የ”ፀሐይ ዲፕሎማሲ…!”

የቅርስ ማገገሚያ ዲፕሎማሲ /Heritage Recov­ery Diplomacy/ ባሕላዊ ቅርሶችን፣ የጥበብ ሥራዎችን፣ ታሪካዊ ሰነዶችን እና ሌሎች ጉልህ የሆኑ ባሕላዊ፣ ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ከትውልድ ቦታቸው የተነቀሉ እና በአሁኑ ጊዜ በውጭ ሀገራት የሚገኙ እና ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ያለመ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን ይመለከታል። በቅኝ ግዛት፣ በጦርነት ወይም በሕገ-ወጥ ዝውውር ምክንያት ከሀገር የወጡ ቅርሶችን ይመለከታል። የዚህ ዓይነቱ ዲፕሎማሲ ቅርሶች ወደ ሀገራቸው ወይም ወደ ማኅበረሰባቸው እንዲመለሱ መደራደር ላይ ያተኩራል።

የቅርስ ማገገሚያ ዲፕሎማሲ ባብዛኛው የባሕል ቅርሶቹን በያዙት ሀገራት ወይም ተቋማት እና በቅርሶቹ ሕጋዊ ባለቤት ሀገራት ወይም ማኅበረሰቦች መካከል ውስብስብ ድርድርን ያካትታል። እነዚህ ድርድሮች ሕጋዊ፣ ሥነምግባራዊ እና ባሕላዊ ጉዳዮችን ሊመለከቱ ይችላሉ። እንዲመልሱ የሚፈለጉ ቅርሶች ካላቸው ፋይዳ የተነሳ ድርድሮች ስሜታዊ እና አድካሚ ሊሆኑ ይችላሉ። ባሕላዊና ሌሎች ቅርሶች ወደየመጡበት መመለሳቸው ብዙውን ጊዜ የፍትሕ ጉዳይ፣ የባሕል ቅርሶችን የመጠበቅ እና የማኅበረሰቡ ባሕላዊ ቅርሶቻቸውን የማስመለስ እና የመጠበቅ መብት ተደርጎ ይታያል። እንደ ዩኔስኮ ያሉ ብዙ ዓለምአቀፍ ድርጅቶች በስምምነቶች፣ መመሪያዎች እና ቅስቀሳዎች የቅርስ ማገገሚያ ጥረቶችን ይደግፋሉ ። ያመቻቻሉ።

የቅርስ መልሶ ማግኛ ዲፕሎማሲ ዲፕሎማቶችን፣ የሕግ ባለሙያዎችን፣ የአርኪኦሎጂስቶችን፣ የታሪክ ተመራማሪዎችን፣ የሙዚየም ባለሙያዎችን እና የሀገሬው ተወላጆች እና የአካባቢ ማኅበረሰቦች ተወካዮችን ጨምሮ የተለያዩ ተዋናዮችን ያካትታል። በመደራደሪያ ጉዳዮች ዙሪያ ያሉትን የሕግ ማዕቀፎችን፣ ባሕላዊ ስሜቶችን እና ታሪካዊ ሁኔታዎችን እንዲሁም በሚመለከታቸው አካላት መካከል መግባባትን እና ትብብርን ለመፍጠር ቁርጠኝነትን በጥንቃቄ መመርመርን ይጠይቃል። ቅርሶች ወደየመጡበት መመለሳቸው ብዙውን ጊዜ የፍትሕ ጉዳይ፣ የባሕል ቅርሶችን የመጠበቅ እና የማኅበረሰቡ ባሕላዊ ቅርሶቻቸውን የማስመለስ እና የመጠበቅ መብት ተደርጎ ይታያል።

በጥንታዊ የሀገራችን ታሪክ በተደረጉ ወረራዎችና ጦርነቶች ቅርሶች ወድመዋል። ተዘርፈዋል። ከዘመናዊው የኢትዮጵያ ታሪክ ወዲህ በመጀመሪያ የእንግሊዝ ጦር አፄ ቴዎድሮስን ለመውጋት በኋላ ደግሞ ጣሊያን ሀገራችንን በመውረር ቅርሶቻችንን አውድመዋል። ዘርፈዋል። እንግሊዞች ልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስን “ማርከው!? “በርካታ ጥንታዊ ብራና መጽሐፍትን፣ ጽላት፣ መስቀልና ሌሎች ንዋየ ቅድሳትን ዘርፈው ወደ እንግሊዝ የወሰዱ ሲሆን የፋሺስቱ ቤኒቶ ሞሶሎኒ አገዛዝ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ሀገራችን በወረረ ጊዜ የአክሱምን ሐውልት፣ ፀሐይ የተሰኘችውን አውሮፕላንና በርካታ ንዋየ ቅድሳትን ዘርፎ ወስዷል። እንግሊዝ ከዘረፈችው በመቶዎች ከሚቆጠር ቅርስ የአፄ ቴዎድሮስን ቁንዳላ የመለሰች ሲሆን፤ ጣሊያንም መጀመሪያ የአክሱም ሐውልትን ሰሞኑን ደግሞ “ፀሐይ” የተሰኘችውን አውሮፕላን ወደ እናት ሀገሯ ለመመለስ ተስማምታለች።

በ1940 ዓ.ም በፓሪስ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር በተደረሰ የሰላም ስምምነት አንቀጽ 37 መሠረት ማንኛውንም በአምስት ዓመታቱ የወረራ ዘመን ከኢትዮጵያ የዘረፈችውን ቅርስ እና ንብረት በ18 ወራት ጊዜ ውስጥ ልትመልስ ጣሊያን ቃል ገብታ ነበር። ይሁን አንጂ ጣሊያን የተለያዩ ምክንያቶችን በመደርደር ቅርሶቹን ሳትመልስ ቆይታለች። በተደረገው ተደጋጋሚ ጥረት እና የዲፕሎማሲ ሥራ ግን የአክሱም ሐውልት ቀደም ብሎ ተመልሶ የነበረ ሲሆን፣ የተሰረቀችው የኛ ፀሐይም ከተወሰደች ከ88 ዓመታት በኋላ ወደ ቤቷ ፊቷን መለሰች። ቀድሞ የተመለሰው የአክሱም ሐውልትም ሆነ ፀሐይ የሀገራቱን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጎልበትና ለተጨማሪ ግንኙነት ፈር ቀዳጅ ይሆናል ብዬ ስለማምን የ”ፀሐይ ዲፕሎማሲ”ብየዋለሁ።

“ፀሐይ” በ1935 ዓ.ም ሄር ሉድዊግ ዌበር የተባለው ጀርመናዊ ኢንጂነር እና የንጉሡ ፓይለት በወቅቱ ከነበሩ ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን በኢትዮጵያ የተሠራች የመጀመሪያው አውሮፕላን ናት። ስያሜውም የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ልጅ ልዕልት ፀሐይን ለማሰብ የተሰጠ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ላለፈው አንድ ዓመት ጊዜ ከጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጂኦርጂያ ሜሎኔ ጋር አውሮፕላኗ ወደ ኢትዮጵያ ስለምትመለስበት ሁኔታ ትልቅ ጥረት እና ሰፊ ንግግር ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ፀሐይ ባለሁለት መቀመጫ እና ሁለትዮሻዊ መቆጣጠሪያ ያለው ብሎም የባለከፍተኛ ኃይል ሞተር ባለቤት ተደርጋ የተሠራች አውሮፕላን ስትሆን፤

“ፀሐይ” ኮምፓስ፣ የአብራሪ መቆጣጠሪያዎች፣ ሁለት ያለ ፍሬን ማቆሚያ የተገጠሙ የማረፊያ ሽክርክሪቶችም አሏት። ሞተሩ ባለሰባት ሲሊንደር ዋልተር ቪነስ ሲሆን የውሃ ማቀዝቀዣ ስርዓት ያለውና ባለ115 የፈረስ ጉልበት ነው።“ፀሐይ” ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊት በኢትዮጵያ የተሠራች ብቸኛ አውሮፕላን ሰትሆን፤ ፀሐይ በውስን ሃብት እና ስፍራ በጊዜው የነበሩትን አናፂዎች እውቀት እና የእጅ ጥበብ በመጠቀም የተሠራች አውሮፕላን ናት። የ1930ዎቹ የአቪዬሽን ጥረት ማሳያ ሆና የተረፈችን አውሮፕላን ሲል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት መረጃ አመልክቷል።

የ”ፀሐይ” አውሮፕላን መመለስ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪውን በራሳችን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ለመተካት የቅስምና የወረት ስንቅ ናት ሲል የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የገለጸ ሲሆን፤ “ፀሐይ” አውሮፕላን ወደ ኢትዮጵያ መመለስን አስመልክቶ ባስተላለፈው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት÷ “ፀሐይ” አውሮፕላን በሀገራችን የአቪዬሽን ታሪክ ጉልህ ሚና ያላትና ከ87 ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ምድር ተሠርታ የተሳካ የሙከራ በረራ ለማድረግ መቻሏን አስታውሷል። በዳግም የጣሊያን ወረራ ወቅት ወደ ጣሊያን ተወስዳ በሙዚዬም ለዓመታት ተቀምጣ የነበረችው “ፀሐይ” አውሮፕላን ወደ ኢትዮጵያ ልትመለስ በመሆኗ የተሰማውን ደስታ ገልጿል፡፡ የ“ፀሐይ” መመለስ ለቀጣዩ ትውልድ ትልቅ መነቃቃትን የሚፈጥር ከመሆኑም በተጨማሪ አውሮፕላኗ የኢትዮጵያ አቪዬሽን ኢንዱስትሪ ኩራትና ሃብት መሆኗን አስገንዝቧል፡፡

የአንጋፋው የኢትዮጵያ አቪዬሽን ታሪክ አብነት የሆነችው እና በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ግዜ ተገጣጥማ በሀገሪቱ ሰማይ ላይ ናኝታ የነበረችው “ፀሐይ” አውሮፕላን ከበርካታ ዓመታት በኋላ ለሀገሯ እንደምትበቃ በመስማታችን ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶናል። ይህች አውሮፕላን ሀገራችን ዛሬ ለደረሰችበት የአቪዬሽን ዕድገት ፈር ቀዳጅ ከመሆኗም በላይ ለአቪዬሽኑ መስክ ዕድገት በየዘመናቱ ያለንን ቀናዒነት ማሳያ ምልክትም ናት። ይህች ብርቅዬ ታሪካዊ አውሮፕላን ለሀገሯ እንድትበቃ መንግሥትን ጨምሮ ማንኛውንም ዓይነት አበርክቶ ለነበራቸው አካላት ሁሉ ከፍተኛ ምስጋናችንን እናቀርባለን ሲል የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሥራ አመራር የተሰማውን ደስታ በቴሌግራም ገጹ ገልጿል።

“ፀሐይ” በ1935 ዓ.ም ሄር ሉድዊግ ዌበር የተባለው ጀርመናዊ ኢንጂነር እና የንጉሡ ፓይለት በወቅቱ ከነበሩ ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን በኢትዮጵያ የተሠራ የመጀመሪያው አውሮፕላን ነው። ስያሜውም የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ልጅ ልዕልት ፀሐይን ለማሰብ የተሰጠ ነበር።

የመጣበትና የፋሽስት ጣሊያን ወራሪ ኃይል ሀገራችንን የወረረበት ጊዜያት ይጠቀሣሉ፡፡ የአክሱም ሐውልትም ከሀገራችን ተወስዶ በሮም አደባባይ እንዲቆም የተደረገው የፋሽስት ወራሪ ኃይል አገራችንን በወረረበት እ.ኤ.አ በ1936 ዓ.ም ነው፡፡ ይህ የአክሱም ሐውልት ከእናት ሀገሩ ተዘርፎ ከተወሰደበት ጊዜ ጀምሮ በመላ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሕዝቦችና መሪዎች ዘንድ ከፍተኛ የሆነ ቁጭትን ፈጥሮ ነበር፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት ጨምሮ በሦስት የመንግሥት ሥርዓቶች ከግለሰብ ጀምሮ እስከ ሀገር መሪዎች ድረስ ሐውልቱን የማስመለስ ጥረቶች ሲደረጉ እንደነበር የታሪክ ማስረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

የሐውልቱ ይመለስልን ጥያቄ የተጀመረው ሐውልቱ ተዘርፎ በሄደበት ዓመት እ.ኤ.አ በ1936 ዓ.ም የወቅቱ የሀገራችን መሪ፣ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ባቀረቡት ክስ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በመቀጠልም ንጉሠ ነገሥቱ እ.ኤ.አ በ1955 ዓ.ም የዘውድ ም/ቤቱ በጣሊያን ስለተወሰዱ ቅርሶች እንዲመክርበት ማዘዛቸውን፤ እ.ኤ.አ በ1967 ዓ.ም ሐውልቱ እስካልተመለሰ ድረስ የወቅቱ ፓርላማ የጣሊያን ጎብኚዎችን ለመከልከል፣ የንግድ ማዕቀብ ለማድረግና የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን እስከ ማቋረጥ የሚደርስ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁነቱን ወስዶ እንደነበር፤ እ.ኤ.አ በሰኔ 1971 ዓ.ም ሁለት መሐንዲሶች ወደ ሮም ተልከው ስለ ሐውልቱ ጥናት አድርገው እንዲመለሱ መደረጉንና በጥናታቸው መሠረትም ሐውልቱን መመለስ እንደሚቻል ማረጋገጫ መስጠታቸውን፤ ወዘተ. መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ይህ ጥልቅ የሆነ አገር ወዳድነትና የቅርስ ተቆርቋሪነት ስሜት በሀገራችን ሕዝብ ልብ ስር ሰድዶ ይቆይ እንጂ በወታደራዊው የደርግ ሥርዓት ወቅት ሐውልቱን አስመልክቶ የፓርቲው ልሳን በሆነው “ሠርቶ አደር ጋዜጣ” ኅትመቶች ከመዘገብ ባለፈ ለማስመለስ የተደረገ ምንም ዓይነት ጥረት እንዳልነበረና የይመለስልን ጥያቄውም የተቀዛቀዘበት ሁኔታ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ወታደራዊው የደርግ አስተዳደር በ1983 ዓ.ም ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከተገረሰሰበት ማግስት ጀምሮ ግን ሐውልቱን የማስመለሱ ጉዳይ እንደገና ተጧጡፎ መቀጠሉን በተመሳሳይ መልኩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ሐውልቱን ለማስመለስ የነበረው ሕዝባዊ ግፊት ከፍ ብሎ ታዋቂ ግለሰቦች በራስ ተነሳሽነት ኮሚቴ በማቋቋም ጉዳዩን ወደ መንግሥት ማቅረብ የቻሉበት ወቅትም ነበር፡፡ ከደርግ ወታደራዊ መንግሥት ውድቀት ማግስት የተቋቋመው የሽግግር መንግሥትና በኋላም በኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሙሉ ይሁንታ ተመሥርቶ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት በሰጠው ልዩ ትኩረትና በወሰደው ቁርጠኝነት ሐውልቱን የማስመለሱ ሂደት ወደ አዲስ ምዕራፍ ለመሸጋገር በቅቶ ነበር፡፡ ከ1983 ዓ.ም በኋላ መንግሥት በግል ተነሳሽነት ተዋቅሮ ለነበረው የአክሱም ሐውልት አስመላሽ ኮሚቴ ድጋፍ ከመስጠት ባሻገር ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ተቋማት ያካተተ በመንግሥት የሚመራ የአክሱም ሐውልት አስመላሽ ብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ እስከ ማዋቀር ደረሰ፡፡

በመቀጠልም መንግሥት ልዩ ትኩረት በመስጠት ወደ መሬት የወረደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረጉ በጣሊያን መንግሥት በኩል የነበረው “ሐውልቱን አልሰጥም” አቋም እየላላ እና እየተለሳለሰ ሊመጣ ችሏል። ሐውልቱን ለማስመለስ በተደረጉ ጥረቶች ቀደም ብለው የተደረጉ ሁለት ስምምነቶች ቢኖሩም (የጣሊያን ፋሽስት መንግሥት በ2ኛው የዓለም ጦርነት መሸነፉን ተከትሎ እ.ኤ.አ በ1947 ዓ.ም ከተ.መ.ድ. ጋር የገባው ቅርሶችን በ18 ወራት ውስጥ ለኢትዮጵያ የመመለስ የሠላም ስምምነት እና እ.ኤ.አ በ1956 ዓ.ም ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የተደረሰው የሁለትዮሽ ስምምነት)፣ ፍጹም የሆነ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሶ ሐውልቱ ወደ እናት ሀገሩ ለመመለስ የበቃው ግን በሦስተኛውና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ም/ሚኒስትር የሚመራ አስራ ሦስት የተለያዩ ሙያተኞችን የያዘ አባላት ያሉት አንድ የልዑካን ቡድን ወደ ኢጣሊያ በመጓዝ ከየካቲት 21 እስከ 27 1989 ዓ/ም (እ.አ.አ የካቲት 1997) በሮም ቆይታው በቴክኒክም ሆነ በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ከኢጣሊያ አቻው ጋር ውይይት አድርጎ በተደረሰና በተፈረመ ስምምነት ነው፡፡

ከግማሽ ምዕተ ዓመታት በላይ በዘለቀው ያላሰለሰ የታዋቂ ግለሰቦች፣ ምሑራን፣ ሀገር በቀልና ዓለም አቀፍ ተቋማት ድጋፍና ግፊት እንዲሁም የፖለቲካ መሪዎች በሳል ዲፐሎማሲያዊ ጥረት የሐውልቱ መመለስ ዕውን ሲሆን፣ በጣሊያን መንግሥት በኩልም የነበረው ትብብር እፁብ ድንቅ የሚባል ነበር፡፡ የጣሊያን መንግሥት ሐውልቱ ከቆመበት የሮም አደባባይ ስለሚነሳበት፣ ስለሚጓጓዝበትና በቀድሞ ቦታው ስለሚቆምበት ሁኔታ በሀገራችን በኩል ተሰይሞ ሥራውን ሲሠራ ከነበረው ብሔራዊ አስመላሽ ኮሚቴ ጋር በቅንጅት ከመሥራቱ ባሻገር፣ በእያንዳንዱ ምዕራፍ ያለውን ሙሉ ወጪ በመሸፈን በአጠቃላይ ከስድስት ሚሊዮን ዩሮ በላይ ወጪ በማድረግ በቀድሞው የጣሊያን ፋሽስት መንግስት በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያውያን ላይ ጥሎት ያለፈውን ታሪካዊ ጠባሳ የሚያለዝብ ሥራ ለመሥራት በቅቷል፡፡

ሻሎም ! አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)

አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥር 30 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You