የዲፕሎማሲ ሳምንቱን ለኅብረቱ ጉባኤ ተሳታፊዎች

 ኢትዮጵያ በቅርቡ በመዲናዋ አዲስ አበባ ለሚካሄደው 37ኛው የአፍረካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ዝግጅት እያደረገች ትገኛለች፡፡ ሀገሪቱ በኅብረቱ አባልነቷ ማድረግ የሚጠበቅባት ዝግጅት እንዳለ ሆኖ ከፍተኛ ኃላፊነትን የሚጠይቀው የጉባኤው አስተናጋጅነት ሥራ አለባት፡፡ እነዚህ ዝግጅቶች የኅብረቱ የመሪዎች ጉባኤ በየዓመቱ በሀገሪቱ ሲካሄድ የምታደርጋቸው ናቸው፡፡

የኅብረቱ መቀመጫ እንደመሆኗ የጉባኤው አስተናጋጅ ሀገር ናት፡፡ ለእዚህም በሰላምና ጸጥታ፣ በመስተንግዶና በመሳሰሉት ላይ በከፍተኛ ኃላፊነት ትንቀሳቀሳለች፡፡ ሀገሪቱ ለበርካታ ዓመታት ይህን ጉባኤ በማስተናገድ እነዚህን ኃላፊነቶቿን በሚገባ በመወጣት ገጽታዋን እንደገነባች ሁሉ ዘንድሮም ይህንኑ ኃላፊነቷን በብቃት ለመወጣት መሥራቱን ተያይዛዋለች፡፡ ለዚህም የተለያዩ ግብረ ኃይሎች ተቋቁመው ወደ ሥራ ገብተዋል።

ሀገሪቱ ይህ ጉባኤ በስኬት እንዲጠናቀቅ ከምታደርገው ዝግጅት በተጨማሪ መድረኩን እንደ አንድ የኅብረቱ አንጋፋና ንቁ ተሳትፎ የሚያደርግ አባል ሀገር ትጠቀምበታለች፡፡ ለኅብረቱ እቅዶች፣ ራእዮችና አጀንዳዎች መሳካት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥታ እንደምትሰራ ሁሉ ለጉባኤው አላማዎች መሳካትም ከተለመደውም በላይ ትሰራለች፡፡

ጉባኤው ገጽታዋን የመገንቢያ ሁነኛ መሳሪያ አርጋዋለች፡፡ በዚህም በጸጥታ፣ በልማትና በመሳሰሉት የደረሰችባቸውን ከፍታዎች ታሳይበታለች፡፡ የጉባኤው ተሳታፊዎች ሀገሪቱን የሀገራቸው ያህል አድርገው እንዲቆዩባት አድርጋ በማስተናገድ ትታወቃለች፡፡ በጸጥታና ደህንነት ላይ በትኩረት በመሥራት ያለምንም ኮሽታ ጉባኤው እንዲካሄድ ስታደርግ እንደኖረች ሁሉ ዘንድሮም ይህንኑ ትቀጥልበታለች፡፡

የዘንድሮ የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ በዚህ ሁሉ ላይ የሚጨምረው ሁነትም አላት፡፡ ይህ ሁነት ሀገሪቱ በዲፕሎማሲው መስክ የተጓዘችበትን ርቀት የሚያስቃኘው የዲፕሎማሲ ሳምንት ኢግዚቢሽን ነው። ይህ በሳይንስ ሙዚየም እየተካሄደ ያለና ሳምንታትን የዘለቀ ኢግዚቢሽን የኅብረቱ ጉባኤ ታዳሚዎች በሙሉ ሊመለከቱትና ተሞክሮ ሊቀስሙበት የሚገባ ታላቅ መድረከ ነው፡፡ ሀገሪቱ የኅብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ተሳታፊዎች ይህን ታላቅ መድረክ እንዲጎበኙት ለማድረግ ዝግጅት አድርጋለች፡፡ ለእዚህም ሲባል ለዜጋ የነበረውን ይህን መድረክ የመድረኩ አዘጋጅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም አድርጎታል።

ይህ ‹‹ዲፕሎማሲያችን ለብሔራዊ ጥቅማችን፤ ከአፍሪካ መዲና እስከ ዓለም መድረክ›› በሚል መርህ በዲፕሎማሲ ማእከሏ አዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ የሚገኘው የዲፕሎማሲ ሳምንት፣ በአያሌ ኢትዮጵያውያንና ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ በሆነ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት እየተገበኘ ይገኛል። ይህን መድረክ በህብረቱ መሪዎች ጉባኤና ከዚሁ ጎን ለጎን በሚካሄዱ የተለያዩ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ተቋማት ድርጅቶች በሚካሄዱ ስብሰባዎች የሚሳተፉ አካላት እንዲጎበኝ ለማድረግ መታቀዱ ሀገሪቱ በዲፕሎማሲው መድረክ ያላትን ከፍታ በሚገባ እንድታሳይ ያስችላታል፤ ገጽታዋን የበለጠ እንድትገነባም ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል።

ሀገሪቱ የአፍሪካ ኅብረትና እንደ ተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ያሉ የበርካታ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ተቋማት መቀመጫ እንደመሆኗ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የዲፕሎማሲ ሥራዎች ይካሄዱባታል፡፡ ይህ ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ ተግባር ሀገሪቱን በተለይ መዲናዋን አዲስ አበባን የዲፕሎማሲ ማእከል አድርጓታል፡፡ የዲፕሎማሲ ሳምንቱ ይህን የአፍሪካና የተቀረው ዓለም የዲፕሎማሲ ማእከልነቷን ይመጥናል፤ ይህን መድረክ ማስጎብኘቷ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ባላት ጥንካሬ ላይ ሌላ ጥንካሬ ይደርብላታል፡፡

እንደሚታወቀው፤ ሀገሪቱ በውድ ልጆቿ መስዋእትነት በዓድዋ ለቅኝ ግዥዎች አንበረከክም ብለው በከፈሉት መስዋእትነት የተቀዳጀችው ድል፣ ያንን ተከትሎ ስሟ በመላው ዓለም መናኘቱና በቅኝ ግዛት ስር የነበሩ መላ ጥቁር ሕዝቦች በፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ታግዘው ከቅኝ ገዥዎች ነጻ ለማውጣት ላደረጉት ትግል ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። ሀገሪቱ በቅኝ ግዛት ዘመን ብቸኛዋ የጥቁር ሕዝቦች ወኪል በመሆን በሊግ ኦፍ ኔሽን ተሳትፋለች፡፡ ይህም የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ከራሷ አልፎ ለጥቁር ሕዝቦች ጉልህ አስተዋጽኦ ያደረገ ነው፡፡

የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት እንዲመሰረት ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክታለች፡፡ ሀገሪቱ ለአፍሪካና ለአፍሪካ ሀገሮች በዲፕሎማሲው መስክ ያበረከተችውን አስተዋጽኦ የዲፕሎማሲውን ሳምንት በሚገባ የሚያስቃኝ እንደመሆኑ መንግሥት የኅብረቱ ጉባኤ ተሳታፊዎች ኢግዚቢሽኑን እንዲጎበኙት ማድረጉ ሀገሪቱ ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ብሎም ለመላ ጥቁር ሕዝቦች ያበረከተችውን አስተዋጽኦ በሚገባ እንዲረዱ ራሳቸውንም በሚገባ እንዲመለከቱና ለአህጉሪቱ ራእይና አጀንዳዎች ስኬት ቆርጠው እንዲነሱ ያደርጋል፡፡

ሀገሪቱም ይህንና ሌሎች የሀገሪቱን የዲፕሎማሲ ስኬቶችን የሚያመለክት ኢግዚቢሽን ነው ያዘጋጀችው፤ ይህን መድረክ ለጉባኤው ተሳታፊዎች ማሳየት የምትችልበት ትልቅ አጋጣሚ እንደመሆኑም የዘንድሮው የኅብረቱ መሪዎች ጉባኤ በኢትዮጵያ ትልቅ ስፍራ ይሰጠዋል፡፡

አፍሪካውያን ይህን ታላቅ የዲፕሎማሲ መድረክ በመመልከት የራሳቸውን የዲፕሎማሲ ጉዞ መለስ ብለው መቃኘት፣ የራሳቸውን የዲፕሎማሲ ሳምንት ማዘጋጀት፣ የዲፕሎማሲ ጉዞአቸውን በሚገባ የሚሰንዱበት መልካም አጋጣሚን መፍጠር የሚያስችላቸው እንደመሆኑ መላልሰው እንዲጎበኙት ለማድረግም ጭምር መስራት ያስፈልጋል፡፡

በዚህ በኩል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢግዚቢሽኑን የቆይታ ጊዜ እንደማራዘሙም ኢግዚቢሽኑን የጉባኤው ተሳታፊዎች መላልሰው በሚገባ እንዲጎበኙት በማድረግ በዚህም የኢትዮጵያን ገጽታ በተለይ የዲፕሎማሲ ዘርፍ ስኬቷን በሚገባ አውጥቶ በማሳየት የዲፕሎማሲ ሳምንት ኢግዚቢሽኑን የበለጠ ውጤታማ ማድረግ ይኖርበታል፡፡  

አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥር 30 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You