ ወር መጨረሻ አንስቶ በአዲስ አበባ ስታዲየም እና አበበ ቢቂላ ስታዲየም ዝግጅቱን ሲያደርግ የቆየው ቡድኑ ለ26 ቀናት በክፍል ውስጥ እና በመስክ የታገዘ ልምምድ በማድረግ ነበር የመጀመሪያውን ጨዋታውን ያከናወነው፡፡ ቡድኑ በመጀመሪያ 35 ተጫዋቾችን በመጥራት ለቀናት በተደረገው ልምምድ 25 ተጫዋቾችን በማስቀረት ቀጥሎም በልምምድ ሂደት አምስት ተጫዋቾችን በመቀነስ 23ቱን መያዝ ውድድሩን ጀምሯል፡፡

ከደቡብ አፍሪካ ጋር ከነበረው ጨዋታ አስቀድሞም ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎችን ከመቻል እና ከልደታ ክፍለ ከተማ ጋር ማድረግ ችሏል፡፡ ከቀናት በፊት አዲስ አበባ ላይ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በተከናወነው ጨዋታም ኢትዮጵያ 3 ለምንም በሆነ ፍጹም የበላይነት ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው፡፡ ቡድኑ በደጋፊው ፊት ያስመዘገበው ይህ ውጤት ቀጣዩን ዙር ለመቀላቀል መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥርለት ይታመናል፡፡ ነገ ፕሪቶሪያ ላይ ለሚያደርገው የመልስ ጨዋታ ዝግጅቱን ሲያደርግ የቆየው ቡድኑ ትናንት ረፋድ ላይ ጉዞውን የጀመረ ሲሆን፤ ከ5 ሰዓት በረራ በኋላ ውድድሩን ከሚያደርግበት ስፍራ ደርሷል፡፡

አራት ዙሮች ያለው የማጣሪያ ውድድሩ በደርሶ መልስ ጨዋታ አሸናፊ በመሆን እስከመጨረሻው የሚጓዙ ሦስቱን ቡድኖች ብቻ በዓለም ዋንጫው ያሳትፋል፡፡ ከእነዚህ ቡድኖች መካከል አንዱ ለመሆን እየተፎካከረ የሚገኘው ቡድኑ የመጀመሪያውን ጨዋታ ባደረገ በማግስቱ ነበር ወደ ዝግጅቱ የተመለሰው፡፡ አጠቃላይ የቡድኑን ቆይታ በተመለከተ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስተያየት የሰጠችው ዋና አሰልጣኟ ራውዳ አሊ፤ ቡድኗ እሁድ ዕለት የመጀመሪያ ጨዋታውን ካደረገ በኋላ ለመልሱ ጨዋታ የሚሆነውን ዝግጅት በማግስቱ ሰኞ የጀመረ መሆኑን ጠቁማለች፡፡

ቡድኑ በሜዳው በነበረው ጨዋታ የታዩ ክፍቶችን መሠረት ያደረገ ልምምድ በመሥራት ዝግጁ በመሆንም ወደ ደቡብ አፍሪካ አቅንቷል፡፡ ቀደም ሲል ከተመረጡ 23 ተጨዋቾች መካከል ቤዛዊት ንጉሤ ለመጀመሪያ ጨዋታ በፓስፖርት ምክንያት ያልተካተተች ቢሆንም የፖስፖርቱ ጉዳይ ተጠናቆ ከቡድኑ ጋር መቀላቀል ችላለች፡፡ ከዚህ ባለፈ ሁሉም የቡድን አባላት በጥሩ ጤንነት፣ መነቃቃትና ሞራል ላይ የሚገኙ በመሆኑ 23ቱም ተጫዋቾች ለመልሱ ጨዋታ ወደ ስፍራው እንደተጓዙም አብራርታለች፡፡

በደርሶ መልሱ ጨዋታ ኢትዮጵያ አሸናፊ የምትሆን ከሆነ በሦስተኛው ዙር ጨዋታ ከጎረቤት ሃገር ኬንያ ጋር የምትገናኝ ይሆናል፡፡ በማጣሪያው ምድብ ሁለት ከዴሞክራቲክ ኮንጎ ጋር የተደለደለው የኬንያ ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን በጨዋታው እንደማይሳተፍ ባሳወቀው ተጋጣሚው ምክንያት በቀጥታ ወደቀጣዩ ዙር ማለፉን ያረጋገጠው አስቀድሞ ነው፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት ህንድ ላይ በተደረገው የዓለም ዋንጫ፤ እንዲሁም ከዚያ ቀደም በ2018 ኡራጓይ ላይ ቻምፒዮን በመሆን ዋንጫውን ያነሳችው ስፔን ናት፡፡ በዚህ የዕድሜ እርከን ጠንካራ ቡድን መመስረት የቻለችው ስፔን ውድድሩ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ጠንካራ ተፎካካሪ መሆኗን እስከ ግማሽ ፍጻሜ በመድረስ አስመስክራለች፡፡ በዚህ ውድድር አፍሪካን ከወከሉ ሃገራት ደግሞ ረጅም ርቀት መጓዝ የቻሉት ጋና እና ናይጄሪያ ናቸው፡፡ የጋና ብሔራዊ ቡድን ትልቁ ውጤቱ እአአ በ2012 አዘርባጃን ላይ በተካሄደው ውድድር ሦስተኛ በመሆን ያጠናቀቀበት ነው፡፡ በተመሳሳይ በሴቶች እግር ኳስ ስመጥር የሆነው የናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድንም እአአ 2022 ላይ የዋንጫ ግስጋሴው በግማሽ ፍጻሜው ቢገታም ለደረጃ በተደረገው ጨዋታ የነሐስ ሜዳሊያ ማጥለቅ ችሎ ነበር፡፡

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን  የካቲት 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You