ለትውልድ የሚተላለፍ ተምሳሌታዊ ጽናት!

 ሀገራዊ ለውጥ የተሻለ ነገር ለመፍጠር የሚደረግ ማኅበረሰባዊ ክስተት ነው፤ በአግባቡ መመራት ካልተቻለ ይዞት ሊመጣው የሚችለው አደጋ /ምስቅልቅል ከፍያለ ነው። ለዚህም ደግሞ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ነጋሪ የሚያስፈልገን አይደለም። እንደ ሀገር በተለያዩ ወቅቶች ሞክረናቸው ያልተሳኩ ለውጦች እንደሀገር ያስከፈሉን ዋጋ ምን እንደሚመስል ለሁላችንም የተሰወረ አይደለም።

አብዛኞቹ ፣ በተለይም በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ የተካሄዱ የለውጥ ታሪኮቻችን በለውጥ ፈላጊው ኃይል መካከል ሳይቀር መግባባት / መደማመጥ ሳይቻል ቀርቶ ተስፋ የተጣለባቸውን ያህል ውጤታማ ሳይሆኑ ቀርተዋል። በብዙ ተቃርኖዎች ተፈትነው መሻገር የሚያስችል አቅም በማጣታቸው ሀገርና ሕዝብን ብዙ ዋጋ እንዲከፍሉ አድርገውታል።

ከዚህም ባለፈ ለውጥ በባህሪው ፤ የተሻለ አስተሳሰብ የሚወልደው፤ተሸክሞ የሚያሻግረው መሆኑ፤ ይህም ተጨባጭ በሆነው ሀገራዊ የፖለቲካ ንቅናቄ ባለመታገዙ፤ ዛሬም ትውልዶች የሚፈልጓቸው የለውጥ አስተሳሰቦች ተግባራዊ እንዳይሆኑ ተግዳሮት ሆነዋል። ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍሉም አድርጓቸዋል።

በኃይል እና ኃይል በሚፈጥረው የአሸናፊ፣ ተሸናፊ ትርክት ላይ መሰረቱን አድርጎ ዘመናት ያስቆጠረው የሀገሪቱ የፖለቲካ ባህል ፤ የሕዝባችንን የለውጥ መሻት፤ትርጉም ያለው ፍሬ እንዳያፈራ በማድረግ ፤በየዘመኑ ትውልዶች ከተስፋዎቻቸው ጋር የሚጋጩበትን ሰፊ የታሪክ ገጽ ፈጥሯል።

ይህ ታሪካዊ እውነታ በባለፉት አምስት የለውጥ ዓመታት ላይም ጥላ እንዳጠላ የሚዘነጋ አይደለም። መላው ሕዝባችን በብዙ ተስፋ እና መስዋእትነት የጀመረው ለውጥ በብዙ የውስጥና የውጪ ፈተናዎች ውስጥ ለማለፍ ተገድዷል። በዚህም ሕዝቡና የለውጥ ኃይሉ ብዙ ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍሉ ሆኗል።

በርግጥ በብዙ ተቃርኖዎች የሚታጀቡ የለውጥ ምዕራፎች ለስኬታማ ፍጻሜያቸው ከሁሉም በላይ የለውጥ ኃይሉን አቅም የሚጠይቁ ናቸው። የለውጡን ዘላቂ ስኬት ማየት፤ ተገማችና ተገማች ያልሆኑ ችግሮችን ተገንዝቦ መፍታት የሚያስችል ፤በለውጥ ኃይል ማንነት የሚለካ የስብእና ዝግጁነት የሚጠይቅ ነው።

ከስልጣን /ከመቀመጫ ባለፈ ለውጥ አማጭ የሆኑ ሀገራዊ ስብራቶችን አውቆና ተረድቶ ማከም ፤ለውጥ በራሱ የአዲስ ታሪክ ምዕራፍ ጅማሬ መሆኑን ተገንዝቦ የራስን የታሪክ ገጽ በደመቀ ቀለም ጽፎ ትውልዳዊ ኃላፊነትን የመወጣት የውስጥ መሻት ፤ለዚህ የሚሆን የማይሰበር ጠንካራ ማንነት የሚፈልግ ነው።

በጅማሬ ውስጥ ፍጻሜን አሻግሮ ማየት የሚያስችል ፤ በእያንዳንዱ የዕለት ተዕለት የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ የራስን ታሪክ ሠሪነት እያጸኑ ፤ በሚሠራ ታሪክ ፤ታሪክ ሠሪ ማንነት ያለው ትውልድ እየፈጠሩ ፤ የሀገር እና የሕዝብን የተሻሉ ነገዎች በጠንካራ መሠረት ላይ ማዋቀርን የሚጠይቅ ነው።

ታሪክ በመሥራት እና ታሪክ የሚሠራ ትውልድ በመፍጠር ከሚገኝ ደስታ ዛሬዎችን የበለጠ ትርጉም እንዲኖራቸው ማድረግ ፤ ለዚህ የሚሆን የተከፈተ ልብ፣ አዕምሮና ዓይን ባለቤት መሆን፤ ለውጥን ከሚመራ ኃይል የሚጠበቅ ነው። የለውጡ ቀጣይነትም ማስተማመኛም ይኸው ነው።

ባለፉት አምስት የለውጥ ዓመታትም ለውጡ ያስገኛቸው ተስፋዎች ፤ብዙ የለውጥ ኃይሎችን መፍጠርና በጽናት ማስቆም አስችለዋል። እጅግ ብዛት ያላቸው የለውጥ ኃይሎች ፤ መራራ በሆነ የለውጥ ተሞክሮዎች ውስጥ ለማለፍ ቢገደዱም በለውጡ በነበራቸው የጸና እምነት በጥንካሬያቸው በመዝለቅ ከፈተናዎች በላይ መሆናቸውን በተጨባጭ ማሳየት ችለዋል።

ሀገርና ሕዝብ አስቸጋሪ በሚባል የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ በተገኙባቸው ወቅቶች ፤ለውጡ ይዟቸው በመጣቸው ተስፋዎች አቅም እየገዙ፤ፈተናዎቹ የሚጠይቋቸው መስዋዕትነቶችን ሳያቅማሙ በመክፈል ፤ ሀገርና ሕዝብን ፈተናዎቹ ከፈጠሯቸው ክፉ ቀናት ማሻገር ችለዋል።

ከዚህ አንጻር ትናንት ከፍ ላለ ኃላፊነት ታጭተው ፤ወደ ስልጣን የመጡ የለውጥ ኃይል አባላት ፤ አሁንም እንደ ትናንቱ ለውጡ በደረሰበት ምዕራፍ ለሚጠይቀው መስዋዕትነት ራሳቸውን ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል።አዲሱ የለውጥ መንገድ ይዞት ከመጣው አዲስ የፖለቲካ እሳቤ አኳያ ለስኬታማነቱ የሚፈልገውን አርቆ አሳቢነት ፤ትዕግስትና ሆደ ሰፊነት ዋነኛ የትግል ስትራቴጂ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

በክብር የተሰናበቱ የለውጥ ኃይሉ አባላትም ፤በለውጡ ውስጥ ያላቸው የደመቀ ታሪክ ፤ ለውጡ ይዞት ከመጣው አዲስ ሀገራዊ ትርክት አኳያ ፤ በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ልብ ውስጥ የሚኖረው ስፍራ የከበረ ነው። ፈተናዎችን የተሻገሩበት ጽናትም፤ ተምሳሌታዊነቱ ትውልድ ተሻጋሪ ነው!

አዲስ ዘመን  የካቲት 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You