ወላይታ ሶዶ፡- የወላይታ ሶዶ ከተማ እና የጣሊያኗ ብራቻኖ ከተማ በባህል ያላቸውን አንድነት ለማጠናከር የሚያስችል የእህትማማችነት ስምምነት ተፈራረሙ። የባህል ግንኙነቱን በልማት ለማጎልበት እንደሚሠራም የሁለቱ ከተሞች አመራሮች ገለጹ።
በወላይታ ሶዶ ከተማ ሰሞኑን በተደረገው ‹‹ ሰላም የባህል ፌስቲቫል›› የወላይታ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ደጋፎ ኩንቤ እንደተናገሩት፤ የወላይታ ሶዶ ከተማ ከጣሊያን ከተማ የገንዘብ እገዛ ሳይሆን የምትፈልገው ከተማዋ ያላትን እምቅ አቅም በቴክኖሎጂ ታግዛ እንዴት ተጨማሪ ሀብት ማፍራት እንደምንችል ትምህርት ለመቅሰም ነው። የልምድ ልውውጡም ለዕውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግሩ የማይተካ ሚና ይኖረዋል።
ጣሊያን የወላይታ ዞንን በተመለከተ ከማስተር ፕላን ጀምሮ ስትደግፍ መቆየቷን አስተዳዳሪው ጠቅሰው፣ ወላይታ ሶዶም ከዚህ ልምድ ቀስማ ብራቻኖ ከተማን ለመሆን እንድትተጋ ፍላጎቱ እንዳለ ተናግረዋል። በተለይም ያሉት ባህላዊ ቅርሶችና የተፈጥሮ ሀብቶች ተጨማሪ ሀብት አስገኝተው አገር እንደሚቀይሩ ጠቅሰው፣ስምምነቱም ለዚህ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
የወላይታ ሶዶ ከተማ ከንቲባ አቶ ሀንጄላ ደሴ በበኩላቸው ‹፤ስምምነቱ ጠቀሜታው ለከተማዋ ብቻ ሳይሆን ለአገርም ጭምር መሆኑን ጠቅሰው፣ ወላይታ ሶዶ ስትለማና በቱሪዝሙ ዘርፍ ስትልቅ አገርም አብራ ከፍ ትላለች ብለዋል።
በክብርት ዶክተር ሰናይት ማሪዮ የተጀመረው የሁለቱ ከተሞች ቅርርብ መጠናከር እንደሚኖርበት ተናግረው፣ ለዚህም ከባህል የዘለለ የልማት ትስስር በማድረግ እንደሚሠራም ጠቁመዋል።
እንደ አቶ ሀንጄላ ገለጻ፤ የወላይታ ሶዶ ከተማ ከብርቻኖ ከተማ ብዙ የሚያመሳስላት ነገር አለ። የመጀመሪያው የመልከአምድር አቀማመጧና የቱሪስት መስህብ መሆኗ ነው። በዚህም ይህንን እምቅ ሀብት በመጠቀም ወላይታ ሶዶ ላይ ለመሥራት ጥረት ይደረጋል። ሌሎች የከተማዋንም ምርጥ ተሞክሮ ለማየት የሚሞከር ይሆናል። ለዚህ ስኬት ግን ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል።
የፕሮግራሙ አዘጋጅ የክብርት ዶክተር ዲዛይነርና ሞድሊስት ሰናይት ማሪዮ ፤ ሌሎች አገሮች በሌላቸው ሀብት ራሳቸውን በስፋት ይሸጣሉ ፣ያስተዋውቃሉም። በዚህም ገንዘብ ያገኛሉ ሲሉ ጠቅሳ፣ ኢትዮጵያ ከዚህ የተለየች በመሆኗ የተፈጥሮም ሆነ የባህልና ቅርሶቿን በመያዝ ሀብት በማድረግ ላይ መሥራት አለባት ብላለች። ለዚህም አገር ወዳድና በየአለበት ሆኖ ስለአገሩ የሚጨነቅ ዜጋ ሊኖር እንደሚገባም ተናግረዋል። አንድ ከተማ ወይ ዞን ሲያድግ አገር ትለወጣለችና መሠራት አለበት ብላለች።
ዲዛይነርና ሞድሊስት ሰናይት እንደ አገር ያለንን ሀብት ማሳወቅ ላይ ብዙ አልተሠራም ስትል ገልጻለች። በተለይም በግለሰብ ደረጃ ተነሳሽነት ያላቸው አካላት ለአገር መሥራት ላይ ከቤተሰብ ወጥተው ለአገር እውቅና መቆም ላይ መሥራት ልምድ ሊሆን እንደሚገባ አስገነዝባለች። የአገራት ትስስር ለአገሪቱ ዕድገት ትልቅ ሚና እንዳለው በመግለጽም፣ እነዚህ ዓይነት ዕድሎች እንዳያመልጡን መሥራት ያስፈልጋል። በልማት ማስተሳሰርም ይገባል ብላለች።
አዲስ ዘመን ግንቦት 28/2011
ጽጌረዳ ጫንያለው