ሃይማኖት የችግር መፍቻ እንጂ ምንጭ እንዳልሆነ አስተምሮዎቻችን በተጨባጭ ሊያሳዩን ይገባል

 ሃይማኖትና ምግባር ተጣጥመው መሄድ ያለባቸው የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው የሚባለው ሃይማኖተኞች የሃይማኖታቸውን አስተምህሮ በሥራ የመተርጎም የውዴታ ግዴታ እንዳለባቸው ስለሚታመን ነው። ከዚህ አንጻር በተለይም የሃይማኖት አባቶች ለምዕመናን የሚሰብኩትን እና የሚያስተምሩትን ኖረው በማሳየት ግንባር ቀደም ምሳሌ መሆን ይጠበቅባቸዋል።

ከዘጠና አምስት በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃይማኖተኛ እንደሆነ ይነገራል። የየትኛውም ሃይማኖት ተከታይ ከፈጣሪው ጋር ተቆራኝቶ መኖርን የሚመርጠው ወይም በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ የሚታቀፈው በምድር ላይ ሲኖር ጸጋ እና በረከትን ፤ ሲሞት ጽድቅን አገኛለሁ ብሎ በማሰብ ነው።

ሃይማኖቶች በዋና ዋና አስተምህሮዎቻቸው ቢለያዩም በርካታ የጋራ እሴቶች አሏቸው። ፍቅርን፣ ሰላምን፣ እርቅን፣ መተዛዘንን፣ ኅብረትን፣ አንድነትን ይሰብካሉ። አትግደል፣ አትስረቅ፣ አታመንዝር ፣ እናትና አባትህን አክብር፣ በሀሰት አትመስክር፣ ባለንጀራህን እንደራስህ ወደድ … የሚሉት በሁሉም ሃይማኖቶች ውስጥ ትልቅ ዋጋ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው።

ከሃይማኖታዊ አስተምህሮዎች ወጣ ብለን ስንመለከት ደግሞ የሰው ልጅ በተፈጥሮም የተሰጡት ሰብዓዊ ባህሪዎች አሉት። ከእነዚህም እንደ መራራት ፣ ማዘን ፣ መሳቅ፣ ማስተዋል፣ ማመዛዘን የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል። ሰው ሃይማኖት ይኑረውም አይኑረውም መልካም ነገርን እንዲያስብና እንዲሠራ የሚያደርጉት እነዚህ የተሰጡት ተፈጥሯዊ ጸጋዎቹ ናቸው።

ሰው ጥሩ ሥራ ሲሠራ ህሊናው ይረካል፤ መጥፎ ሥራ ሲሠራ ደግሞ የገዛ ሕሊናው ይወቅሰዋል። መልካምነት የህሊና ምግብ በመሆኑ ሰው ሁሌም ለራሱ ሲል የሚተገብረው ጉዳይ ነው፡፡እነዚህ ተፈጥሯዊ፣ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ እሴቶቻችን ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ለዘመናት ሰምና ወርቅ ሆነው እንዲኖሩ ያስቻሉ ሀብቶቻችን ናቸው።

ከሰማንያ በላይ ብሔር ብሔረሰቦች እና ከመቶ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሕዝቦች ማህበራዊ ትስስራቸውን አጠናክረው በሀገራቸው ጉዳይ እንደ አንድ ሰው እያሰቡ እዚህ ድረስ እንዲዘልቁም አድርገዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃይማኖተኛ እና ፈጣሪውን የሚፈራ ነው ሲባል እንደው ዝም ብሎ ያገኘው ሳይሆን በሃይማኖት አባቶች ትጋትና ብርታት ነው። ለዚህም የሃይማኖት አባቶችን ማመስገን ያስፈልጋል።

ከጥንት ጀምሮ ኢትዮጵያ ችግር ሲገጥማትና ማህበራዊ ቀውሶች ሲፈጠሩ ሕዝቦቿ አንድ ላይ ቆመው ችግሮችን የማስወገድ ልምድ ያላቸው ናቸው። የሃይማኖት አባቶችም ቢሆኑ ሕዝቦችን በማረጋጋት፣ በማስታረቅ፣ በመጸለይ፣ በማጽናናትና አይዟችሁ በማለት ከጥንት ጀምሮ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን ሲወጡ ቆይተዋል ።

አሁን አሁን ግን ከዚህ ያፈነገጡ ተግባራትን በአደባባይ ማየትና መስማት እየተለመደ መጥቷል። ሀገርን ከገባችበት የሰላም ችግር ለመታደግ ሰፊ ሥራዎች እየተሰሩ ባለበት ሁኔታ ፤ ከሃይማኖታዊ አስተምሮዎቻችን ወጣ ያሉ ሕዝብን ለግጭት የሚገፋፉ የሃይማኖት አባቶችንና ሃይማኖተኞችን እያስተዋልን ነው።

የሃይማኖትን ጭምብል ለብሰው ዘረኝነትን የሚሰብኩና የራሳቸውን የፖለቲካ አቋም የሚያራምዱ፤ ተሰሚነታቸውን ተጠቅመው ጠብ አጫሪ፣ ቀስቃሽና አፍራሽ መልዕክቶችን የሚያስተላልፉ፤ እነርሱ ከሃይማኖታዊ አስተምህሮዎች ውጪ መጓዛቸው ሳያንስ ሌሎችም ቀናውን መንገድ ትተው የእነርሱን የጥፋት መንገድ እንዲከተሉ የሚጎተጉቱ የሃይማኖት አባቶችን እያየን ነው።

ሕዝብ እንደጠላት እንዲተያይ፤ አንዱ ሌላውን እንዲያሳድድ፣ እንዲያጠፋ፣ በሕዝቦች መካከል መተማመን እንዳይኖር የሚሠሩ ፣ መንግሥትንና ሕዝብን ለማቃቃር የሚደክሙ ሃማኖተኞችንና የሃይማኖት አባቶችን እዚህም እዚያም እያየን ታዝበናቸዋል፤ አፍረንባቸዋልም።

በእርግጥ ሃይማኖትና ምግባር አብረው ካልሄዱ እንዲህ አይነት አስገራሚና አሳፋሪ ጉዳዮች መፈጠራቸው የማይቀር ነው። በሰላሙ ጊዜ ሲያስተምሩን ‹‹እግዚአብሔር ዘረኝነትን አይወድም፤ ግራህን ሲመቱህ ቀኝህን ስጥ፤ አትግደል ፣ አትራገም፤ በቀል የእግዚአብሔር ነው አትበል፤” እንዳላሉ ሁሉ ትንሽ ኮሽ ሲል በየዘር ከረጢታቸው ውስጥ ገብተው ያን ሁሉ ያስተማሩትን ሃይማኖታዊ ትምህርት በተቃራኒ እንተርጉም የሚሉ ሃይማኖተኞችን አይተን ኩምሽሽ ብለናል። የሃይማኖትን ጭንብል በለበሱ ብሔርተኛ ሃይማኖተኞችና የሃይማኖት አባቶች ምክንያት ኢትዮጵያ የቱን ያህል እየተፈተነች እንደሆነም እያየን ነው።

የበጎች እረኛ የሆኑት የሃይማኖት አባቶች ከሚሰብኩት ሃይማኖታዊ አስተምህሮ አፈንግጠው ከክፋት ተዋናዮች ጎን መሰለፋቸው ሊያስደነግጠን ይችል ይሆናል። ነገር ግን የሃይማኖት አባቶችም ቢሆኑ እንደኛው ሰው ናቸውና አንዳንድ ጊዜ ስሜታዊ ሲሆኑ የአፍ ወለምታ ሊያጋጥማቸው ይችላል። ማለትም የመድረክ ሞቅታን ተከትለው ፈር የለቀቀ ንግግር ሊያደርጉ ይችላሉ ማለቴ ነው፡፡

በዚህ አንኮንናቸውም። ለምን ቢባሉ ለምሳሌ በክርስትና እምነት አስተምህሮ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመረጣቸው አስራ ሁለቱ ሐዋርያት መካከል እንኳ በፈተና የወደቁ ነበሩና ነው። የይሁዳ ፍጹም የሆነ ክህደት ለዚህ ጽሑፍ ጥሩ ምሳሌ ስለማይሆን ለጊዜው እንተወው።

ሐዋርያው ጴጥሮስ በአንድ ሌሊት ኢየሱስ ክርስቶስን ሶስት ጊዜ ክዶት እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳል። ኢየሱስ ክርስቶስ ጴጥሮስ እንደሚክደው ያውቃል፤ አስቀድሞም ለጴጥሮስ ነግሮታል፤ ነገር ግን እንደሚክደው እያወቀም ቢሆን መርጦታል፤ ጴጥሮስ በዚያ ቅጽበት የፈጸመው ስህተት አጠቃላይ የእርሱን ሰብዕና እና ማንነት የሚገልጽ አለመሆኑን ኢየሱስ ያውቃል። ለዚያም ይመስላል ጴጥሮስ በፈጸመው ስህተት ውሎ ሳያድር ጸጸቱን በእንባ የገለጸው። ያ ስህተቱ እና ጸጸቱ ደግሞ ለቀጣይ ሕይወቱና ሃይማኖታዊ ተልዕኮው አቅም ፈጥሮለታል።

ሰው የክብሩ ወይም የእውቀት ደረጃው ምንም ይሁን ምን ስህተት ሊሠራ የሚችልበት አጋጣሚ ይኖራል። ዋናው ጉዳይ ግን ከስህተት መታረም ነው። ይህ ሲሆን የበጎ ነገር ምሳሌ መሆን ይቻላል። ከትዝብት መዳን እና ተሰሚነትንም ማግኘት ይቻላል። ከዚያ ውጪ ግን በሥራ ወይም በምግባር የማይገልጹትን ሃይማኖትና የሃይማኖት አባትነት ስም ይዞ ሕዝብን ለክፉ ድርጊት ማነሳሳት ኢ-ሃይማኖታዊም ብቻ ሳይሆን ኢ-ሰብዓዊ እና ኢ-ሕገ መንግሥታዊም ጭምር ነው።

ሃማኖተኞች የሚጠበቅብን ስለሀገር ሰላምና ስለህዝብ ደህንነት መጸለይ እንጂ ዘው ብለን በማያገባንና ባልተጠራንበት ፖለቲካ ውስጥ ገብተን ፤የሀገርን ህልውና ስጋት ውስጥ ፤የሕዝቦችን አብሮ የመኖር እሴት አደጋ ውስጥ የሚከት ፤በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለውን ግንኙነት ፈተና ውስጥ የሚከት ተግባር ውስጥ መገኘት አይኖርብንም። ከማይገቡ ንግግሮች መቆጠብ ይጠበቅብናል። ሃይማኖት የችግሮቻችን መፍቻ ቁልፍ እንጂ ምንጭ እንዳልሆነ እና እንደማይሆን አስተምሮዎቻችን በተጨባጭ ሊያሳዩን ይገባል።

ቃለአብ ኢያሱ

አዲስ ዘመን  የካቲት 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You